የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ውስጣዊ ቍጣ ክፍል 9

“የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና ።” ያዕ. 1 ፡ 20 ።

10 – ፍላጎትን አለማወቅ

በትዳር ውስጥ ከሚነሡ ጠቦችና መሰለቻቸቶች አንዱ ፣ አንደኛው ወገን የሚፈልገውን አለማወቁ ነው ። እርሱን ለማስደሰት አንድ ነገር ሲደረግለት አይረካም ። ለምሳሌ ጫማ እፈልጋለሁ ብሎ በደመ ነፍስ ፍላጎቱን ይናገራል ። ጫማው ተገዝቶ ሲመጣ ግን ደስተኛ አይሆንም ። ቢረካ ተብሎ ጫማ ፋብሪካው ይከፈትለታል ፤ የበለጠ ኀዘነተኛ ይሆናል ። ስለዚህ መነጫነጭ ፣ ማዘን ፣ ማልቀስ ፣ ሌሎችን መክሰስ ያበዛል ። ለማስደሰት የሞከረው ሰውም ሙከራውን ሲጨርስ ፣ አቅርቦቱን ሲያጣ መሰልቸት ይጀምራል ። መፈራራትና ላለመገናኘት መንገድ መፈለግ ይጀመራል ። ይህም በትዳር ውስጥ ያለውን ክፍተት እያሰፋው ይመጣል ።

ብዙዎች ይሠራሉ ፣ ይነግዳሉ ፣ ይሮጣሉ ምን እንደሚፈልጉ ግን አያውቁትም ። አንድ ሕንፃ ይሠራሉ ፣ እርሱን ሳያጣጥሙት ሁለተኛው ያምራቸዋል ። መንግሥት ቤት የሚሠራ ሠራተኛ በቃህ ፣ ዕረፍ ተብሎ ጡረታ ይወጣል ። የግል ሥራቸውን የሚሠሩ ግን መቆሚያ በሌለው አዙሪት ውስጥ ይገባሉ ። ይሰበስባሉ ለምን እንደሚሰበስቡ ግን አያውቁም ። ራሳቸውን በድለው ያጠራቀሙት ገንዘብ ፣ ጤናቸውን ጎድተው የሰበሰቡት ሀብት ግቡ ምን እንደሆነ አያውቁም ። ለትዳራቸው ለልጆቻቸው ጊዜ ነፍገው ፣ የፍቅር ጥያቄን በገንዘብ እየመለሱ መኖር የሚችሉ ይመስላቸዋል ። ዓይናቸውን ሲገልጡ ግን ትዳራቸው ሄዷል ፣ ልጆቻቸው ከድተዋቸዋል። ትዳር ጊዜን የሚካፈሉበት ትልቅ ተቋም ነው ።

የሚፈልጉትን የማያውቁ በመስገብገብ ፣ ሌላውን ሰልቅጦ በመዋጥ ፣ ሁሉም ነገር የእኔ ይሁን በማለት ብዙ ጠላት ያፈራሉ ። ፍላጎትን የማያውቅ ሰው ድንበር የለውም ። የሚያቆመው ነገር አይፈልግም ። ፍላጎትን ባለማወቁ ምክንያት የመጣበትን አለመርካት ፣ ያበዛውን የጠላት ቍጥር ፣ የደረሰበትን ብቸኝነት ሲያስብ ውስጣዊ ቍጣ ይገጥመዋል ። የማይፈለግ ሰው መስሎ ራሱ ይሰማዋል።

በሃያዎቹ መጀመሪያ ያሉ ወጣቶች የሚፈልጉትን ነገር መለየት ያቅታቸዋል ። ሠዓሊ ሲያዩ ሠዓሊ መሆን ፣ ሙዚቀኛ ሲያዩ ሙዚቀኛ መሆን ያምራቸዋል ። ያልተሰጣቸው ይሆንና አቅም ሲያጡ፣ ገደብ ሲገጥማቸው ተስፋ ይቆርጣሉ ። የሚፈልጉትን ነገር በትክክል ቢያውቁ ከብስጭት ይድናሉ ። የሚፈልጉትን ማወቅ እንዲህ በቀላል የሚገኝ ላይሆን ይችላል ። የጸሎት ኃይል ፣ የአባቶች እገዛ ያሻዋል ። የሚፈልጉትን ባለማወቅ ከሃይማኖት ሃይማኖት የሚገላበጡ ፣ አህያ “እኛ ያልፈሳንበት ዳገት የለም” ብላ በክብር እንዳወራችው ፣ ያላየነው ሃይማኖት የለም በማለት ነውሩን እንደ ክብር የሚያወሩ ሰዎች አሉ ። እነዚህ ሰዎች የሚገጥማቸው ችግር ሦስት ዓይነት ሊሆን ይችላል ። የመጀመሪያው ከሀዲ መሆን ነው ፣ ሁለተኛው ሚና የለሽ መሆን ፣ ሦስተኛው ምግባር የለሽ መሆን ነው ። የምፈልገው ምንድነው ? ብለው ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው ። በዚህ ምክንያት እነዚህ ሰዎች በብስጭትና ሁሉም ነገር ባዶ ነው በሚል ስሜት ውስጥ ይወድቃሉ ። ምርጫችን እንጂ ሕይወት ከንቱ አይደለችም ።

ስለዚህ ሰው አስቀድሞ የምፈልገው ምንድነው ? ማለት አለበት ። የሚፈልገውን ካወቀ ገበያ ላይ ያየውን ሁሉ ልግዛ አይልም ። ቤቱን በማይጠቀምበት ሸቀጥ ሞልቶ መራመጃ አያጣም ። ሁሉም የእኔ ይሁን ብሎ ራሱን አይከስርም ። ድንበር የለሽ ሆኖም ጠላት አያበዛም ። አብረውት ለሚኖሩት ወዳጆቹም ጥያቄ አይሆንም ። የብዙ ሰዎች ዕረፍት ማጣት ፣ መነጫነጭ ፣ ማዘንና ማጉረምረም ከእኛ ጋር በተያያዘ ሳይሆን የሚፈልጉትን ባለማወቅ የመጣ ነው ። እኛም የምንፈልገውን የማናውቅ ከሆነ ተሰቃይተን ሌላውንም ሰው እናሰቃያለን ። ሰው ስላደረገው ብቻ የምናደርገው ፣ ሰው ስለገዛ ብቻ የምንገዛው ነገር እርካታ ቢስ ያደርገናል ። በአገራችን ከጎን ሰው ሳያዩ ምንም ማድረግ የተከለከለ ይመስላል ። ራሱ የሚያስደስተውን ከሚለብስ ፣ ሰዎች ይደሰቱበታል የሚለውን የሚለብስ ይሆናል ። ራሱ የሚኖርበትን ቤት የሌሎችን ደስታ በማዳመጥ ያንጸዋል ። በመጨረሻ ይሰለቸዋል ። ከገንዘቡም ከኅሊናውም መሆን ስለሚያቅተው ብስጭት ውስጥ ይገባል ።

አዎ ውስጣዊ ቍጣ ከሚያመጡ ነገሮች አንዱ የሚፈልጉትን አለማወቅ ነው ። ሥራ አልን ሥራ መጣ ፣ ትዳር አልን ትዳር ያዝን ፣ ልጆች አልን ልጆች አገኘን ። የምንጠራው ፍላጎት በመጣ ቍጥር የእኛ ደስታ እየራቀ ከመጣ የመጀመሪያው የምንፈልገውን አለማወቅ ሲሆን ሁለተኛው ከክርስቶስ የሚገኘውን ደስታ ከዚህ ዓለም ንብረትና ሰዎች እየፈለግን ነው ማለት ነው ። ዛሬ የምፈልገው ምንድነው ? በማለት ጊዜአችንን ፣ ገንዘባችንን ፣ ደስታችንን እናትርፍ ! እንደ እርጉዝ ሴት በመቅበጥበጥ ፣ ያምረናል እንጂ የሚያምረንን መለየት የማንችል ሰዎች መሆን አይገባንም !

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 16 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ