የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዘመናችንን አድስ

“አቤቱ፥ ወደ አንተ መልሰን እኛም እንመለሳለን ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ።”
ሰቆቃወ ኤር. 5፡21 ።

ይህ የልቅሶ ድምፅ ፣ ይህ የንስሐ ጩኸት ፣ ይህ ከራሴ አድነኝ የሚል ምህለላ ሲሰማ ኢየሩሳሌም ፈርሳ ፣ ቅጥሯ ተንዶ ፤ ትንቢት የተነገረለት ፣ ሱባዔ የተቆጠረለት መቅደስ ፈርሶ ነበር ። ባቢሎናውያን ላይበሏት ኢየሩሳሌምን አርደው ፣ ሕዝቡንም አፍልሰው ነበር ። አይሁዳውያን ከቤተ መንግሥት የተማረከ በቤተ መንግሥት ፣ ከእርሻ የተማረከ በእርሻ የሚኖር ግን የደለበ ባሪያ ሆነው ራሳቸውን በባቢሎን አግኝተውት ነበር ። ባቢሎናውያን ወደ ሰሎሞን መቅደስ መዶሻና እሳት ይዘው ሲቃረቡ ድንቅ የዝማሬ ቃና ሰምተው ነበርና ይህን ዝማሬ በባዕድ ምድር እንዲዘምሩላቸው ጠየቁአቸው ። ዝማሬ ግን ለትዝታ ሳይሆን ለአምልኮ ፣ ለዜማ ጥበብ ሳይሆን ለተመስጦ የሚቀርብ በመሆኑ ካህናቱ እንቢ አሉ ። ቅዳሴውን በመቅደሱ እንጂ ፣ የአምላክን አምኃ ለጨዋታ አይቀርብም ብለው መሰንቆዎቻቸውን በአኻያ ዛፎች ላይ ሰቅለው ነበር ። ከአምልኮተ እግዚአብሔር የተፈናቀሉ ፣ አገር የለሽ ሆኑ ። ልቅሶው ብቻ ሳይሆን ማልቀሻ ቦታም አጡ ። ድህነታቸው እጅግ የሚያሳቅቀው ጠላት ለመማረክም የተጸየፋቸው ጥቂት አይሁዳውያን በኢየሩሳሌም ቀርተው የጎረቤት ሕዝቦች መዘበቻ ሆነው ነበር ። አገር እያላቸው አገር የለሽ ፣ እንጀራ እያላቸው ረሀብተኞች መሆናቸው ያሳዝናል ።

ንጉሡም ሕዝቡም በባቢሎን ምርኮኛ ሆነው ነበር ። ለኃጥአን የመጣ ለጻድቃን ይተርፋልና ነቢዩ ኤርምያስም በባቢሎን ተጋዘ ። ባለጌ ልጅ ቆሞም ሞቶም ያሳዝናልና ነቢዩ ሁለት ጊዜ ቆዘመ ። ምክሩን አልሰማ ብለው በኃጢአት ኳስ በተጫወቱ ጊዜና ፣ ኳስ ነው ያሉት ቦምብ ፈንድቶ በሞቱ ጊዜ አለቀሰ። እግዚአብሔር ሕዝቡን ጨርሶ እንዳልተወ ምልክቱ መምህራን መኖራቸው ነውና ነቢዩ ዳንኤልና ሕዝቅኤል የምርኮ ዘመን ነቢያት ሁነው ተነሡ። አገርን ያለ ንጉሥ ፣ መንበሩን ያለ ካህን ፣ ሕዝቡን ያለ መምህር አትተው ብሎ መጸለይ በእውነት ይገባል ። ነቢዩ ኤርምያስ ለዚያ ሕዝብ ሙሾ ጀመረ ። ወትሮም አልቃሻ ነቢይ ነበረ ። “እንኳን እናቴ ሙታብኝ እንዲሁም አልቅስ አልቅስ ይለኛል” እንዲሉ እንኳን ኢየሩሳሌም ሙታበት እንዲሁም አልቃሻ ነበር ። እርሱ የታየውን ሕዝቡ አልታይ አለውና አልቃሻ ሆነ ።

በእንባ ጅረትም፡- “አቤቱ፥ ወደ አንተ መልሰን እኛም እንመለሳለን ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ” ብሎ ለመነ ። ልባችንን እንደ ሰዓት ቆጣሪ በራስህ ፈቃድ ላይ አስቀምጠው ፣ ነጻ ፈቃዳችንን ተጠቅመን ለውጠን እንልሃለን እያለ የሸፈተ ልብን ለእግዚአብሔር ተናዘዘ። ዘመን አርጅቶብናልና አድስልን አለ ። ዘመን ሰው ነው ፣ ሰውም ዘመን ነው ። ዘመን እንደ ሰው ያረጃል ። ያረጀ ዘመንም ያረጀ ዓለም ይወልዳል ። ዘመን ሲያረጅ የኋላ ትዝታ እንጂ የፊት ተስፋ እያጣ ይመጣል ። ድሮ በአባቶቻችን ዘመን እየተባለ ክፉውም እንደ ደግ ይተረካል ። ከደግና ከክፉ የሚመርጥ የምቾት ዘመን ነዋሪ ነው ። ከበጣም ክፉ የተሻለ ክፉ ይመረጣል ። ትዝታ ለወሬ እንጂ ለጥጋብ አይሆንም ። “አገር ሲያረጅ ጃርት ያበቅላል” ይባላል ። ሁሉም ነገር እየተዋጋ ይመጣል ። ግራ ቀኙ የሚያሳርፍ ርእስ ይታጣበታል። “ወዳጅ ሲያረጅ በጓሮ ይሄዳል ።” ዘመንም ሲያረጅ የኋላ ትውስታ እንጂ የአሁን እውነት ፣ የፊት ተስፋ ያጣል ። ያረጀ ዘመን አማኞች የሚወገዙበት ከሀድያን የሚጸድቁበት ነው ። ያረጀ ዘመን ሚዛንን ይጥላል ። ያረጀ ዘመን ፍርስራሹ ይበዛል ። ደጉ ቃል በክፉ ይመነዘራል ። ሰዎች በክስ ይጠመዳሉ ፣ ለንስሐ ጊዜ ያጣሉ ። ቀን ሲከፋ ያሳደጉት ውሻ ይነክሳል ። እንጀራችንን የበላ ተረከዙን ያነሣብናል ። እኛ ለተቸገርነው የሚሰናበተን ይበዛል ። ብዙ ሰዎች ጭር ሲል አይወዱም ። እንደ ዘፈን ባንድ ሰርግ እንጂ ልቅሶ አይፈልጉም ።

ያረጀ ዘመን ዳኛ ወንጀለኛ የሚሆንበት ፣ የሰው ሕይወት በገንዘብ የሚለወጥበት ፣ ነቢያተ ሐሰት የሚንጎማለሉበት ፣ ጥቅመኛ አማኞች የሚፈሉበት ነው ። ያረጀ ዘመን ካህን ጠመንጃና መስቀልን ላስታርቅ የሚልበት ፣ መነኩሴ መሳፍንት ካልሆንሁ እያለ የሚዳክርበት ፣ ወንጌላዊ በነፍስ የሚነግድበት ነው ። ያረጀ ዘመን ፍቅር ሞኝነት ፣ ትሕትና የበታችነት የሚባልበት ነው ። ያረጀ ዘመን እንደ ተሳለ አንበሳ ፣ እንደ ግድግዳ ሥዕል ሽማግሌ የማይታፈርበት ነው ። ያረጀ ዘመን ሁሉም ልጅ ለመሆን የሚጥርበት የሽምግልና ቋንቋና አለባበስ የሚናቅበት የሕፃናት ዓለም ነው ። ባለ ሙሾው ነቢይ ያ ዘመን፡- አገር የሚናድበት ፣ መቅደስ የሚቃጠልበት ፣ እርሱ እንጂ እኔ አጠፋሁ የማይባልበት ነውና ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ ብሎ ለመነ ።

ጸሎት

አንድ እርምጃ ወዳንተ ከመጣን በኋላ ሁለት እርምጃ የምንሸሽህ ፣ ገብተን የማናልቅ ልጆችህ ነንና እባክህ ወደ ራስህ መልሰን ። ቆንጆና ጎበዝ ሲቀጠፍ እናይና ዓለም ከንቱ ነው እንላለን ፤ መልሰን የንብረት ውድድር ውስጥ እንገባለን ። ያረጀውን ዘመናችንን አድስና አገርን በክብር ፣ ቤትህን በፍቅር ጠብቅልን ። በማይረታው ኢየሱስ በተባለው ስምህ ። አሜን ።

ዕለተ ብርሃን 2

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 2 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ