የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዐርፍ ዘንድ ተወኝ (9)

“ከዝምታ የተነሣ እንደ ዲዳ ሆንሁ፥ ለበጎ እንኳ ዝም አልሁ፥ ቍስሌም ታደሰብኝ ። ልቤም በውስጤ ሞቀብኝ ከማሰቤም የተነሣ እሳት ነደደ፥ በአንደበቴም ተናገርሁ ።” መዝ. 38፡2-3 ።

“ጨርሰህ ብላ እንጂ ጨርሰህ አትናገር” ይባላል ። ደግሞም፡- “ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል” ይላሉ ። ወላጆች፡- “ሆድ ብዙ ቆሻሻ ነገር እንኳ ተሸክሟልና ምሥጢርን መቋጠር ፣ የሰውን ገመና መደበቅ ልመዱ” እያሉ ይመክራሉ ። ጨርሶ መናገር አብሮ ለመቀጠልም ለመለያየትም አይሆንም ። ብንቀጥል ፍቅር ፣ ብንለያይ ትዝታ ይሆናልና ጨርሶ ከመናገር መቆጠብ ያስፈልጋል ። ሁሉም ነገር ኢኮኖሚ በሆነበት በእኛ ዘመን ንግግር ኢኮኖሚ አለመሆኑ ይገርማል ። ቆጥቦ መናገር የሰውነት ክብር ነው ። ሰው አእምሮው ትክክለኛ ነው የሚባለው ቆጥቦ መናገር ሲችል ነው ። ብዙ ሰው ልብስ ለብሷል ፣ ግን ሁሉን ያወራል ። ልብስ የለበሰው የሚደበቅ ነገር ስላለው ነው ። ቤት የሠራው የራሱን ነገር መሸፈን ስለሚፈልግ ነው ። ቤት አደባባይ ፣ አደባባይም ቤት መሆን የለበትም ። ሁሉም ነገር ውበት የሚኖረው በመልኩ ሲቀመጥ ነው ።

የመጨረሻው ዘመን ትልቅ ፈተና አንደበት ነው ። ስለ ሐሳዊ መሢሕ በተነገረበት አንቀጽ፡- “ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፥ በአርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው። እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ” ይላል ። (ራእ. 13 ፡ 5-6 ።) የስድብ አፍ የመጨረሻው ዘመን መገለጫ ነው ። የአውሬው መንፈስ እንደ ገነነ ምልክቱ የስድብ አፍ ሲከፈት ነው ። አውሬው በስድብ አፍ የከበሩትን ማዋረድ ይፈልጋል ። የከበረን ማዋረድ አይቻልም ። የከበረን ማዋረድ ለመዋረድ ነው። ሁለተኛው በነገድ በቋንቋ መካከል መለያየትን ይዘራል ። እነዚህ ምልክቶች በዚህ ዘመን እየታዩ ነው ። የከበሩትን ሲያዋርዱ የሚውሉ ትንሽነት የሚሰማቸው ሰዎች እየበዙ ነው ። ደግሞም ዘረኝነትን እንደ ቀላል የሚያወሩ ፣ ድልድይ ከመዘርጋት ግንብ ሲገነቡ የሚውሉ ብዙ የአውሬው ቅጥረኞችን እያየን እየሰማን ነው ።

ነቢዩ ዱዳ እስኪመስል ድረስ ዝም ብሎ ነበር ። በዝምታ አቅምን ማጠናከር ይቻላል ። የሰውነት አቅም ከሚባክንባቸው በሮች አንዱ አንደበት ነው ። ስንናገር ብዙ ኃይል እናባክናለን ። ያለንበትን አድራሻ ለጠላት እናሳውቃለን ። ልባችንን አደባባይ እናደርገዋለን ። መከራን ወደ ሕይወታችን እንጋብዛለን ። የፈረድንባቸውን ሰዎች ጾር ወይም ፈተና ወደ ራሳችን እንጠራለን ። ለጠላት ፍላጻ ተላልፈን እንሰጣለን ። ዝም ስንል ግን ውስጣችንን ማዳመጥ እንችላለን ። ለእግዚአብሔር አገልጋይነት እንታጫለን ። መንግሥት እንኳ ለጥብቅ ሥራ የሚፈልገው ምሥጢር የሚውልለት የሚያድርለትን ሰው ነው ። ዘርዛራ ወንፌት የሆነ ፣ ለማን ልናገር ላብድ ነው ለሚል ሰው ምሥጢር አይነገርም ። የእግዚአብሔር ሰው ለመናገር ቦታን ፣ ጊዜን ፣ ሰውን መለየት አለበት ። ዝምታ አያጸጽትም ። ቅዱስ አርሳዮስ፡- “ብዙ ጊዜ በመናገሬ ተጸጽቻለሁ ፣ በዝምታ ውስጥ ግን ተጸጽቼ አላውቅም” ብሏል ።

ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ ፍኖተ አእምሮ (የዕውቀት ጎዳና) በተሰኘ መጽሐፋቸው፡- “ከመናገር ከሚሠራው ጽድቅና በዝምታ ከሚሠራው ጽድቅሳ ማናቸው ይበልጣል ። ሁለት እጅ የሚሆነው የአንደበታችን ኃጢአት ግን ሐሰት ፣ ሐሜት ፣ ፅርፈት ፣ ሙግት ፣ ቧልት ፣ የዘፈን ጨዋታ የስንፍና ተረት ፣ የክርክር ድፍረት ይህን ፰ቱን ኃጢአት እንሠራበታለንና ስለዚህ መጻሕፍተ ጥበብ ዝምታ ወርቅ ነው መናገር ብር ነው ሲሉ የጥቅማቸውን መበላለጥ ነግረውናል ። በዚህ ዓለም ኑሮ ቢሆን የነገር አራቃቂዎች ይደኸዩበታል ፣ የሥራ አራቃቂዎች ይከብሩበታልና ዝም እንበል” ይላሉ ። (ገጽ 204 ) ።

ዝምታ ብዙ ዓይነት ነው ። አርምሞ የሚባል የዝምታ ኑሮ አለ ። ጸጥታ የሚባል የጨዋነት መገለጫ አለ ። እውቀት በማጣት የሚናገረው አጥቶም ዝም የሚል አለ ። የደበቀው ምሥጢር እንዳይወጣበት ፣ ብዙ ከመናገር የተነሣ እንዳይሳሳት የሚሞክር የብልጥ መለጎም አለ ። “ጅብ እስኪነክስ ያነክስ” እንዲሉ የራሱ እስኪያደርግ ድረስ ለማታለል ዝም የሚል የቀበሮ ባሕታዊ አለ ። ጊዜ እስኪያልፍ ብሎ ለቅሶውን ውጦ ዝም የሚል አለ ። ራስ ጉግሣ ወሌ ኑሮአቸውን ተቀምተው በቁጭት ኖረው ፣ ተዋግተው በመሞታቸው ቀኛዝማች ምስጋናው እንዲህ ብለው ገጠሙላቸው፡-

አባ ደልድል ጉግሣ ጣሉህ እንደ ማንም
እንዳላለቅስልህ ያለ ቀን አይሆንም ።

ለራስ ጉግሣ ወሌ ለማልቀስ ጃንሆይ እስኪሞቱ መጠበቅ ያስፈልጋል ። በጣይቱ የወንድም ልጅነት ምኒልክ ልጃቸውን ዘውዲቱን ዳሩለት ። ጣይቱ ሲጋዙ እንደገና እስረኛ አደረጉት ። በ1909 ዓ.ም. ንግሥት ዘውዲቱ ሲነግሡ እንዳይመክር ፣ እንዳይዘክር ተፈርቶ ትዳሩን አፋቱት ። አርቀውም ሾሙት ። በቁጭት ተዋግቶ ቢሞት ለማልቀስም ዘመኑ አልፈቀደም ። ጃንሆይ የወረዱት በ1967 ዓ.ም ነው ። ራስ ጉግሣ የሞተው በ1922 ነው ። ደርግ ሲወድቅ ለዓመታት ታፍነው የኖሩ ለልጆቻቸውና ለዘመዶቻቸው ሞት አልቅሰዋል ። ማልቀስ መቻልም ለካ በረከት ነው ። አዎ ቀኑን በመጠበቅ ልቅሶአቸውን ያፈኑ ዝምተኞች አሉ ። ነቢዩ ዳዊት ዱዳ እስኪመስል ድረስ ዝም አለ ። ለሰው ዝም አለ እንጂ ለእግዚአብሔር ዝም አላለም ። አንዳንድ ዘመንን በዝምታ እናሸንፈዋለን ።

የማርያም ልጅ አስችለን !

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 23 ቀን 2016 ዓ.ም.

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።