የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዐርፍ ዘንድ ተወኝ (8)

“ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ አልሁ ።” (መዝ. 38 ፡ 1 )።

ንጉሥ ዳዊት ጥበቃ ማለት ምን ማለት መሆኑን ድሮ በአርበኝነት ዘመኑ ፣ አሁን በንግሥናው ክብሩ ያውቀዋል ። በአርበኝነት ዘመኑ ለሕይወቱ ይጠበቃል ፣ አሁን ለክብሩ ይጠበቃል ። ሰዎች ተጋፍተው እንዳይጨብጡትም ጥበቃዎቹ ይከለክላሉ ። ሰው መጠበቅ ያለበት ከሰዎች ጥቃት ብቻ ሳይሆን ከውዳሴ ከንቱም ነው ። ለቤታቸው ጥበቃ ያላቸው አፋቸው ግን ጥበቃ የሌለው ሰዎች ይህን መዝሙር ቢጸልዩ መልካም ነው ። ለሱሪ ቀበቶ ፣ ለቀሚስ መቀነት ያደረጉ ሰዎች ለአፋቸው ጠባቂ ማድረግ አለባቸው ። መኪና ፍሬን ባይኖረው ከመድረስ ይልቅ መንገድ መቅረት ዕጣው ይሆን ነበር ፣ መንገድ መቅረትም መልካም ነው ፤ አደጋም ያስከትላል ። ፍሪሲዮን የሌላቸው መኪናዎች መጥተዋል ፣ ፍሬን የሌለው መኪና ግን የለም ። ለመኪና ፍሬን ካለ ፣ ለአንደበት መቆጣጠሪያ ያስፈልገዋል ። ቆጥረው የማይናገሩ ሰዎች ይፈርሳሉ ፣ ያፈርሳሉ ። መቼም የፈረሰ ነው የሚያፈርሰው ። ሠራዊቱ ሁሉ የዳዊትን አንደበት መጠበቅ አይችልም ። ዳዊት ግን ራሱ አንደበቱን ይጠብቃል ። አንደበት የባለቤቱ ኃላፊነት ነው ።

ሰው አንደበት የሚጠበቀው እንዴት ነው ? ብሎ ሊያስብ ይችላል ። አፍ ጸሎት ከያዘ አንደበት መናገር አይችልም ። ጸሎት የሚያበዙ ወሬ ይቀንሳሉ ። አንደበትን ለመጠበቅ የሚናገሩበትንና ዝም የሚሉበትን ቦታ ማወቅ ያስፈልጋል ። አንደበትን ለመመቆጣጠር ኃይለ መንፈስ ቅዱስን መለመን ያሻል ።

አፍ ያለው ካፋፍ ነው ፣
ላዩም ታቹም ገደል።

መንገድ አላሳልፍ የሚል ኃጢአተኛ ነው ። እስራኤል ወደ ከነዓን ጉዞ በጀመሩ ጊዜ መንገድ አልሰጥ ብሎ እንቢ አለ ። በዚህ ምክንያት የአማሌቅ ዝክር እንዲደመሰስ ታወጀ (ዘጸ. 17 ፡ 14) ። የሰውን ተስፋ ማጨለም ፣ ግቡ ላይ እንቅፋት መሆን ፣ ዓላማውን ማኮላሸት ፣ አካላዊ ሥነ ልቡናዊ ጫናዎች ማሳደር ፣ ማሸበር ፣ በያዘው በጎ ነገር ግራ እንዲጋባ ማድረግ ፣ አድማ ማሥነሣት ትልቅ ኃጢአተኝነት ነው ። ኃጢአተኛ ዓላማ የለሽ ነው ። ትልቁ ኃጢአት ሌሎችንም ከዓላማ ማስቀረት ነው ። “እኛም አንገባ ፣ ሰውም አናስገባ” ማለት ትልቅ በደል ነው ። ስም ማጥፋት ፣ ማውገዝ ፣ ማኮሰስ ትልቅ ኃጢአት ነው ። እግዚአብሔርን እኔም አልበጅህም ፣ እገሌም ሊበጅህ አይገባውም ብሎ በእርሱ ላይ ጠላት ማብዛት ነው ። ለሰው መሰናክል መሆን የበደል በደል ነው ።

መቃወም ጽድቅ የሚመስላቸው ብዙ ሰዎች ናቸው ። መቃወም የሐቀኝነት ምልክት ተደርጎ በመታሰቡ ዝም ብለው የሚቃወሙ ሰዎች አሉ ። ሥሩ ተብለው ቢሰጣቸው ግራ የሚጋቡ ለመቃወም ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተቀቡ የሚናገሩ አይታጡም ። ሰዎች የራሳቸውን የሕሊና ወቀሳ ለማምለጥ የሌሎችን ስህተት ሊያወሩ ይችላሉ ። እኔ ብቻ አይደለሁም እገሌም ስቷል በማለት ለመጽናናት ይሞክራሉ ። የሚያጽናናው ግን የክርስቶስ ምሕረት እንጂ የሌሎች በደል አይደለም ።

ነቢዩ ዳዊት ወይም ንጉሥ ዳዊት ተቃዋሚዎች ነበሩት ። “ንጉሥ በግንቡም ሳይታማ አይውልም” እንዲሉ ። ንጉሥ ዳዊት በጦር ኃይሉ ማጥፋት ሲችል ክፉ እንኳ እንዳይናገራቸው ይጨነቅ ነበር ። እነዚያ ተቃዋሚዎች ስህተትን የሚያጎሉበት ፣ የሌለውን በደል በልበ ወለድ የሚጽፉበት ነበሩ ። ለእነዚህ ሰዎች መልስ መስጠት ደምን በደም ለማጥራት መሞከር ነው ። ሁለተኛ ሰምቻችኋለሁ እንደ ማለት ነው ። ሦስተኛ የባለጌ ክብሩ መልስ ማግኘቱ ነው ። አራተኛ ትልቅ ዱላ ዝምታ ነው። አምስተኛ እኛ ስንናገር እግዚአብሔር ዝም ይላል ። ደግሞም ተቃዋሚዎች ብዙ ናቸው ። ለሁሉ መልስ መስጠት ቆሞ መቅረት ነው ። የእነርሱ መደበኛ ሥራ መቃወም ነው ። ሥራችሁን ሠራችሁ ብለን መውቀስ አይገባንም ። የእኛ መደበኛ ተግባር ግን ሌላ ነው ። “ዶሮ ባልበላውም ጭሬ ልበትነው” አለች ይባላል ። ለእኛ ካልሆነ ለማንም አይሁን የሚል እሳቤ እየበዛ ነው ። “ይህን ሁሉ እየተባልህ እንዴት መልስ አትሰጥም?” የሚሉ ተቆርቋሪ ሰዎች ይኖራሉ ። ወዳጅ ለወዳጁ አምባሳደር ነው ። ስለ ወዳጁ መመስከር ይገባው ነበር ። ያልደረሰበት መላ ለማቅረብ አይቸገርም ። ነቢዩ ለአፉ ጠባቂ ነበረው ። ሠራዊቱን አፌን ጠብቁልኝ ማለት አይችልም ። አንደበት በባለቤቱ የሚጠበቅ ነውና ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 21 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ