የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዛሬ ና

 በውስጤ ሳለህ ብዙ ዘመን በአፍኣ ፈለግሁህ ። የወደድኸኝ አንተ እያለህ የሚወዱኝን ለማየት ዓይኔን አማተርሁ ። ቃልህን እያሰማኸኝ የሰዎችን የድምፅ ቅላፄና ቃና መረመርሁ ። በራሳቸው ጉዳይ ሲያኮርፉ በእኔ ጉዳይ መሰለኝ ። ፊትህን ገሸሽ ብዬ የፍጡራንን ፊት አሰስሁ ። ስትከተለኝ ጀርባዬን ሰጠሁህ ። ስትጠራኝ የባልንጀሮቼን ጨዋታ ወደ መስማት አዘነበልሁ ። ሞተህልኝ ሳለ በጥቂት ፍላጎቴ ጠረጠርሁህ ። ደምህን አፍስሰህልኝ ሳለ ዋጋዬን አሳንሼ ኖርሁ ። አኗኗርህ የከበረ ፣ ሳይሾሙህ የምትሾመው ንጉሥ ፣ ካንተ ፊት ቀደምሁ ፣ ካንተ ኋላ ቀረሁ የሚልህ የለምና የነግህ ምስጋና አቀርብልሃለሁ ። የጦር መሪዎች ሰማዕታት ፣ ቆነጃጅት ደናግላን ፣ ነገሥታት መናንያን ፣ ገዳዮች ሟች ፣ ተቃዋሚዎች ሐዋርያት ፣ አሳዳጆች ወንጌላውያን የሆኑልህ ሁሉን በፍቅር የረታህ አንተ ጌታዬ ነህ ። አንተ በአንድ ቀን የተቀበልከውን መከራ እኔ በሕይወት ዘመኔ በየተራ ብቀበለው ይከብደኛል ። መከራዬ በመከራህ ፊት የማይወራ ብናኝ ነው ። ወደ አገሬ ስደርስ ፣ ወደ ቤቴ ስመለስ የምትቀበለኝ ፣ በሰማይ አዳራሽ ሰርግን ፣ በመንግሥተ ሰማያት እልፍኝ መኖሪያን ያዘጋጀህልኝ የምድር ኑሮዬ ቢፈርስ ባንተ እጽናናለሁ ። ማን ይቀበለኛል ? ብዬ አልሰጋም ። በምድርም በሰማይም ያለኸው አንተ ነህ ።
ነፍሴን ከጽኑ ቊጣ በራስህ ውስጥ የሸሸግሃት ፣ በፍቅር ብርሃንም ያረጋጋሃት አንተ ነህ ። ለኃይልህ ጠፈር ፣ ለክብርህም ጉልላት የለውም ። የተሠሩ ከተሞች ሲፈርሱ ፣ ያማሩ እንዳልነበሩ ሲሆኑ ያንተ ሥራ ግን ጸንቶ ይኖራል ። ስንት አምፑል ሲቃጠል ያንተ ፀሐይ ግን ታበራለች ። ስንት እቅድ ከመንገድ ሲቀር ያንተ ወንጌል ግን ዛሬም ይሠራል ። በማጣትም በማግኘትም ነፍሳቸው የተጨነቀችባቸውን እባክህ አሳርፍ ። ነፍሶችን ለማዳን የሚሮጠውን ያንተን አገልጋይ ሩጫውን ባርክለት ። ልነቀል ፣ ልነቀል የምትለውን የምእመን ነፍስ አንተ አጽና ። ሕይወት የመረረውን አንተ አጣፍጥለት ። አሳቡ እየባከነ ማንበብ ፣ መጸለይ ያቃተውን አንተ አረጋጋው ።
የበሰለ በረከት ያለህ ፣ በሰማያዊ ማዕድም ገና የምታጠግበን ፣ ለመኖራችን ትርጉም ፣ ለሞታችንም አድራሻ የሰጠኸው ጌታ አንተ እግዚአብሔር ነህ ። እችላለሁ ብዬ ብቻዬን የተጓዝሁበት ፣ አውቀዋለሁ ብዬ መንገዱን የጀመርሁበት ፣ ጀግና ነኝ ብዬ ጦርነት ውስጥ የገባሁበት ፣ ጠቢብ ነኝ ብዬ መድረክ የፈለግሁበት ያን ሁሉ ዘመን አንተ ካሰው ። አንተ ከሌለህበት ነገር ሁሉ ባዶና አሰልቺ ነው ። እጅህን ጭነህ ባርከኝ ፣ በእፍታህም ሕይወት ዝራብኝ ። ከአፈርነት ሰው አድርገኝ ። ዕድል ፈንታዬን ከማዕድህ ከሚቆርሱት ልጆችህ አድርግልኝ ። የቡችሎችን ፍርፋሪ ገንዘብና ጤናን ብቻ መሻት ከእኔ ይራቅ ። የልጆችህን ገበታ የነፍስ መዳንን አድለኝ ።
ሰው ቢጨክን አይራራም ። አንተ ግን ብትቀጣም ትመለሳለህ ። ሰው እየለመኑት ይገድላል ። አንተ ግን የለመኑህን ታድናለህ ። በምሠራው ላይ ልትሠራ ፣ በምኖረው ሕይወት ላይ ልትኖር ዛሬ ና ። አሜን ።
የነግህ ምስጋና /5
የካቲት 19 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ