እሳት ምንም ቢያምር በእጅ አይጨብጡትም ፣ ጽጌረዳ ምንም ቢዋብ ቀጥፈው አይበሉትም። ሕፃኑ እሳቱን ካልጨበጥኩ ብሎ ሲያለቅስ አዋቂዎች ባለማወቁ ያዝኑለታል። ዓለምን ሁሉ ካልጨበጥኩ ስንል ብዙ ያዩ አይ አለማወቅ ብለው ይሳቀቁልናል። ሕፃኑ ልጅ ጽጌረዳውን ለመብላት ሲፋጠን ያርቁበታል። የሚያምር ሁሉ የሚበላ አይደለም። በዓለም ላይ ገዳይ ነገሮች ሁሉ ውብ ማስታወቂያ አላቸው። ጥሩ ነገር ማስታወቂያ አያስፈልገውም ። እሳትን ካልነካሁ ብሎ ሲያምፅ ወላጆች የሕፃኑን ጣት በትንሹ ያስነኩታል። ካልነካሁ የሚል ልቅሶው በማቃጠሉ ድንጋጤ ይዋጣል። እሳት ማቃጠሉን ለማወቅ መሞክር አላስፈለገንም። አውቀን መተው ችለናል። ሁሉን ቀምሼ ላረጋግጥ የሚል አንድ ቀን መርዝ ቀምሶ ይሞታል። ዕድሜአችንና የተቀበልነው አካል ሁሉን ሞክሮ ለማረጋገጥ የሚበቃ አቅምና ጊዜ የለውም። ትእዛዝ የተሰጠው ክፉውን ያለ ጉዳት እንድናውቀው ነው። ዓለም እሳት ናት ፣ ሕፃን ልባችን ካልነካሁ ሲል በሽታን፣ ውድቀትን እናተርፋለን። ዓለም የሞትታይ ጽጌረዳ እንጂ የምትበላ እንጀራ አይደለችም።
ሕፃን ልጅ እሳትን ሥዕል፣ ጽጌረዳን ጮማ፣ እሾህን ጡት አድርጎ እንደሚያስብ ዓለምን ያመነም እንዲሁ ነው። እዳስሳለው ሲል መቃጠል፣ እበላለሁ ሲል መመረዝ፣ እጠባለሁ ሲል መወጋት ይገጥመዋል። ዓለም የወረት በጀት አላት። አቦ አቦ የምትልበት፣ አንቱ አንቱ የምታበዛበት ማደንዘዣ አላት። ማደንዘዣው ሲያበቃ ሕመሙ ይጀምራል። “የወረት ውሻ ስሟ ወለተ ጴጥሮስ” ይባላል።
ዓለም ዋሾ ናት። እምነት የጣልንበትን ነገር ከቦታው ስናጣው ትልቅ ጉዳት ይገጥመናል። ዓለም አባብላ አስገብታ እየገረፈች ታኖራለች። እንደ በሬ አስብታ ታርዳለች። አለሁ እያለች የመንፈቅ መንገድ ያህል ከእኛ ትርቃለች። ዓለም ዋሾ ናት። ለዘላለም የመጣች ትመስላለች፣ ፀሐይ ሲወጣ ወዲያው እንደ ጤዛ ትረግፋለች። ንጉሡና ባለሥልጣኖቻቸው ታስረው አይበቃም ተብለው ተገድለዋል። እነርሱ ላይ የፈረዱ የደርግ ባለ ሥልጣናት እዚያው ታስረዋል። እስር ቤቱ ዓለም ዋሾ ብሎ የሚመስክር ነው።
ዓለም ዋሾ ናት፣ ዓለም ዘማ ናት። ዓለም እንደ እባብ ለስልሳ የምትናደፍ ናት። ገደል ላይ እንደ ተገኘ ጠላት ገፍትራ የምትጥል ናት። ዓለም ይቅርታ ፣ ዓለም ማስተዛዘኛ የላትም። ዓለም አላውቀውም ብላ ስትክድ አፏን አይዛትም። ዘማ ሳለች ድንግል ነኝ ብላ ትቀርባለች፣ በእጅዋ እስክታስገባ እጅ ትሰጣለች ። ኑሮን አሳምራ ሕይወትን ትነጥቃለች። ውኃን አቅርባ እርካታን ትነሣለች። ጉንጭን እንቡጥ ጽጌረዳ አስመስላ ውስጥን ትጨርሳለች። ትልቅ ቤት አሠርታ ትንንሽ ቡና ቤት ስታንከራትት ታሳድራለች። በቀይ ምንጣፍ እያስኬደች እጅን በደም ታስታጥባለች። በመሐላ ትዳርን አስጀምራ የቤት ውስጥ ድራማ ታስጀምራለች። ይህች ዓለም መኖሪያዋ ኒው ዮርክ ፓሪስ አይደለም። መኖሪያዋ የሰው ልብ ነው። አበባ ሊረግፍ ሲል ያምራል። ዓለምም በመጨረሻው ቀን እውቀትና ውበትዋ ይበዛል። ሊቁ የአገር ሰው እንዲህ እያለ ትዝብቱን ይገልጣል:-
ዓለም ዋሾ ፣ዓለም ወረተኛ ፣ ዓለም አታላይ፣
ጎንደር ቴዎድሮስ ቤት አልነበርሽም ወይ ?
ትግራይ ዮሐንስ ቤት አልነበርሽም ወይ ?
ሸዋ ምኒልክ ቤት አልነበርሽም ወይ ?
ጎጃም ተክለ ሃይማኖት ቤት አልነበርሽም ወይ ?
ወሎ ሚካኤል ቤት አልነበርሽም ወይ ?
ዓለም ዋሾ ፣ዓለም ወረተኛ ፣ ዓለም አታላይ
ወደ እኛ እንዳትመጪ
ከገባሽበት ቤት በደኅና ላትወጪ፣
በትልቁ ፋጋ ኮሶ ሳታጠጪ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 5 ቀን 2ዐ17 ዓ.ም.