የመጨረሻው ክፍል
“ወደማልመለስበት ሳልሄድ ዐርፍ ዘንድ ተወኝ ።” (መዝ. 38 ፡ 13 ።)
ወደ ተለያዩ አገራት ለመሄድ የኤምባሲዎችን ደጃፍ ስናንኳኳ እንደምንመለስ ማረጋገጫ ይፈልጋሉ ። የደርሶ መልስ ትኬታችንን ያያሉ ። አገራቸው እንዲጎበኝ እንጂ ሌላ ዜጋ እንዲቀርበት አይፈልጉም ። የሰማይ መንገድ ግን መሄጃ እንጂ መመለሻ የለውም ። የሰማይ መንገድን የጀመረው ምእመን የመሄጃ እንጂ የመመለሻ ትኬት አይቆርጥም ። የሰማይ አገር ከገቡ መውጣት ፣ ካረፉ መንከራተት ፣ ከተደሰቱ ማዘን ፣ ከተወዳጁ መከዳዳት የለበትም ። በምድር ላይ ያፈራነውን ሀብትና ንብረት ጥሎ መሄድ ከባድ ነው ። ይዞ የሄደ ሰውም ፣ ወርቁ የተከተለውን ባለጠጋም አናውቅም ። የድሆች ሆድ ፣ የአገልጋዮች የታረዘ ጀርባ ግን ንብረታችንን ወደ ሰማይ የምንልክበት ነው ። አገር የሚለውጥ ሰው አስቀድሞ ንብረቱን በመርከብ ይልካል ። በመጨረሻ ራሱ ይሄዳል ። ሰማይ ስንደርስ ንብረታችን ቀድሞ ሄዶ ከሆነ ዋጋ እናገኛለን ። ከእኛ በኋላ የሚላከው ንብረት ግን ጥቅም የለውም ። ቆመን የመጸወትነው እንጂ ሞተን የሰጡልን ገንዘባችን ሽልማት አያሰጥም ። በእኛ ቤት ክርስቶስን የምንጋብዘው በድሆች አማካይነት ነው ። ያን ጊዜ በሰማይ አገሩ ክርስቶስ ይጋብዘናል ።
የሞተውን ወገናችንን ስናስብ ዳግም በዚህ ምድር አናገኘውም ። ዳግም በዚህ ምድር ላንገናኝ እንለያያለንና ለምን በምድራዊ ነገር እንፋጃለን ። ነቢዩ ዳዊት ልጁ በታመመ ጊዜ ጽኑ የሆነ ሱባዔ ያዘ ። ደኅና ነው ፣ በርታ ቢሉትም እሺ አላለም ። ያ ልጅ በሞተ ጊዜ ሊነግሩት ፈሩ ። እርሱ ግን በሁኔታቸው የልጁን ሞት ተረድቶ ማቁን ቀደደ ፣ ወርቅ ለበሰ ፤ አመዱን አራገፈ ፣ ዙፋኑ ላይ ነገሠ ። ሲታመም ያዘነው ፣ ሲሞት የበረታው ለምንድነው ? ብለው ግራ ቢገባቸው ዳዊት እንዲህ ሲል መለሰ፡- “ሕፃኑ ሕያው ሳለ፡- እግዚአብሔር ይምረኝ ፥ ሕፃኑም በሕይወት ይኖር እንደ ሆነ ማን ያውቃል ? ብዬ ጾምሁ አለቅሰሁም ። አሁን ግን ሞቶአል የምጾመው ስለ ምንድር ነው ? በውኑ እንግዲህ እመልሰው ዘንድ ይቻለኛልን ? እኔ ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ እርሱ ወደ እኔ አይመለስም አለ ።” (2ሳሙ. 12 ፡ 23 ።)
መቃብር ላይ ቲያትር ከምንሠራ በቁም መጠያየቅ ተገቢ ነው ። ሲሞት በሬ የምናርድለት ድሀ በቁሙ አንድ ዳቦ ያጣ ሊሆን ይችላል ። በሬ ያረድነውም ለራሳችን ክብር ፣ መሰሎቻችን ጋር ለመወዳደር ነው ። እስከ መቼ የሬሳ ሚዜ እንደምንሆን ግራ ያጋባል ። ሲሞት ልብሰተክህኖ ለብሰው የመጡ ካህናት ሲታመም ያልጸለዩለት ፣ ሲባዝን ያላጽናኑት ሊሆኑ ይችላሉ ። ከሞት በኋላ ምንም ልናደርግለት አንችልምና ሰውን በቁሙ መውደድ ፣ መቀበልና ማገዝ ተገቢ ነው ። በቁሙ ለወዳጁ የለፋ ልቅሶው ትንሽ ነው ። ሲቸገር አብረነው የደከምንለት ሲሞት ብዙ አናለቅስለትም ። የሰውነት ድርሻችንን ከተወጣን ሞት የእግዚአብሔር ጥሪ ነው ። ወደማይመለሱበት እየሄዱ ነውና ሰዎችን ማስከፋት አይገባም ። አሁን የምናወራውን ሰው የምናገኘው ለመጨረሻ ጊዜ ሊሆን ይችላል ። ማንም አዝኖብን ሊሞት አይደለም ፣ ወደ እንቅልፍ ሊሄድ አይገባውም ። ጀምበር ሳይጠልቅ የተቋጠረውን ነገር መፍታት ያስፈልጋል ።
ሞት መንገድ ነው ። ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚያደርስ መንገድ ነው ። የፍጡር ሁሉ መንገድ ነው ። ማንም ሰው መቼ መሞቱን አናውቅም እንጂ እንደሚሞት እርግጠኞች ነን ። ሞት መጥፋት አይደለም ። የኑሮ ለውጥ ነው ። ደግሞም ክርስቶስ ትንሣኤና ሕይወት ነው ። ወደማንመለስበት ሳንሄድ ጥቂት ማረፍን እንመኛለን ። ሕይወታችን ከጭንቀት ነጻ ወጥቶ ፣ ቤተሰባችን በሰላም ተባርኮ ፣ ልጆቻችን መልካም ውሳኔ አድርገው ፣ አገራችን በልጽጋ ፣ ቤተ ክርስቲያን ተከብራ ማየት እንመኛለን ። ከዚህ ሁሉ በላይ እውነተኛው የሕይወት ሰንበት ክርስቶስ ነውና በእርሱ ማረፍ ይገባል ። በንስሐ ሸክምን ማራገፍ ፣ በመድኃኒትነቱ መዳን ያስፈልገናል ። እርሱ ራሱ፡- “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ፥ ወደ እኔ ኑ ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና ፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ ፤” ብሏል ። (ማቴ. 11 ፡ 28-29 ።) ደግሞም፡- “ዕረፉ፥ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ” ይላል ። (መዝ. 45 ፡ 10 ።) የጌታ ዕረፍት ኃላፊነት አለበት ። ማረፍ በእምነት ለእግዚአብሔር መንገድ መልቀቅ ነው ። በዚህ ዓለም ላይ ጥቂት ማረፍ ይኖር ይሆናል ። የዘላለም ዕረፍት ግን በሰማይ ነው ።
ነቢዩ ዳዊት እግዚአብሔርን ደጅ ጠና ። ጥቂት ማረፍን ለመነ ። እግዚአብሔርም ስሙንና ዝክሩን ሊያጠፉ በተመኙት ፊት አከበረው ። የዳዊት ጸሎት ላለፉት ሦስት ሺህ ዓመታት በቤተ አይሁድና በቤተ ክርስቲያን ዕለታዊ ምስጋና ነው ። ከዘር ሐረጉም የቀጠለው ሥርዓተ ንግሥ ለአራት መቶ ዓመታት ዘለቀ ። ወልደ እግዚአብሔር ክርስቶስ ወልደ ዳዊት ተብሎ መጣ ። እስራኤል ዛሬም ትልቅ መሪዋ ዳዊት ነው ። ዓርማዋ የዳዊት ኮከብ የሚባለው ነው ። በዓለም ላይ በብዛት ከተሰየሙት ስሞች “ዳዊት” የሚለው ተጠቃሽ ነው ። የዳዊት በገና በየቤቱ ይገኛል ።
የነቢዩ ዳዊትን በረከት ያሳድርብን !
ተፈጸመ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 18 ቀን 2016 ዓ.ም.