“ወደማልመለስበት ሳልሄድ ዐርፍ ዘንድ ተወኝ ።” (መዝ. 38፡13) ።
የቅዱስ ዳዊት ትግሎች ብዙ ነበሩ ።
4- በልጆች የተፈተነ ነበር
ልጆች እንደ አባት አይሆኑም ። ነጻ ፈቃድ ያላቸው ናቸውና እንደ ራሳቸው ናቸው ። ልጆች የአባትን አርአያ ይከተላሉ ። ዳዊት ብዙ ሚስቶችን አገባ ፣ ልጁ ሰሎሞን ሺህ ሚስቶች አገባ፤ ዳዊት እንደ ወንድሙ ያለውን ኦርዮንን አስገደለ ፣ ልጁ አቤሴሎም ወንድሙ አምኖንን ገደለ ። ልጆች እንደ ራሳቸው ናቸው ፣ መልካም ነገርን በሚመለከት ግን ላይከተሉ ይችላሉ ። ክፉ ነገርን ግን በግድ ይከተላሉ ። ዳዊት በሕይወቱ የዘራውን ማጨድ ያደከመው ሰው ነበረ ።
ቅዱስ ዳዊት በልጆቹ ሕይወት የተጎዳ ነበር ። ልጆቹ በሥነ ምግባር ውድቀት ፣ እርስ በርስ በመጋደል ፣ ወገን በመለየት ይፈተኑ ነበር ። እርሱ የእስራኤል ንጉሥ የሕግ አስከባሪ ነው ። በአገር ላይ ሊያየው የሚፈልገውን ሥነ ምግባር ከቤቱ አጥቶት ነበር ። አገር ተገዝቶለት ቤቱ ሸፍቶበት ፣ ሠራዊት እሺ ብሎት ልጆቹ አምጸውበት ነበር ። ሕዝቡ ዛሬስ ምን ይፈርድ ይሆን አላለውም ። ዳዊት ልቡን የሚረዳውና የሚያውቀው ሕዝብ ነበረው ። እርሱ ግን ቤቱ ከድቶት አገር ልግዛ ሲል ማፈር ይተናነቀው ይሆናል ። ልጆች እርስ በርስ ሲጋደሉ ከማየት የበለጠ ቅጣት የለም ። “የገደለው ባልሽ ፣ የሞተው ወንድምሽ ፤ ኀዘንሽ ቅጣ አጣ ከቤትሽ ልወጣ” የተባለው በዳዊት ላይ ደረሰ ። ከብዙ ሚስቶች ልጆች ሲወለዱ የአባቴ ልጅ ፣ የእናቴ ልጅ የሚል የባዕድነት ስሜት ያመጣሉ ። አቤሴሎም ለእኅቱ ትዕማር ሲቆጭ ፣ አምኖን ደግሞ የአባቴ ልጅ በማለት አቃለላት ። በቁምም በሞትም የአባቴና የእናቴ ልጅ እንደ ማለት የሚያስቀይም ነገር የለም ። ዳዊት ይህ ሁሉ ጦርነት ይካሄድ የነበረው በቤቱ ነበር ። የሚያየውን አላይም ፣ የሚሰማውን አልሰማም ማለት አይችልም ። ትልቅ ቤት ጉዱም ትልቅ ነውና ይህ በዳዊት ላይ ደረሰ ።
ልጅን መፍራት ከባድ ነው ። ቀጥሎ ምን ይሆን ? እያሉ መጠበቅ አስጨናቂ ነው ። ዳዊት ብዙ ኃላፊነት ቢኖረውም ልጆቹ እርስ በርስ የሚጣሉ ፣ ከጠላት ጋር የሚሻረኩ ፣ የራሳቸውን ክብር የጣሉ ነበሩ ። አዳም አቤልን ወልዶ ፣ ዳዊት አምኖንን መውለዱ የሚገርም ነው ። ኃጢአተኛው አዳም ጻድቁ አቤልን ፣ ጻድቁ ዳዊት መረን አምኖንን ወለደ ። ዳዊት ኦርዮንን ሲያስገድል ኃጢአቱን ለመደበቅ አስቦ ነበር ። በቆሻሻ ልብስ ላይ ሽቱ ማርከፍከፍ ክፉ ጠረኑን ማባስ ነው ። ኃጢአት በንስሐ እንጂ በሌላ ኃጢአት አይሸፈንም ። ዳዊትን ያጸናው የመጣው ነገር ይገባኛል ፣ በኃጢአቴ የመጣ ነው ብሎ በማመኑ ነበር ። ኃጢአት በመነሻው ትንሽ ነው ። ኃጢአት ትልቅ የሚሆነው ራሱን በሌላ ስህተት ለመሸፈን በሚያደርገው ጥረት ነው ።
ደግ አባት ፣ ልጆቹን የሚወድድ በቁሙም በሞቱም የሚፈራው የልጆቹን ሰላም ማጣት ነው ። አቤሴሎም አባቱን ዳዊት ከዙፋን አባሮታል ። ዳዊት ከዚህ በኋላ በምንም ላለመደነቅ የወሰነበት ክስተት ነው ። የገዛ ልጄ እንዲህ ካደረገኝ ከማንም ምንም አልጠብቅም ያለበት የሕይወት ልምድ ነው ። አቤሴሎም መድረክ ሠርቶ በአደባባይ የአባቱን ቁባቶች አስነወረ ። ዳዊት ያልሆነው ምን ነገር አለ ? (2ሳሙ. 16፡11) አኪጦፌል የዳዊት አማካሪ ነበር ። ዳዊትን እየደለለ ፣ አቤሴሎምን ደግሞ አባትህን ገልብጠው ይለው ነበር ። ሁለት ገጽ ያለው አኪጦፌል ላመነው ዳዊት ያልታመነ ሰው ነበር ። ሳይጎድልበት አባትና ልጅን አጣላ ። አገር አፈረሰ ። አቤሴሎም ላይነግሥ ዳዊት ኮበለለ ። “ሳይቸግር ጨው ብድር” እንዲሉ ነው ። ዳዊት በስንቱ ተጎዳ ፣ በስደቱ የተናቁ ሰዎች ትቢያ እየበተኑ ሲሰድቡት አልተከፋም ። አባትን በልጅ ላይ ጠላት አድርጎ የሚያስነሣ ጨካኝ ሰው ነው ። ተማሪን በመምህሩ ላይ የሚያዘምት የክፉዎች አውራ ነው ።
ራስ አዳል ልጃቸው መርዝ ጨምሮ ምግብ ሰጣቸው ይባላል ። ታማሚው አባትም እንዲህ ብለው ገጠሙ፡-
አለህም እንዳልል እንዲህ ይደረጋል ፣
የለህም እንዳልል ይመሻል ይነጋል ፤
ልጄ እንዴት ባባቱ መድኃኒት ይምሳል!?
ዳዊት በገናውን ይዞ ይህን የኀዘን እንጉርጉሮ ቢመታው በእውነት ይገልጠው ነበር ። ባለ ቅኔው ሐሰትና እውነት ፣ ትዕቢትና ትሕትና የሚያፈልቀው ፣ ሞቱን የረሳው የሰው ልጅ ቢገጥመው፡-
ጸላእኩ ሰብአ እምነ ርእስየ ፣ ሰውን ጠላሁት ከራሴ ጀምሮ ብሏል ። ቅዱስ ዳዊት ብዙ የዋሻ መንገዶችን ሄዷል ። ማንንም አልነካም ማለት ውጤታማ አያደርግም ። ሰዎች እኛን የመንካት ጥማት ሊኖራቸው ይችላል ። ልብን ማስፋት ግን ከመሰበር ይጠብቃል ።
ብዙ ሰው ቤተሰቡ ሰላም በማጣቱ ይታወካል ። አባትና እናቱን ለማስታረቅ ሽቅብ ቁልቁል የሚል ልጅ አለ ። እኅትና ወንድሞቹን ለማግባባት ሞክሮ ያልተሳካለት ፣ ከመሐል ላይ ሆኖ ከሁለት ወገን እሳት የሚነድበት አያሌ ነው ። ቤት የሸፈነው ጉድ ብዙ ነው ። አደባባይ እውነት የተደበቀበት ነው ። የሰው ሐቅ ያለው ቤቱ ነው ። በዚህ ሁሉ የዋሻ መንገድ እግዚአብሔር ቀና ያደርጋል ። አንዳንዴ ሰዎቹን በመለወጥ ይረዳናል ። ሌላ ጊዜ ደግሞ እኛን በመለወጥ ያድነናል ። አዎ ሰዎቹ ካልተለወጡ እኛ መለወጥ ግዳችን ነው ። ታዲያ ዳዊት “ዐርፍ ዘንድ ተወኝ” ቢል እውነቱን ነው!
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 12 ቀን 2016 ዓ.ም.