የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ውቅያኖስን በዋና

የኃጢአት ማዕበል የሚያንገላታቸውን ፣ ወጣሁ ሲሉ የሚዘፈቁትን በደለኞች ያየው ዮሐንስ መጥምቅ ፤ ከኃጢአት ነጻ የሆነውን ፣ የዓለምን ዕዳ የሚያስወግደውን የእግዚአብሔር በግ አየ ። ብዙ የወደቁትን አይቶ ዘመን የማያናውጸውን ጌታ አየ ። ከአዘቅት እስከ ምጥቀት አየ ። የሥነ ልቡና አማካሪዎች ፣ የሰውን ኃጢአት ሲሰሙ የሚውሉ አባቶች ፣ በደለኞችን ለንስሐ የሚጋብዙ ሰባኪዎች ሥራቸው ትልቅ ዋጋ እንዳለው የጌታችን መገኘት ይገልጻል ። በምድር ላይ ከተራራ ይልቅ የሚመዝን ሸክም አለ ፤ እርሱም ኃጢአት ነው ። ከበሰበሰ ውኃ ይልቅ የሚሸት ክፉ ጠረን አለ ፤ እርሱም ኃጢአት ነው ። ከሰናዖር ግንብ ይልቅ የሚረዝም ግድግዳ አለ ፤ እርሱም ኃጢአት ነው ። የነካውን ሁሉ የሚመርዝ የዛገ ብረት አለ ፤ እርሱም ኃጢአት ነው ። በካንሰር የሚሰቃዩ ሰዎችን እናውቃለን ። የኃጢአት ሕመም ፣ የጸጸት ስሜት ከዚያ በላይ የሚጠዘጥዝ ነው ። ኃጢአት ከአጥንት ስብራት ፣ ከሴት ምጥ ይልቅ ከባድ ሕመም አለው ። የንስሐ ሰባኪዎች ፣ አማካሪዎች ፣ ኑዛዜን የሚሰሙ ለድኩማነ ነፍስ ትልቅ እፎይታ ይሰጣሉ ። ኃጢአት ጸጸት ብቻ ሳይሆን የሞት ዕዳም ያለበት ነው ። ባለ ቅኔው እንዲህ ብሏል፡-

ከጎጃም ከዳሞት ፣
የቱ ይበልጣል በስፋት ፤
አስተውሎ ላየው፣
ትልቁ ዳሞት ነው ።

ዮሐንስ በረሀብ አንጀቱ ፣ በበረሃ ዝለቱ ፣ በጋለው አሸዋ ፣ በሚያቃጥለው ምድረ በዳ ቆሞ እነዚህን ደካሞች ያግዛል ። ኃጢአተኞች በጌታችን አጠራር “ደካሞች” ናቸው ። ለጽድቅ የደከሙ ፣ ለኃጢአት ግን የበረቱ ናቸው ። ኃጢአተኞች ቀራጮች ናቸው ። ለባዕድ መንግሥት ሰውነታቸውን የሚያስገዙ ናቸው ። ኃጢአተኞች እግዚአብሔር ይማርህ አልተባሉም እንጂ ታማሚዎች ናቸው ። ጌታችን በመስቀል ላይ “ይቅር በላቸው” በማለት እነዚህን ሕሙማነ ነፍስ ጠይቋል ። ባለ መድኃኒት በበሽታ ዓይነት አይደነቅም ፣ መድኃኒትን ይሰጣል እንጂ ። መንፈሳውያን አማካሪዎችም በኃጢአት ዓይነት ሊደነቁ አይገባም ። የእግዚአብሔር ምሕረት የማያሸንፈው ኃጢአት የለም ። ጌታችን ለተነሣሕያንና ለንስሐ ሰባኪዎች እውቅና ሊሰጥ በዮርዳኖስ ተገኘ ።

ነገ መስቀል ላይ የሰውን ኃጢአት የሚሸከመው ክርስቶስ አሁን በኃጢአተኞች መካከል ተገኘ ። ፀሐይ በቆሻሻ ቦታ ብትወጣ እንደማትቆሽሽ የእርሱ ንጽሕናም በሰዎች በደል አይረክስም ። እውነተኛ ጻድቅ ኃጢአተኞችን አይገፋም ። በደለኛ ሲያገኝም ድንጋይ በመወርወር የራሱን ጽድቅ አይሠራም ። የቱንም ያህል ብንቀደስ የክርስትናው የመልክ ጥግ ክርስቶስን መምሰል ነው ። እርሱን ዕድሜ ልካችንን በሙሉነት መምሰል አንችልም ። ስለዚህ ክርስትና የማያቋርጥ ዕድገት ነው ። እውነተኛ ማንነታችንን የምናገኘው ከደካማው ወንድም ጋር ራሳችንን በማስተያየት ሳይሆን በቃሉ ነው ። እውነተኛ ሚዛን ቃለ እግዚአብሔር ነው ። ስድስቱ ቃላተ ወንጌል ተብለው የሚጠሩት ኃጢአተኞችንም ይመለከታሉ ። “ብራብ አብልታችሁኛል” የሚለው ኃጢአተኛ የጽድቅ ረሀብተኛ ፣ የሰላም ጥማተኛ ነው ። ውስጡ እያረገረገበት ፣ “ልወድቅ ነው” ብሎ የሚሰጋ ነው ። ኃጢአተኛ በገዛ አገሩ ባይተዋር ነው ። ብዙ ሱሰኞችን የሚቀርባቸው ሰው የለም ። እስረኛ ነው ። ሥልጣን ያለው አካል ነጻ ሊያወጣው ይገባል ። ኃጢአተኛ ሕመምተኛ ነው ። ሥጋው በበሽታ ፣ ነፍሱ በድንቁርና ፣ መንፈሱ አምልኮተ እግዚአብሔርን በማጣት ታማሚ ነው ።

በብሉይ ኪዳን የኃጢአት መሥዋዕት ይቀርብ ነበር ። የማስተስሪያ በዓል ቢከበርም ስርየት ስላልመጣ ቀኑ “የኃጢአት መታሰቢያ ቀን” ነበር ። ዛሬ የአንዳንድ በሽታዎች ዓመታዊ ቀን ይታሰባል ። በብሉይ ኪዳን የነበረው የማስተስሪያ ቀን ስርየትን ስላላመጣ የኃጢአት መታሰቢያ ቀን ነበር ። በየዕለቱ የሚቀርቡት መሥዋዕቶች በዋጋ የሚገዙ ነበሩ ። ኃጢአት ዋጋ ያስከፍላል የሚል መልእክት አላቸው ። ሰሎሞን በአንድ ቀን ከሃያ ሺህ በላይ መሥዋዕቶችን አቅርቧል ። እነዚህ መሥዋዕቶች ቍጣን ማብረድ እንጂ ማጥፋት አልቻሉም ። እንኳን ለዓለም ሁሉ ሊበቁ እስራኤልን ማስማር ያልቻሉ መሥዋዕቶች ነበሩ ። መሥዋዕቶቹ ኃጢአትን አዳፈኑ እንጂ ማስወገድ አልቻሉም ። የሰው በግ ነበሩና ይህን ማድረግ አልቻሉም ። የሰው መፍትሔ ለራሱም አይበቃም ። ዮሐንስ ግን የእግዚአብሔር በግ ብሎ ጮኸ (ዮሐ. 1፡29) ። አንድ ጊዜ ተሠውቶ ለዘላለም የሚበቃ መሥዋዕትን አስተዋወቀ ። ዋጋው ሰማይና ምድር የማይችሉት ፣ ከዋጋ በላይ የሆነ ፣ ለዋጋዎች ዋጋን የሰጠ ነው ። ስለዚህ ዓለመ ሰብእን ብቻ ሳይሆን ዓለመ መላእክትንም ማስማር የሚችል በግ ነው ። አንድ በግ ለመላው ዓለምና ዘመን ተሰጠ ። ዮሐንስ ይህን በግ ለዓለም አስተዋወቀ ።

ዮሐንስ ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር- እነሆ የእግዚአብሔር በግ ይላል ። አብ በደመና “ልጄ” ይለዋል ። አብርሃም ልጁን ሊሠዋ ሲል የከለከለው እግዚአብሔር አብ አሁን ልጁን ለዓለም ቤዛ ሰጠ ። ፍቅር ለሌላው ጨክኖ ለራስ ማዘን አይደለም ። የልጃቸው ትኩሳት የሚረብሻው ባለሥልጣናት የሚሊየን ሕዝብ እልቂት አይገዳቸው ይሆናል ። እግዚአብሔር አብ ግን ለበደለ ባሪያ ልጁን ሰጠ ። ልጅን ለወዳጅም ምትክ አይሰጡትም ። ስጦታ ሁሉ የሚሰጥ የፍቅር መግለጫ ነው ። ስጦታው ራሱን ሰጠን ፣ ራሱን የሚሰጥ ስጦታ ክርስቶስ ብቻ ነው ። ለሌላው ከራሳችሁ ያነሰውን አትስጡ ሊል መጣ ። “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ብሎ በኦሪት ያዘዘው ፤ አሁን ግን ነፍስን ለወዳጅህ በመስጠት ከራስህ በላይ ውደደው አለ (ዮሐ. 15 ፡ 13) ።

ኦ ጌታ ሆይ! ፍቅርህን እያረፍን እናስበው ፣ ውቅያኖስን በዋና ማቋረጥ የማይቻል ነው !!! የምትወዱት እልል በሉለት !

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ. ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ