የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዐርፍ ዘንድ ተወኝ (15)

“ከኃጢአቴ ሁሉ አድነኝ ፥ ለሰነፎችም ስድብ አታድርገኝ።” (መዝ. 38 ፡ 8 ።)

የእግዚአብሔር ሥራ ማዳን ፣ የሰው ሥራ መሳደብ ነው ። ኃጢአተኛውን እግዚአብሔር በምሕረት ዓይን ያየዋል ፣ ሰዎች ደግሞ በጥላቻ ዓይን ያዩታል ። የምሕረት ዓይን ለማትረፍ ይሯሯጣል ፣ የፍርድ ዓይን የወደቀውን ሰው ለመርገጥ ይፈጥናል ። ንብም ሥራ ላይ ናት ፣ ዝንብም ሥራ ላይ ናት ። አንድዋ ድካምዋ ማር ለመሥራት ነው ። የሌላዋ ድካም በሽታ ለማስተላለፍ ነው ። ስድብ በሽታን ማስተላለፍ ነው ። ስንሳደብ በደለኛው ይደነድናል ፣ ስህተት ለመሥራት ያሰቡ ሰዎች መንገዱን ያገኙ ያህል ይነቃቃሉ ። የንጹሐን ልብ ይሰበራል ፣ እግዚአብሔር ያዝናል ። ልጁን ሲሰድቡበት የሚደሰት አባት የለምና ። የእገሌ ስህተት የእገሌን ስድብ ትክክል አያደርገውም ። ንብን የምንወደው ፣ ዝንብን የምንጠላው በተፈጥሮአቸው ሳይሆን በሥራቸው ነው ።

ትጋት ሁሉ ዋጋ አያሰጥም ። የተጋነው ለምንድነው ? የሚለው ሚዛን ላይ ይወጣል ። ሌሊቱን በሙሉ የሚተጉ አሉ ። አንዳንድ አባቶች ለጸሎትና ለማኅሌት ነው ። ሌሎች ለዘፈን ፣ ለስካር ፣ ለዝሙት ፣ ለሌብነት ነው ። ትጋቱ ሳይሆን ለምን እንደ ተጋን ይታያል ። ለስድብ የሚተጉ ብዙዎች ናቸው ። ራሳቸውን እንደ በትር ፣ እንደ እግዚአብሔር ሰይፍ ፣ እንደ ቀጪ አድርገውም መሰየም ይዳዳቸዋል ። ሰው ሲወድቅ ሲያዩ ለማንሣት ሳይሆን ዘመናውያን ነን ባዮች ቪድዮ ለመቅረጽ ፣ ሌሎች ደግሞ ለመሳደብ ይፋጠናሉ ። የሚደንቀው የሰው ውድቀት አይደለም ። ሰው በታሪኩ ሁሉ ውዳቂ ነው ። ማጥፋት ሲችል ያኖረን እግዚአብሔር ግን ከሁሉ በላይ ይደንቀናል ።

የወደቀን ሰው የሚያሳድዱ ራሳቸው የወደቁ ናቸው ። ሰንጋ እንደ ጣሉ “እግዚአብሔር በእጄ ላይ እገሌን ጣለልኝ” በማለት የደስታ ነጋሪት ይጎስማሉ ። እንኳን እግዚአብሔር የመከረው ጨዋ ቤት ያደገም “አየሁ አላየሁም ፣ ሰማሁ አልሰማሁም” የሚል ሸፋኝ ነው ። ደግሞም ሁሉም እንደ መንገዱ ዋጋውን ያገኛልና የእኛ ፈራጅነት ራስን ከማቆሸሽ በቀር አንዳች ፋይዳ የለውም ። በፍርድ ቀን ሁሉም ስለ ራሱ ይጠየቃል እንጂ ማንም ስለማንም አያወራም ። ትዕቢተኛ የሆነ የሃይማኖት ሰው “እኔ በሥራዬ ፣ ሌሎች በምሕረቱ ይዳኙ/ይፈረዱ” ይላል ። ትዕቢተኛ የሆነ ስሑትም የእኔ በደል ከእገሌ በደል ይሻላል እያለ በእግዚአብሔር ምሕረት ፣ በፈሰሰው ደሙ ሳይሆን በማያድን ነገር ይመካል ።

እግዚአብሔር አትማረኝ አይባልም ፣ ክፉ ሰዎችንም አትስደቡኝ አይባሉም ። በድን ባለበት አሞራዎች ይሰበሰባሉ ። የደወቀ ባለበትም ሰነፎች ለስድብ ይኮለኮላሉ ። በሕይወት ውስጥ ትልቁ ቁምነገር ሰዎችን ከቆሻሻ ላይ አንሥቶ ባለ ማዕረግ ማድረግ ነው ። የሰው ሕንፃ እግዚአብሔር የሚያድርበት ነውና አንድን ሰው ማትረፍ ከተማን ከመገንባት ይበልጣል ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው የአገር ግንባታን ፣ የፖለቲካ ፍልስፍናን ለማጠናከር አይደለም ። ሰውን ለማዳን ነው ። ሰው ሲድን የሰው የሆነው ነገር ሁሉ ይድናል ። እግዚአብሔር አድነኝ የሚባል አምላክ ነው ። ማዳን የባሕርይ ግብሩ ነውና ። እግዚአብሔር ሰዎችን ከተበከለ አስተሳሰብ ፣ ከሰይጣን ሽመቃ ፣ ከግዞት ፣ ከፍርሃት ፣ ከቀቢፀ ተስፋ ፣ ከባዶነት ስሜት ፣ ከዘላለም ሞት ፣ ከመቃብር ቍራኝነት ፣ ከአጋንንት እስራት ያድናል ። የትኛውም ነጻ አውጪ እነዚህን ዝግ በሮች መስበር አይችልም ። እግዚአብሔር ብቻ በማዳኑ ትልቅ ነውና ሰንሰለትን ይቆርጣል ። ነጻ አውጪ ተብለው ለተጠሩት ፣ ለሕዝባቸው ለታገሉት ዓለም ትልቅ ክብር ትሰጣለች ። ማርቲን ሉተር ኪንግ ፣ ማኅተማ ጋንዲ ፣ ኔልሰን ማንዴላ እየተባለ በየቀኑ ይነገራል ። ለተግባራቸው እውቅና መሰጠቱ አስፈላጊ ነው ። ዓለም ግን ያዳናትን ፣ ከማያልፈው ጨለማ ያወጣትን ክርስቶስን ረስታለች ።

ማሸማቀቅ የዘመኑ የውጊያ ስልት ሆኗል ። እውነት ሊናገሩ አንደበታቸውን የከፈቱትን ፣ ጉሮሮአቸውን የሳሉትን በቃላት ዘነዘና መትቶ ዝም ማሰኘት ዘመናዊ የውጊያ ስልት ሆኗል ። በዚህ ዘመን በጥይት ከቆሰለው በሰው ምላስ የቆሰለው ይበዛል ። ቅጥረኛ የሆኑ ፣ የራሳቸው ጠብ የሌላቸው አሸማቃቂዎች ተግተው እየጠበቁ ነው ። ሥራ እንዳይሠራ ፣ ወደ ከፍታው እንዳይወጣ ፣ የምሥራች እንዳይነገር ፣ ሰው እንዳያርፍ ተግተው እየሠሩ ነው ። ትጋታችንን የምናውቀው ሰነፎች በሰደቡን መጠን ነው ። ሥራችን በሁሉ ሰው ከተመሰገነ አንድ ችግር አለበት ማለት ነው ።

ነቢዩ ዳዊት፡- “ከኃጢአቴ ሁሉ አድነኝ ፥ ለሰነፎችም ስድብ አታድርገኝ” በማለት ጸለየ ። ከኃጢአት የሚያድን ድል ነሺ ወይም መድኃኒት በዓለም ላይ የለም ። ማዳን የእግዚአብሔር ነው ። የደጁ በር ሲንኳኳ የተዝረከረከውን በቶሎ እናስተካክላለን ። ሌሎች በልባቸው እንኳ እንዳይታዘቡን ጥንቃቄ እናደርጋለን ። ዳዊት እግዚአብሔር ከቆሻሻ ነገር እንዲያጸዳውና ሰነፎችን የስድብ ጠኔ እንዲይዛቸው ለመነ ። የሚገርመው የሚሳደቡት ሰነፎች ናቸው ። ትጉህማ የራሱን ጨርሶ የሌላው ሥራ ይሠራል ፣ የጎረቤቱን ደጅ ያጸዳል ። ሰነፎች ግን ምላሳቸው ከሎሌ በላይ ይታዘዛቸዋል ። ሲያድነን በርግጥም ይህ እግዚአብሔር ነው እንላለን ። ሲሳደቡ በርግጥም ሰነፎች መሆናቸውን እናረጋግጣለን ። የሚሠሩ ሰዎች እንኳን ለነገር ለምግብም ሰዓት ያጥራቸዋል ። ስንፍና የሰውን ኑሮ ያሳያልና ልናስወግደው ይገባል ።

“እደግ እደግ ብለን ያሳደግነው ቀጋ
ዘመም ዘምበል ይላል እኛኑ ሊወጋ።”

ይቀጥላል

#ዲያቆን #አሸናፊ #መኰንን
ኅዳር 8 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ