የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዐርፍ ዘንድ ተወኝ (13)

“ በከንቱ ይታወካል እንጂ በእውነት ሰው እንደ ጥላ ይመላለሳል ያከማቻል የሚሰበስብለትንም አያውቅም።”

(መዝ. 38 ፡ 6 ።)

በዓለም ላይ በታወቁ የልብሰው ዲዛይነሮች አስነድፈው ይለብሱ የነበሩ ሰዎች ዛሬ የሉም ። ንጹሕ መልበስ እንጂ ልዩ ለመሆን መልበስ በእውነት ከንቱ ነው ። ልብስም ብል ፣ ሥጋም አፈር ይበላዋል ። የእግራቸው ኮቴ ፣ የጫማቸው ደወል ከሩቅ የሚሰማው “እነ እገሌ መጡ” ለመባል ይከጅሉ የነበሩ ያ ድምፅ ከጠፋ ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል ። እነርሱን ባሰጠመ መንገድ ለመሄድ ፣ የእነርሱ እንጂ የእኔ ዱካ አይደበዝዝም ብሎ ለማሰብ መልአክ መሆን ይጠይቃል ። መልአክም በትዕቢት እንደሚሞት ሰይጣን ምስክር ሁኖ ቆሟል ። ሞትም የማያበቃ ዘላለም አዘቅት መውረድ መሆኑን ዲያብሎስ ይመሰክራል ። ትዕቢት ዘላለማዊ ሞትን ያመጣል ። ሽቶአቸው የሚያውድ ፣ ያለፉበትን ሰፈር የሚያነቃንቅ ፣ የተቀቡት ቅባት እጃቸውን የጨበጠ ሰው ሁሉ ላይ የሚታተም ላለመረሳት ፣ በደግ ለመታወስ ይጥሩ የነበሩ ዛሬ አይታሰቡም ። መቃብራቸውንም የሚያውቅ ማንም የለም ። በልቅሶአቸው ቀን ያበዱላቸው አንድ ቀን መቃብራቸው ላይ አበባ ለማስቀመጥ አልሄዱም ። እነዚህን ሸኝተን እኛ እንደ ደመቅን እንኖራለን ብሎ ማሰብ በእውነት ከንቱነት ነው ።

ብዙ ዘመድ የነበራቸው አንድም ሰው ለአንድ ቀን መቃብራቸው ስፍራ አላደረላቸውም ። አንድም ቆራጥ አልተከተላቸውም ። የሞት መንገድ አጃቢ የለውምና ። ከመቃብር ወዲያ የማያገኙትን ዘመድ ብሎ መጥራት በእውነት ሐሰት ነው ። ይህን ሁሉ ዘንግተን የእኔ ዘመዶች ከተማውን ሁሉ ይሞላሉ እያልን ብቸኞችን እናሸማቅቃለን ። ጎዳና ላይ የወደቀ ድሀ ሁሉ ባለጠጋ ዘመድ አለው ። ዘመድ ግን የሚወድደው ገንዘብ ያለውን ነው ። ዝምድና ያለ ገንዘብ ብቻውን መቆም አልቻለም ። “የሌለውን ልጅ እናቱም ትጠላዋለች” ይባላል ።

ትምህርት ቤት ፣ ድልድይ ፣ ሆስፒታል ፣ እጓለ ማውታ በስማቸው የተሰየመላቸው ስማቸው ዛሬ ወድቋል ። ዓለም ተረኛ እንጂ ቋሚ ወዳጅ የላትም ። ፍቅሯም የኮንትራት እንጂ ጽኑ አይደለም ። በየአምስት ዓመቱ መሪዎች ካልተለዋወጡ ፣ የሕይወት ዘመን ኪዳን የሆነው ትዳርም በየወሩ የሚታደስ ውል ካልሆነ እያለች የምታስቸግር ዓለም ናት ። ሰው በእውነት በከንቱ ይታወካል ። የሚሆነው ከመሆን ላይቀር ይሸበራል ። እንቅልፍ ያጣበት ጉዳይ ፣ ቀኑን ጨለማ ያደረገበት ክፉ መርዶ ፣ ሞትን እንዲመኝ ያደረገው ጉድለት እርሱ የቀረ ቀን አብሮ ይቀራል ። ሁሉም ነገር እንደ ተጻፈለት ይቀጥላል ። ተጨናቂው ግን ዕድሜውን ያሳጥራል ። ግዴለሾች እየኖሩ የሚታወከው ሰው በፍርሃት ዘመኑ ይቆረጣል ። “እኔማ አላጣም” በማለት በእምነት ሳይሆን በልበ ሙሉነት የሚናገሩ ሰዎች ሞልቶላቸው ፣ ተጨናቂው ግን የጨበጠውን እየጣለ መንገድ ይቀራል ።

ዳዊትን ያስጨነቁት ነገሮች ብዙ ናቸው ። ግን ከንቱ ነበሩ ። ምክንያቱ ጭንቀትን ልክ አያደርገውም ። ጭንቀት አለማመን ነው ። ልናገር አልናገር እያለ ዳዊት ሲጨነቅ ኖሯል ። ሲናገር የሚቀየመው ፣ ዝም ሲል ግዴለሽ እያለ የሚታዘበው ብዙ ሰው ነበር ። ድንገተኛ ውሳኔም ዋጋ ሲያስከፍለው ኖሯል ። በዚህ ምድር ላይ ሰባና ሰማንያ ዓመት ሳይሆን ዘላለም የሚኖር እየመሰለው ፈርቷል ። ለዕለት ምግቡም ጎተራ እህል እንደሚጨርስ ያህል ተጨንቋል ። የልክ ዓለም መሆኑን ዘንግቶ ከልኩ ላያልፍ ፣ አንድ ቀን ሁሉን ጥሎ ሲሄድና እንደሚረሳ ዘንግቶ ታውኳል ። የተጨነቅነው በከንቱ ነው ። ተጨንቀን ካቀረብነው ያራቅነው ይበዛል ። ተጨንቀን ብናገኝም ጭንቀቱ በሽተኛ ስላደረገን ልንበላው አንችልም ። የኖርንላቸውና የአንድ ቀን መከፋታቸውን ማየት ያልፈለግንላቸው ወዳጆች ሁሉም እንደ ጉም በነዋል ። የዕድሜ ልክ ልፋት በአንድ ቀን አዋጅ ይወረሳል ። “በዚህ ዓለም ላይ ማግኘትህን የሚወድ ሌባ ብቻ ነው” ይባላል ። እርሱም ሊሰርቅ ነው ።

ስለ መሰብሰባችን እንጂ ስለ መብላታችን እርግጠኛ አይደለንም ። የዓለም ሚሊየነር ተብለው የተጻፉ ዛሬ የቁም እስረኞች ናቸው ። ንብረታቸውን ብዙ ሺህ ሕዝብ የሚበላው ባለጠጎች በክፉ በሽታ ተሰቃይተው ሞተዋል ። ቢሊየነርነትን ስንመኝ እንደ እነርሱ ለመሆን ፣ ፍጻሜአችንን ለማስጨነቅ እየፈለግን ነው ። ለራሳችን የሰሰትነውን ገንዘብ አንድ ቀን ጠላት ይበላዋል ። ያልለፉበት ገንዘብ ነውና ልጆቻችን ለሱስ ይበትኑታል ። ከሰማይ ቤት ሁነን የምድር ንብረታችንን ማዘዝ አንችልም ። ብንቆጣም የሚሰማን የለም ። ሰው እንደ ጥላ ይመላለሳል ። ጥላ አንዴ ከፊት አንዴ ከኋላ ይሆናል ። ሰውም አንዴ ትልቅ አንዴ ትንሽ እየሆነ ይዘልቃል ። ሲመሽ ጥላ ለዘላለም ይከዳል ፣ ሰውም ለነፍሱ ከሠራው በቀር በምድር ላይ የኖረለት ክብር በሞት ያበቃል ። ሞት መጨረሻው ያልሆነ በእግዚአብሔር የሚያምን ሰው ብቻ ነው ። ከንቱነትን በትንሣኤው ጌታ ካልሆነ በሀብት መሻር አይቻልም ።

የምድር ኑሮ ጥላ ነው ። አካል ባለበት ጥላ ይታያል ። ሰማይ ስላለ የምድር ኑሮ እርግጠኛ ሆኗል ። የሚታየው ኑሮ መሠረቱ የማይታየው እግዚአብሔርና ቃሉ ናቸው ። የሚታየው ኑሮ መጠቅለያውም የማይታየው ዓለም ነው ። ለዚያ ንስሐ ያስፈልጋል ። ታምሜአለሁ በማለት ብቻ የሚያድን አንድ ፍጹም መድኃኒት አለ ። እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ