የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዐርፍ ዘንድ ተወኝ (7)

“ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ አልሁ ።” (መዝ. 38 ፡ 1 )።

በዚህ ዘመን ከፍተኛ ገንዘብ የሚወጣው ለጥበቃ ነው ። አገሮች ፣ ቤቶች ፣ ግለሰቦች ይጠበቃሉ ። የሰለጠኑ ጠባቂዎች በመላው ዓለም እየፈሉ ነው ። በአገራችንም ሰዎችና ንብረቶች ጥበቃ ይደረግላቸዋል ። ጥበቃው ከደኅንነት ካሜራዎች ፣ በሰለጠኑ ውሾች ጭምር ይከናወናል ። አንዳንድ ለጥበቃ የሚውሉ ውሾች በመቶ ሺህዎች ዶላር ወጪ ይደረግባቸዋል ። የተለያዩ የጥበቃ ኤጀንሲዎች በየጊዜው የሥራ አድማሳቸውን ያሰፋሉ ። እነዚህ ሁሉ ጠባቂዎች አራዊትን የሚከላከሉ አይደሉም ፣ ሰው ሰውን የሚከላከልበት መሆኑ ያሳዝናል ። ከክፉ ሰው የሚጠብቁን ሌሎች ሰዎች መሆናቸው ደግሞ ሁሉ ጠላት አለመሆኑን ያሳያል ። ይህ ብቻ አይደለም ማን መሆኑን ከማናውቀው ጠላት በየቀኑ እንዲጠብቁን እንከፍላለን ። ሰው ጠላቱን እንኳ ለማወቅ ይቸገራል ። እነዚህ ሁሉ ጠባቂዎች እውነተኛውን ጠላት ሰይጣንን የሚከላከሉ አይደሉም ። የማይታየውን ጠላት የመመለስ አቅም የላቸውም ። አሁንም ሌላ የሚያስደንቀው ነገር ይህ ሁሉ ጥበቃ እየተከናወነ ወንጀል ሊወገድ አለመቻሉ ነው ። ቅጣቶች ወይም የጥበቃ ጓዶች ሰውን መቀደስ አይችሉም ። ስለዚህ ባላቸውን የሚጠብቁ ሚስቶች ፣ ሚስታቸው ላይ ሰላይ የሚልኩ ወንዶች አርፈው ቢቀመጡ መልካም ነው ። ሰው አገሩን ፣ ንብረቱን ፣ ራሱን ለመጠበቅ ጠባቂ ያኖራል ። ነቢዩ ዳዊት ግን “ለአፌ ጠባቂ አኖራለሁ” ይላል ።

እያለ ያለው ሁልጊዜ አልናገርም አይደለም ። ኃጢአተኛ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ ይላል ። መንግሥታት ፣ ባለጠጎች ፣ ግለሰቦች ሊያቆሙት የሚገባው ጥበቃ ከንብረት ይልቅ አንደበታቸው ላይ ነው ። አንደበት የሚያፈርሰውን ያህል ጠላት ሊያፈርስ አይችልም ። ጠላት እንደውም የማስተሳሰር አቅም አለው ። የተለያዩ ሕዝቦች አንድ የሚሆኑት ጠላት ሲመጣ ነው ። ጠላት ባለውለታ የሚሆንበት ጊዜ አለ ። ጠላት “በተቃወመኝ ጊዜ” ይላል ። “ጊዜ” የሚለው ዘላለማዊ ጠላት ፣ ቋሚ ተቃውሞ እንደማይኖር ያሳያል ። ትላንት የሚቃወሙን ዛሬ የዓላማችን ተባባሪ ሆነዋል ። የሁልጊዜ ጠላት ፣ የሁልጊዜም ወዳጅ የለም ። ቀኖች የሚለዋወጡት ብቻቸውን አይደለም ፣ ሰውን ይዘው ነው ። መንፈሳዊ ሰው ግን በቀኑ ላይ ይኖራል እንጂ ቀኑ አይኖርበትም ። ራስን መግዛት ማለት ራስን መቆጠጠር ማለት ነው ። ራስን መግዛት በትልቁ የሚለካው አንደበት ላይ የበላይ በመሆን ነው ። አስቦ መናገር ካልተቻለ ፣ ተናግሮ ማሰብ ይመጣል ። ያ ደግሞ ጭንቀትን ይወልዳል ።

ዛሬ ሰዎች ያላቸው ግጭት ቦምብ ተወራውረው ፣ ጥይት ተተኳኩሰው አይደለም ። በክፉ ንግግር ተጎዳድተው ነው ። አንደበት ትንሽ የምትመስል ግን ትልቅ ጥፋት የምትሠራ ናት ። የኒውክለር ቁልፍ ትንሽ ናት ፣ ግን ዓለምን ልታጠፋ ትችላለች ። አንደበት በማነስዋ አትናቅም ። አንድ ስፖርተኛ እጁ ላይ ቆልመም ያለ ነገር ነበረው ። ግን ጎበዝ ተጫዋች ነው ። አሰልጣኙ “እኛ የአካል ጉዳተኛ ጣቢያ አይደለንም” የሚል ምጸትና ሞራል ነኪ ንግግር ተናገረው ። ያ ጎበዝ ወጣት በዚያው ደቂቃ ገብቶ ራሱን አጠፋ ። አንደበት ስንቱን እንደ ቀጨና ከሕይወት እንዳፈናቀለ የፈጠረው ጌታ ይቍጠረው ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 20 ቀን 2016 ዓ.ም.

ያጋሩ

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።