“ወደማልመለስበት ሳልሄድ ዐርፍ ዘንድ ተወኝ ።” (መዝ. 38፡13) ።
ነቢዩ ዳዊት ልጁ አቤሴሎም ባሳደደው ጊዜ፡- “አቤቱ ፥ የሚያስጨንቁኝ ምንኛ በዙ ! በኔ ላይ የሚቆሙት ብዙ ናቸው” በማለት ወደ እግዚአብሔር ጩኸቱን አሰምቷል ። (መዝ. 3 ፡ 1) ። በአጭር ዕድሜው ብዙ ጭንቀት ፣ በተሰፈረ ዘመኑ ያልተሰፈረ ጠላት በማስተናገዱ እንዲህ አለ ። ንጉሡ ዳዊት አደባባዩን ለመሸሽ ቤት የለው ፣ ቤቱን ለመሸሽ አደባባዩ በእነ አኪጦፌል የተሞላ ነበር ። አገራዊ ግጥማችን በዳዊት ላይ የደረሰበት ይመስላል፡-
እከክ ብቻ ሁኗል እግሬን ብዳብሰው ፣
እንዴት መቀመጫ መሄጃ ያጣል ሰው ፤
ደግሞም፡-
እሾህ ብቻ ሆነ እግሬን ብዳብሰው ፣
እንዴት መራመጃ መሄጃ ያጣል ሰው !?
ማኩረፊያ ያጣው ዳዊት ፣ በር ሲንኳኳ እየደነገጠ ፣ የልጆቼን ክፉ ልሰማ ነው ወይ ? ብሎ እየፈራ የሚኖር ሆነ ፤ የአደባባዩ ጀግና በትንሽ ልጅ እያነሰ የሚኖር ነበር ። አገሩንም ሲጎበኝ በሚያየው ያዝን ነበር ። ነገር ግን ወደ “እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ” በማለት ተናገረ ። (መዝ. 121 ፡ 1) ። ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ሲባል የሚከፋው ፣ ነገር ግን ቤተ መንግሥት ለመሄድ የጋባዥ ያለ የሚለው አያሌ ሰው ነው ። ቤተ መንግሥት የነበረው ዳዊት ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉት ጊዜ ደስ ይለው ነበረ ። መንፈሳዊ ስሜቱን ሳይደብቅ የሚናገር ንጉሥ ዳዊት ብቻ ይመስላል ። ቤተ መንግሥት የማይገኘው ደስታ እግዚአብሔር ቤት ይገኛል ። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አዝማደ መንግሥቱን ይዘው ፣ ሚኒስትሮችን አስከትለው ወደ እግዚአብሔር ቤት ሲሄዱ ልዩ ውበት ነበረው ። ከእርሳቸው በኋላ የተነሡት ቤተ እግዚአብሔርን የሚዘጉ ፣ ቤተ ክርስቲያንን ሙዝየም እናድርግ እያሉ የሚገዳደሩ ሆኑ ። ነቢዩ ዳዊት መንፈሳዊ ጓደኞች ነበሩት ። ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ብለው በቤተ መንግሥቱ ደጃፍ ቆመው በር ያንኳኩ ነበር ። የነገሥታት መንፈሳዊ ጓደኞች ወደ መልካም ነገር ይመራሉ ። ንጉሡ ወደ መልካም ነገር ሲሄድ አገርም ወደ መልካም ግብ ትጓዛለች ።
የእግዚአብሔር ቤት ከባሕሩ ዓለም እግራችን መርገጫ የሚያገኝበት ደሴት ነው ። ማዕበሉን የምናሳልፍበት ፣ እፎይ ብለን እንደገና ጉዞ የምንጀምርበት መካነ ሰላም ነው ። ነቢዩ ዳዊት “ዐርፍ ዘንድ ተወኝ” ባለበት ምዕራፍ ብዙ ነገሮችን አንሥቷል ። ይህን በየቍጥሩ እናያለን ፡-
“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ አልሁ።” (መዝ. 38 ፡ 1) ።
አንደበት በመንገድ ይመሰላል ። ስለዚህ “እገሌ በአፉ ይስታል” ይባላል ። “እገሌ ሲናገር ድንቅፍ አይለውም” ይላሉ ። “እገሌ ፍሰቱን የጠበቀ ንግግር ይናገራል ።” “እገሌ ንግግር ያረዝማል ፣ ለመጠቅለል ሠላሳ ደቂቃ ይፈጅበታል” ይባላል ። ይህ ሁሉ ዘይቤ አንደበት በመንገድ ተመስሎ ሲነገር ነው። የምንጓዘው ወደ ተናገርነው ነው ። “ወልደው ሳያበቁ ፣ በሰው ልጅ አይስቁ” ይባላል ። ሳቅ ስላቅ መናገር የነገ ትውልድን ሊበድል ይችላል ። ምላስ ብዙ ተናግሮ አንድ ቀን ተመትቶ አያውቅም ። ምላስ በተናገረ ሌላው አካል ሲመታ ይኖራል ። በምላሳችንም ለትውልድ መከራ እናመጣለን ። በንቀት ንግግር ትውልድ ዋጋ ይከፍላል ። በግጥም ፣ በሙሾ ፣ በፉከራ ፣ በሰርግ ዘፈን የምንጥላቸው ቃላት ብርቱ ስቃይ ያመጣሉ ። እኛ እየደከምን ስንመጣ የናቅነው ግን ወደ ክብር ለመድረስ ሲታገል ያድራል ፣ ያን ቀን የንቀትን ዋጋ ያስከፍለናል ። “ሰውን እግሩን ስትረግጠው ክንፍ አበጀህለት” በማለት ካህሊል ጅብራን ተናግሯል ።
“አትፍረዱ” የተባለው ፍርድ የአንደበት ኃጢአት ስለሆነ ነው ። የፈረድነውን መሆናችን አይቀርም ። በሰው ኃጢአት ሲፈርድ የሚውል በዚያ ነገር መፈተን ይጀምራል ። እንደውም አንድን ነገር ደጋግመው የሚያወሩ ያንን ለመሸመት እያሰቡ ነው ። ቤት የሚገዛ ሰው ስለ ቤት ብቻ ያወራል ። መኪና የሚገዛም እንዲሁ ነው ። ስለ አንድ ኃጢአት ደጋግሞ የሚያወራም በዚያ ኃጢአት ይያዛል ። ስንፈርድ ደግፎን የነበረው የእግዚአብሔር እጅ ይነሣል ። ያን ጊዜ ሰዎቹ ከሆኑት በላይ ጭቃ ውስጥ እንለወሳለን ። “ፐ” የሚለው የግነት ምላሽ መፍረድ ነው ። “አቤት ይቅር ይበለን ፣ በእነርሱ የደረሰ ውርደት በእኛ አይድረስ” የሚለው ንግግር ፍርድን መንፈሳዊ ለዛ ለመስጠት የሚደረግ ሙከራ ነው ። ስንፈርድ ማድረግ የሚገባንን ነገር አናደርገውም ። የወሬ ማጣፈጫ ፣ የመጽናኛ ርእስ እናደርገዋለን ። የወደቀ ሰው ስናይ መወዳጀት ፣ እንዲነሣ መርዳት ፣ ከሰው አፍ መሰወር ይገባናል ። መፍረድ ግን ይህን ሁሉ ግዳጅ እንዳንወጣ ያደርገናል ። “እንዴት እርሱ ይህን ያደርጋል” የሚለው በሰዎች የመገረም ንግግር ፍርድ ነው ። በዚህ ዘመን እንኳን በአንደበት የፈረዱት ፣ በልብ የታዘቡት ይደርሳል ።
አዎ የምንጓዘው ወደ ተናገርነው ነው ። ስለዚህ ነቢዩ የነገ መንገዴን እንዳላበላሽ አንደበቴን እጠብቃለሁ አለ ። ያውም የንጉሥ ንግግር ተግባር የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው ። በአንድ ቃል አገር የሚያረጋ ፣ በአንድ ቃል አገር የሚያፈርስ ነውና ንጉሥ ዳዊት አንደበቴን እጠብቃለሁ አለ ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም.