የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዓይን የሌለው እግር ፣ እግር የሌለው ዓይን

 አንድ ዓይነ ሸውራራ ሰውዬ መንገድ ሲያቋርጥ ሳያስብ በድንገት ፊት ለፊት ይመጣ የነበረው ሰው ገፍቶት ጣለው ። በዚህ ጊዜ ተናደደና “ሰማህ ወንድሜ ! ምነው የምትሄድበትን ብታይ !” ቢለው ፤ ተጋፊውም ሰውዬ፡- “ምነው አንተስ ወደምታይበት ብትሄድ” ብሎ መለሰለት ይባላል ። 

አንዱ የሚሄድበትን አያይም ፣ ሌላውም ወደሚያየው አይሄድም ። በዚህ ምክንያት ግጭቶች ይፈጠራሉ ። እግሩ የሚጓዝ ዓይኑ ግን የማያይ ብዙ ሰው አለ ። ይህ ሰው እግሩ በመጓዙ ብቻ ልቡ ቢተማመንም ዓይኑ ባለማየቱ ግን ሌላውን ገፍትሮ ይጥላል ፣ ወደ ገደልም ይገባል ። ሌላኛውም የሚያየውና የሚሄድበት ተለያይቶበታል ። የሚያየው ሌላ ነው ፣ የሚሄደው ግን ወዳላየው ነው ። የሚሄዱበትን የማያዩ ግብታውያን ናቸው ። የዘራፍ አብዮት አራማጆች ናቸው ። ያለ ርእሱ የሚጠቅሱ ፣ በብሔሬማ አትምጣብኝ ፣ በባንዲራዬ ድርድር የለኝም ፣ ሃይማኖቴንም አላስነካም ፣ በእመቤቴ ቀልድ የለም ፣ በጌታ አልደራደርም በማለት የተነሣው ጉዳይና የሚመልሱት መልስ ፍጹም የተለያየ ነው ። እንኳን የሰሙትን ነገር የሚናገሩትንም አያስተውሉትም ። ብሔር ማለት ምን ማለት ነው ? ባንዲራ ማለትስ ? ጌታስ ማነው ? ቢባሉ መልስ የላቸውም ። እየተጓዙ ነው ። የሚጓዙበትን እንዲያውቁት ሲነገራቸው ግን ፈቃደኛ አይደሉም ። “ምርምር ማብዛት ያሳብዳል” ይላሉ ። እንኳን ለምርምሩ ለሀሁ አልደረሱም ። የሚያውቁት አንድ ጥቅስ አለ ፣ እርሱን ሁሉ ቦታ ይጠቅሱታል ። መጽሐፉ አይልም ይላሉ ። መጽሐፉ የሚለውን አያውቁም ። ሕገ መንግሥቱ አይፈቅድም ይላሉ ፣ ሕገ መንግሥቱ ስለዚያ ነገር የሚተነፍሰው ምንም ነገር የለም ። ሁሉን ማርከስ ፣ ሁሉን መከልከል ፣ የሚቻልበትን ሳይሆን የማይቻልበትን ነገር መፈለግ የእውቀት መለኪያ ያደርጉታል ። 

እነዚህ ሰዎች የሚሄዱበትን አያዩም ። ስለዚህ ይጋጫሉ ። አገር የጋራ ሳለ የእኔ ብቻ ነው ብለው ያስባሉ ። ሃይማኖት ፍቅር ሳለ “ኧረ ጎራው ተነሥ” ይላሉ ። ለማወቅ አይፈቅዱም ። ነገር ግን ደፋር ሃይማኖተኛ ናቸው ። ደፋር ፖለቲከኛም ናቸው ። ለመማር አይመጡም ፣ “ችግር ካለ ጥሩኝ” ይላሉ ። ራሳቸውን እንደ እሳት አደጋ ሠራተኛ ፣ እንደ አድማ በታኝ ፖሊስ ይቆጥራሉ ። በግርግር ቢሞቱ ታሪካቸው ከአርበኞች ጋር እንደሚነሣ ፣ ሲኖዶስ ተቀምጦ የቅዱስነት ማዕረግ እንደሚሰጣቸው ያስባሉ ። ሞቅ ሞቅ ሲል ደስ ይላቸዋል ። ዓይናቸውን ጨፍነው የሚነዱ ፣ ለተከተላቸው ሰው ኃላፊነት የማይሰማቸው ፣ ቀጥሎ ምን ይሆናል ? በዚህ ንግግሬ ምን ይፈጠራል ? የሚል ልቡና የራቃቸው ሰዎች ናቸው ። የሚሄዱበትን አያዩም ። ያየም ቢነግራቸው አይሰሙም ።

የሚሄዱበትን የማያዩ ሰዎች ብዙ እውቀት ጠል የሆኑ ሰዎችን ማስከተል ይችላሉ ። መምህር ኤስድሮስ፡- “ከመሃይም አትጣላ ፣ ደጋፊው ብዙ ነው ያሸንፍሃል” ብለዋል ። እነዚህ የሚሄዱበትን የማያዩ ሰዎች “አድማ ይሰምርልኛል” በማለት በጽድቁ ቀርቶ በኃጢአቱ ይመካሉ ። ክፋት የምስክር ወረቀት ቢኖረው ይንበሸበሹ ነበር ። የሰሙትን ቁምነገር ከማሰላሰል ቀድሞ ለማስተላለፍ ፣ ከመኖር ያንን ተናገሮ አዋቂ መባልን ይፈልጋሉ ። በሚወስዱት እርምጃ ቤተሰባቸው ምን ጉዳት እንደሚደርስበት ለማሰብ ጊዜ የላቸውም ። እብደታቸውን በብዙኃኑ አጸድቀው ቢሳደቡ “ተናዶ ነው ፣” ቢያዋርዱ “ልማዱ ነው ተዉት” ተብለው ቅድመ ይቅርታ አግኝተው የሚኖሩ ናቸው ። የሚናገሩትን ዓለም ሁሉ ይስማልኝ ይላሉ ። የሰማም እየመሰላቸው በደስታ ይሞላሉ ። ዓለም ግን ኢትዮጵያ የምትባል አገር መኖሯን ለማወቅ እንኳ ይቸገራል ። ኢትዮጵያዊ ነኝ ስንል እንኳ ግር የሚላቸው ፣ አፍሪካ ስንላቸው ኦ ብለው የሚሰሙን አያሌ የዓለም ሕዝቦች ናቸው ። ለራሳችን የሰጠነው ግምት ትልቅ ነው ። እንኳን አማራነትና ኦሮሞነታችንን ኢትዮጵያዊነታችን የማያውቅ የዓለም ሕዝብ አያሌ ነው ። እነዚህ የሚሄዱበትን የማያዩ ሰዎች የሚያዳምጣቸው ሰው ከኢትዮጵያውያን እንኳ ሦስት ፐርሰንት የማይሞላ ነው ። እነርሱ ሲያስነጥሱ ግን ዓለም ሁሉ “ይማርህ” የሚላቸው ይመስላቸዋል ። አዎ የሚሄዱበትን አለማየት ግጭት ያመጣል ። 

የምናምነውን ነገር ማወቅ ቀዳሚ ሲሆን ለዚያ ነገር መታመንም ተከታይ ነገር ነው ። ያለ እውቀት የሚደረግ ነገር በመጀመሪያ ኃጢአት ነው ። ሁለተኛ ወደ እውነተኛ እምነት አያደርስም ። የሚሄዱበትን የማያውቁ ሰዎች ስለሁሉም ነገር የሚመለከታቸው ይመስላቸዋል ። ስለዚህ ርእስ ይዘው እገሌ ትዳሯን ፈታች ፣ እገሌ ባለመውለዱ ምክንያት ሚስቱን ተወ ይላሉ ። ከእውቅ ሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ከሙያቸው እንጂ ከኑሮአቸው ጋር አይደለም ። ትልቁ ችግራችን ድንበራችንን አለማወቃችን ነው ። የትኛውም ሰው የቱንም ያህል ቢቀርበን የግል ሕይወት እንዳለው ማመንና መቀበል አለብን ። እርሱነቱን እንጂ ነጻነቱን መወዳጀት አይገባንም ። የሚሄዱበትን የማያውቁ ሰዎች የሚመለከታቸውን ርእስ አያውቁትም ። ሰው ሲያዳምጣቸው በርግጥ እንደ አዋቂ የቆጠራቸው ይመስላቸዋል ። ሰው ግን የሚሰማቸው ቀጥተኛ የሆነው ኑሮ ሲሰለቸው ለመዝናናት ብሎ ነው ። የሚሰማቸውም የእብደታቸው ልኩ ምን ያህል እንደ ደረሰ ሊገመግም ነው ። 

“አባቴ” ይላቸዋል ሞኙ ። 

ሽማግሌውም፡- “አቤት” ይሉታል ።

“ሰው ሁሉ ይወደኛል” አላቸው ።

እርሳቸውም፡- “አይ ልጄ ጅልን ማን ይጠላዋል?” ብለህ ነው አሉት ይባላል ።

ወደሚያዩበት የማይሄዱ ብዙ ሰዎች አሉ ። የባከነ እውቀት ማለት ይህ ነው ። ተምሮ ወገንን መሰብሰብ ሲገባ ሕዝብ መበተን ፣ ተመራምሮ አገር መጥቀም ሲገባ ትውልድን መበከል ይህ የባከነ እውቀት ነው ። የሚያዩት ክርስቶስን ፣ የሚሄዱት ግን ወደ አረመኔነት የሆነ ብዙ ሰዎች አሉ ። “ክርስቶስን ወደድኩት ፣ ክርስቲያኖችን ግን ጠላሁ” የተባለው ለዚህ ነው ። በእግዚአብሔር ቤት ከዓለም ስለመውጣታቸው የሚያወሩ ብዙ ሰዎች አሉ ። ዓለም ግን ከልባቸው አልወጣችምና ይኸው የእግዚአብሔርን ቤት ያምሳሉ ። “ጀበና ጥዬ ነው የመጣሁት” በማለት ከጣዖት ቤት መምጣታቸውን ዘላለም የሚተርኩ ሰዎች አሉ ። ጀበናው ግን ከእጃቸው እንጂ ከልባቸው አልወደቀም ። ቅንጣት ፍቅር ለሰው የሌላቸው ፣ በአረመኔነት የሚወዳደሩ ፣ የጌታዬ ፍቅር እያሉ ነገር ግን ዘረኝነትን የሚያራምዱ ወደሚያዩት የማይሄዱ ናቸው ። እነዚህ ሰዎች ከሌላው ጋር ሲጋጩ ይኖራሉ ። ሰላም የላቸውም ፣ ከሁሉ ሰው ጋር ይነታረካሉ ። ጠባቸውን መንፈሳዊ ያደርጉታል ። “ስለ ጌታ ብዬ ተሰደድሁ” ይላሉ ። ያሳደዱአቸውን ሲረግሙ ይውላሉ ። ያለቀሱ እንደሆነ እንባቸው ከአዲሱ የዓባይ ግድብ ይልቃል ። “የውሸታም/የዓባይ እንባ ባቄላ ባቄላ ያህላል” ይባላል ። ቀላል ልብ ያላቸው ሰዎች በእንባቸው ይማረካሉ ። በግላቸው ሲጸልዩ እንባ የማይመጣላቸው ፣ ሰው ፊት ሲቆሙ ግን በእንባ የሚታጠቡ ብዙ ናቸው ። እግረ መስቀሉ ሥር ቆመን ያልመጣ እንባ ፣ ሰው ፊት ስንቆም ከመጣ የልመና ስልት እንጂ የክርስትና ፍቅር አይደለም ። 

አዎ ይህች ዓለም የግጭት ስፍራ የሆነችው የሚሄዱበትን በማያዩ እውቀት ጠሎችና ያወቁትን በማይኖሩበት የአፍ አማኞች ነው ። ዓይን የሌለው እግር ወደ ገደል ይሄዳል ፣ እግር የሌለው ዓይን ሲመኝ ይኖራል ። 

ጌታ ሆይ ወዳሳየኸን ዕለት ዕለት መጓዝ ይሁንልን ። 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ነሐሴ 16 ቀን 2012 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ