የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዐርፍ ዘንድ ተወኝ (14)

“አሁንስ ተስፋዬ ማን ነው ? እግዚአብሔር አይደለምን ? ትዕግሥቴም ከአንተ ዘንድ ነው ።”

መዝ. 38 ፡ 7 ።

የኀዘን እንጉርጉሮው እንዲህ ይላል፡-

“አልተሰበሰበም ያገሬ አዝመራው ፣
ዛላው ዛላው ወድቋል በየጎዳናው ፤”

ወጥቶ መቅረት ለአገራችን ወጣት ታሪኩ ሆኗል ። ይህን በምንጽፍበት ሰዓት እንኳ በስደት ላይ ሁኖ በባሕር በበረሃ የሚገደል ወጣት አለን ። በዱር በገደል የሚሞት ጎበዝ ተሸክመናል ። ገዳይም ሟችም እኛው ሆነን ለጋ ወጣቶችን መሸኘት ሥራችን ሆኗል ። አንድ ወጣት ተወልዶ እስከዚህ እስኪደርስ ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታል ። እንኳን ሞቱ ከባድ እንቅልፉ የሚያስፈራው ልጅ ትርጉም በሌለው ነገር ረግፎ ቀረ ። መሬቶች በሰው ደም ማብቀል እስኪሳናቸው ፣ ከተሞች እስኪበከሉ ፣ አራዊት በቀን እስኪወጡ ብዙ ቅጠሎች ሳያፈሩ ጠወለጉ ።

ወንድ ልጅ አትደግ የተባለበት ዘመን ፣ “ልጄ ቁመቱ አደገ ያፍሱብኛል” ተብሎ ወላጅ የሰጋበት ጊዜ ብዙ ነው ። የአሳብ ልዩነትን በጠረጴዛ ሳይሆን በጥይት የሚያስተናግዱ ልዩ ሕዝቦች እስክንመስል ፣ በተውሶ በመጣ ርእዮተ ዓለም ተጨራረስን ። ከራሽያ በላይ አሜሪካንን ለራሽያ ወግነን ጠላን ። የራሳችን አሮብን የሰው አማሰልን ። ፖለቲካ ቋሚነት የሌለው መሆኑን ባለማወቅ እንደ ሃይማኖት ወስደነው ሃይማኖት አደረግነው ፤ ውጤቱ ተፋጀንበት ። የኑሮንና የሞትን ትርጉም የማያውቁ ወጣቶች በየጎዳናው ወደቁ ። በደማቸው መፈክር ተጻፈ ። ጎረቤት የጎረቤትን ልጅ በላ ። አባትና ልጅ አንዱ አንዱን አሳልፎ ሰጠ ። ይህን መርከስ “አብዮት ልጇን በላች” በሚል ቅብ ሸፈንነው ።

ለ17 ዓመታት የተካሄደው የማያቋርጥ ጦርነት አገሩን እንደ ቋያ እሳት በላው ። ፓትርያርክና ንጉሥን አንቀን ገደልን ። እግዚአብሔርን በአደባባይ ካድን ። ከጦርነት አረፍን ብለን የቆየነው ለ7 ዓመታት ነው ። እንደ ገና በ1990 ዓ.ም ብዙ ሺህ ወጣቶችን የቦምብ ማብረጃ አደረግን ። ጦርነቱ ግን ትርጉም አልነበረውም ። እስካሁንም ያልተቋጨ ምዕራፍ ነው ። 17 ዓመታት የተጫረሰ ማኅበረሰብ ዕረፍት ያደረገው ለ7 ዓመታት ነው ። በቅርቡም በሚሊየን የሚቆጠር ወጣት ገብረናል ። የጦርነት መጨረሻ ጦርነት ሆኖ አያውቅም ። አንድ ቀን ልንነጋገር ወጣት መርገፉ ልብ ይሰብራል ። ነጋ ሲባል እየጨለመ ፣ ተሻገርን ሲባል ግድግዳ እየሆነ ይኸው እስከ ዛሬ አለን ።

ለመጣ ሁሉ ጨፍረናል ። እገሌን የነካብኝ ይወጋ ብለን ረግመናል ። ጣልያን ሲመጣ በየካ ሚካኤል በኩል አንዳንድ ሰዎች ከበሮ ይዘው ወጥተው ተቀብለዋል ። የጦሩ መሪ አማኑኤል ይባላል። እንዲህ ተብሎ ተዘመረለት፡-

“አየነው ሁሉንም አየነው
አማኑኤል ቸር ነው ።”

ሥርዓቶች በተለዋወጡ ቍጥር በጭፈራ እንጀምራለን ፣ በማያልቅ ኀዘን እንፈጽማለን ። ዛላው ወጣት ፣ ይዳራል ፣ ይኳላል ሲባል በየጎዳናው ይወድቃል ። ባለፉት 50 ዓመታት ቀባሪ ካገኘው ወጣት ያላገኘው ይበልጣል ። እስከ ዛሬ ጥቁር ልብሳቸውን ያላወለቁ ፣ ላለፉት 50 ዓመታት በዕንባ ዓይናቸውን ያጡ ብዙ አረጋውያን አሉ ። ያለፈው ቍስል ሳይድን አዲስ ቍስል እንጨምርበታለን ። ስምንተኛው ሺህ የገባው ኢትዮጵያ ብቻ እስኪመስል የጦርነት ፣ የበሽታና የስደት ባለ ታሪክ ሆነናል ። አሁንስ ተስፋችን ማነው ? እመጣለሁ እያለ በደጅ ሆኖ የሚለፈልፈው ሰው ይሆን ? ረታለሁ ብሎ የሚታገለው ይሆን ? ከዚህ በኋላ እግዚአብሔርን ተስፋ ካላደረግን የመዳን ዕድላችን ጠባብ ነው ። የምንጠብቀው እግዚአብሔርን ካልሆነ የሚመጣ ንጉሥ የለም ። የሚመጣው ንጉሥ ክርስቶስ ብቻ ነው ። የተጻፈውን ማንበብና መተርጎም ያልቻሉ ፣ ያልተጻፈ እያነበቡ ከንስሐ ያዘገዩናል ፣ በአጉል ተስፋ ይወጥሩናል ። የተሻለ ዘመን ቢመጣም የተሻለ ሕዝብ ካልሆንን ጥቅም የለውም ። ደግሞም የተሻለ ሕዝብ የተሻለ አገርን ያመጣል ። እግዚአብሔር ለመላው ዓለም እንጂ በተለይ ለኢትዮጵያ ብሎ የያዘው ዕቅድ የለም ። እርሱ በምሥጢር ቍጥር የሚገኝ አምላክ ፣ በኅቡዕ ስም የሚታሰስ ጌታ አይደለም ። እርሱ የመርሕ አምላክ ነው ። ስሙ ያህዌ ፣ አዶናይ ፣ ኢየሱስ ፣ አማኑኤል ነው ። መርሁም፡- “እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ ፥ የምድርን በረከት ትበላላችሁ እምቢ ብትሉ ግን ብታምፁም ፥ ሰይፍ ይበላችኋል” የሚል ነው ። (ኢሳ. 1 ፡ 17 ።)

ስለ አገር ስለ ወገን ደግ መስማት የናፈቀው ዐርፍ ዘንድ ጥቂት ተወኝ ብሎ ይለምናል ።

ተስፋችን እግዚአብሔር ብቻ ከሆነ አናፍርም ። የምንጠብቀው ንጉሥ ክርስቶስ ከሆነም በርግጥ ይመጣል ። አሜን !

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ