የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዕድሌ አንድ ጊዜ

የዲያቆን አሸናፊ መኮንን ገጽ ሰኞ ሰኔ 1/2007 ዓ.ም           
 
በከተማው እየቀረ ነው። አሁንም በገጠሩ አለ። አስለቃሾች ተቀጥረው ያስለቅሳሉ። ድምጻቸውና ግጥማቸው ደንዳናውን ሳይቀር  የሚፈነቅል፣ ዕንባ ሽንፈት የሚመስለውን ወንድ ሁሉ የሚያርድ ነው። እጅግ ስሜት ይነካል። ሀዘነተኛው ሀዘኑን በደንብ እንዲያወጣው ይደረጋል። ዛሬ በመግደርደር ሀዘንን ማመቅ ስለበዛ ጭንቀት እያየለ መጥቷል። ሀዘን ካልወጣ ተሰንቅሮ ይወጋል። ታዲያ አስለቃሽነት ሥራ ነውና አልቃሿ መቼም ሰው መሞቱ አይቀርም ብላ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ ተነሥታ ልብሷን ለብሳ ትጠብቃለች። የሞተ ሰው ካለ 11 ሰዓት ላይ ሌላ ሳይቀድማቸው ይዘዋት ይሄዳሉ። ግጥሙ ምን መምሰል እንዳለበት ተጨማሪ ምክር ይሰጣሉ። በዋለበት ውሎ ይመሰገናልና ሙያውና ጠባዩ ይነገራታል። “ባልዋለበት ውሏል ማለት፣ በሰባራ ቅል ውኃ መቅዳት” ይላሉ ራሳቸው አልቃሾቹ። ከሞተ የቆየ ካለም፡- “እገሌን አንሺልኝ፣ አይረሳብኝ” ተብሎ ሸጎጥ ያደርጉላታል። ታዲያ ይህች አልቃሽ መጥተው እስከሚወስዷት ለራሷ ታለቅሳለች። የምታለቅሰውም፡-
“ዕድሌ አንድ ጊዜ በእሬት ተለውሶ፣
ለሠርግ አልጠራ ሁልጊዜ ለልቅሶ፤” እያለች ነው።
ሁሉም የሚያስታውሳት ልቅሶ ያለ ቀን ነው። ለደስታው የሚፈልጋት የለም። የምትነግሠው ሞት ያለ ቀን ነው። በጠዋቱ ያማረ ትጋበዛለች። የምትፈልገውን መርጣ ትጠጣለች። ከልቅሶ ቀን ውጭ ክብርም የላት። እንደነገረኛ እንደ ሞት አግቢ ትታያለች።
አገልጋይም ጌታን ማየት አቅቶት ዙሪያውን ካየ የሚያለቅሰው፡-
“ዕድሌ አንድ ጊዜ በእሬት ተለውሶ፣
ለሠርግ አልጠራ ሁልጊዜ ለልቅሶ” እያለ ነው።

ሐሰተኛ አገልጋይን የሚቀልብ ሕዝብ እውነተኞቹ እጅግ ይከብዱታል። አገልጋይ ለችግር ለልቅሶ ይፈለጋል። ለደስታ ግን የሚፈልገው የለም። በዚህ ዓለም ላይ ስሜት እንደሌለው ግዑዝ ነገር ከሚታዩት የመጀመሪያው አገልጋይ ነው። የሚያዝን፣ የሚከፋ፣ የሚደክም፣ ፍቅር የሚፈልግ አይመስልም። የቱንም ያህል መከራ ቢደርስበት ያውቃል ተብሎ የሚያጽናናው ያጣል። ለመከራ ቀን ግን የሚያስፈልገው የእውቀት ምክር ሳይሆን የፍቅር ድምፅ ነው።  ይችላል ተብሎ ስለሚታሰብም የሚደግፈው የለም። እንኳን ሊደገፍ የሚሰናበተው ይበዛል። ለብዙዎች የሮጠ አገልጋይ ለእርሱ የሚደነግጥለት እንኳ ያጣል። ብዙዎችን ያማከረ ብቻውን እህ ይላል። ከሥጋ ዘመዳቸው ደብቀው ያማክሩታል፣ የሥጋ ዘመድ ያህል ግን አይወዱትም። ከትዳራቸው ሰውረው ያለቅሱበታል፣ የሰው ያህል ግን አይቆጥሩትም። የብዙዎችን ንስሐ ከድኖ ይኖራል፣ የእርሱ ስህተት ግን በአጉሊ መነጽር ይታያል። ለብዙዎች ጓደኛ ይሆናል ብዙዎች ግን አንድ እርሱን በርታ አይሉትም። ለብዙዎች እንቅልፉን ሠውቶ ያገለግላል፣ እርሱ ግን በቀን እንኳ ሰው እየፈለገ ያጣል። ሁሉን እንደ ልጁ ይቆጥራል፣ አባቴ የሚለው ግን አያገኝም። መንፈሳዊ ዝምድና ዋጋ ባጣበት አገር ማገልገል ከባድ ነው። የአገልጋይ መከራ ከማያምኑ ብቻ ሳይሆን ከሚያምኑትም ነው። ጌታ ከመረጣቸውም እንኳ ይሁዳ ነበርና አይገርምም።
አገልጋይ ማለት እንደ ደጃፍ ምንጣፍ ነው። የደጃፍ ምንጣፍ አቧራን ጭቃን የተሸከሙ ሰዎች ወደቤት ለመግባት ሲሰቀቁ አሸክመውት፣ ጠርገውበት በድፍረት ይገባሉ። ምንጣፉ ግን ሳይከብደው ይቀበላል። ያን ወደ ቤት ለመግባት ድፍረት የሰጣቸውን ምንጣፍ ግን ሲጠርጉ ዝቅ ብለው፣ ሲገቡም ዞር ብለው አያዩትም። አገልጋይ ለመሆን ስታስብ ይህ ነው። ሙሉ ክብር ለማግኘት ሙሉ መራቆት ይኖራል።
ሰው የራሱን ችግር መሸከም ባልቻለበት ዘመን የሰውን ንስሐና ጉዳይ የሚሸከሙ አገልጋዮች ዋጋ ሊሰጣቸው ይገባል። በሁሉም አገር አገልጋይ ክቡር ነው። በሂንዱም፣ በቡዲስትም፣ በእስልምናም አገልጋዮቻቸውን ሲያዋርዱ አልሰማንም። በእኛ አገር ግን የመጣብን ቅሌት ምን እንደሆነ ማሰብ ይከብዳል። እንደ ሰራፕታዋ መበለት ኤልያስን እንደተቀበለች፣ እንደ ሱነም ሴት ኤልሳዕን እንዳሳረፈች ብንሆን ብዙ በረከትንና ትንሣኤንም ባየን ነበር /1ነገሥ. 17፣8-24፤2ነገሥ. 4፡8-37። እውነተኛ የጌታ አገልጋዮች ሕመማችሁን የሚጋራ የላካችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ አለ። ለእናንተ የተደረገውን ቀዝቃዛ ውሃ እንኳ ምላሽ ሊሰጥ ያደገደገ ጌታ አለላችሁ /ማር. 9፡41/። አገልጋይን እንደ ስጦታችሁ ያያችሁና ያበረታችሁ ምእመናን በረከታችሁ እንዴት ብዙ ነው!!!
ሁለት ባልና ሚስት ወንጌላውያን ለሃያ ዓመታት በአፍሪካ ወንጌል ሲሰብኩ ቆይተው ወደ አሜሪካ ይመለሳሉ። እነርሱ በገቡ ቀን ፕሬዝዳንት ሩዝቬልት ለአደን ወጥተው ሲመለሱ ብዙ ሺህ ሕዝብ ቆሞ ይጠብቃቸው ነበር። በዚህ ጊዜ ሁኔታውን በቴሌቬዥን የምትከታተለው ሴት ለባሏ፡- “እኛ ለነፍስ ማዳን ሥራ ሃያ ዓመት ቆይተን ስንመጣ ማንም አልተቀበለንም፣ ፕሬዝዳንቱ ግን ነፍስ ለማጥፋት ወጥተው ሲመለሱ ሁሉ ተቀበላቸው አያሳዝንም ወይ?” ብትለው “አያሳዝንም እኛ እኮ አገራችን አልደረስንም” አላት ይባላል። ተቀባይ ያጣችሁ የመሰላችሁ የጌታ ባለሟሎች አገራችሁ አልደረሳችሁምና በርቱ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ