የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዛሬ

“በውድ ልጁም እንዲያው የሰጠን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ይህን አደረገ ።” ኤፌ. 1 ፡ 6 ።

ክርስቶስ ውድ ልጅ ብቻ ሳይሆን ስሙም “ውዴ” የተባለ ነው ። “ውዴ የእኔ ነው ፥ እኔም የእርሱ ነኝ” መኃ. 2 ፡ 16 ። የዚህ ቅኔ አቅራቢ የታደለ ነው ። ምክንያቱም ውዴ የእኔ ነው ፣ እኔም የእርሱ ነኝ ለማለት በቅቷል ። ወደ እኛ ዘመን ብንለውጠው “ውዴ የእኔ ነው ፣ እኔ ግን የእርሱ አይደለሁም” የሚል ቅኔ ይወጣዋል ። ውዴ ማለት የሚወደኝ ፣ የምወደው ፣ የመኖሬ ምሥጢር ፣ በዚህ ዓለም ካሉኝ ነገሮች በላይ የሆነ ትርፌ ፣ ካለፈው ከሚመጣው ነገር በላይ የሆነ ደስታዬ ማለት ነው ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ሁሉ ነው ። እኛን በመውደዱ አይጠረጠርም ። እኛ እርሱን ለመውደድ በትግል ውስጥ ነን ። መኖር ምሥጢር ከሆነ ምሥጢሩ ክርስቶስ ነው ። እንዴት እንዳኖረን የሚያውቀው እርሱ ብቻ ነው ። መንገዱ ሁሉ እግር እግር የሚያይ እባብና ጊንጥ ፣ ሕያው እንቅፋት ባለበት ዓለም ላይ ዛሬን ማየት ተአምር ነው ። በዚህ ዓለም ያለው ነገር ሳይነጋ የሚጨልም ፣ ሳይጀመር የሚያልቅ ነው ። ደስታው ፍጹምነትና ዕድሜ እያጣ በአንድ ዓይን እየሳቁ በአንድ ዓይን እያለቀሱ የሚኖሩበት ዓለም ነው ። ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ግን የዕንባውን ክረምት የምንወጣበት ደስታችን ነው ። ጥያቄ መልሱን ሲናፍቅ መልሱ ጥያቄ በሚሆንበት ዓለም ላይ ፣ እየተራቡ ማልቀስ አልፎ እየበሉ ማንባት በሚቀጥልበት ምድር ውስጥ ከእርሱ በቀር ለልብ ድጋፍ የሚሆን ፣ የነፍስን ማዕበል ገሥጾ ሰላም የሚሰጥ የለም ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአባቱ ውድ ልጅ ነው ። እርሱ የአማንያንም ውድ ነው ። እርሱ ውዴ ተብሎ የሚጠራ ነው ። ውድ የተወደደ ፣ ከፍ ያለ ፣ የከበረ ፣ ሕይወት የሚሰጡለት ነው ። እግዚአብሔር አብ ለዓለም የሰጠው ውድ ልጁን ነው ። ላገኘናቸው ስጦታዎች ሁሉ መሠረቱ ክርስቶስ እንጂ የእኛ መልካምነት አይደለም ። ወደ ዓለም ያመጣው የእኛ ጽድቅ ሳይሆን በተቃራኒው ኃጢአታችን ነው ። ዲያብሎስ አሳተን እንጂ ኃጢአተኛ አላደረገንም ። ኃጢአተኛ ያደረገን ምርጫችን ነው ። እኛ ብቻ ሳይሆን የምንኖርባት ምድር ተረግማ ሳለ የእኛን ሥጋ በመልበስ ፣ የእኛን ምድር በመርገጥ ሊቀድሰን መጣ ። ነገረ ሥጋዌ ሰው ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅር ሳይሆን እግዚአብሔር ለሰው ያለውን ፍቅር አመልካች ነው ። ትእዛዛት እንደማይገዙን ፣ ፍቅርም እንደማያሸንፈን ቢያውቅም ትእዛዛቱን የፍቅሩ መገለጫ ፣ ሞቱንም የፍቅሩ ፍጻሜ አድርጎ ለዓለም ገለጠ ። መስፈርት ከመጣ ልንወደድ የማንችል ፣ መንገድ የምንቀር ፣ ሚዛን የማንሞላ ነን ። እንዲያው በሚለው መስፈርት በከንቱ ፣ ያለ መለኪያ አዳነን ።

እንዲያው ሲል ርካሽ ማለት አይደለም ። እንዲያው ሲልም ምላሽ የማይሻ ማለት አይደለም ። አዳም በገነት አንዲት ሕግ ተሰጠችው ፣ በአዲስ ኪዳን ደግሞ አንዲት እምነት ተሰጠች ። ዕፀ በለስን አትብላ በሚል ሕግ የወደቀው የሰው ልጅ ኅብስተ ሕይወት ክርስቶስን ብላ የሚል እምነት ተሰጠው ። ላለ መብላት መታዘዝ ፣ ለመብላትም እምነት ያስፈልጋል ። የሰው ልጅ አትብላ ተብሎ በመብላቱ ሕግ አፍራሽ ሆነ ። ብላ ተብሎ ባለመብላቱ ኢአማኒ ሆነ ።

ጸጋው በሙላት የፈሰሰው እንዲሁ አይደለም ። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ጸጋ ተራ ነገር አይደለም ። ክብር ያለው ነው ። መጣያ ጠፍቶ የተሰጠ አይደለም ፣ የወደቀውን የሚያነሣ አቅም ነው ። ለጉራም የተቸረ አይደለም ፣ የፍቅር ማብራሪያ ነው ። በአደባባይ ቢሰጥም በልባችን ጓዳ የምንቀበለው ነው ። ጸጋው የቁሳቁስና የምድራዊ ነገሮች ስብስብ አይደለም ። ክርስትና የሕይወት እንጂ የቁሳቁስ ዋስትና መስጠት ባሕርይው አይደለም ። ጸጋው ክብር ያለው ነው ። ጸጋው ክብር ሊሰጠው የሚገባም ነው ። ስጦታ ሰጪውን የሚያስደስተው ተቀባዩንም የሚጠቅመው አክብረው ሲወስዱት ነው ። እግዚአብሔር ባለ ጸጋ ሳለ ራሱን የሰጠበት ፣ እግዚአብሔር ከእግዚአብሔርነቱ ጋር እኛን ያስማማበት ምሥጢር ትልቅ ነው ።

ይህን ጸጋ ባለን ንብረት ልንገዛው ፣ ብድርም ልንመልስ አንችልም ። የጸጋውንም ክብር ግን ማመስገን ያስፈልገናል ። ዝማሬአችን ነገረ ድኅነትን ፣ ስብከታችንም ነገረ መስቀሉን ማዕከል ማድረግ ያስፈልገዋል ። በአሁንነት ከልደቱ እስከ ሞቱ ያለውን ክንውን ማሰብ እርሱ እምነት ይባላል ። እምነት አሁን ነውና ። በልደቱ “ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ ፣ የዓለም ሁሉ ቤዛ ዛሬ ተወለደ” እያለች ቤተ ክርስቲያን የምትዘምረው እምነት አሁን ስለሆነ ነው ። ሥርዓተ ቅዳሴም ቀራንዮን ዛሬ የሚያደርግ ፣ ትኩስ መሥዋዕት የሚቀርብበት ነው ። ታሪክ ለመዘከር የምትቀድስ ቤተ ክርስቲያን ሳትሆን ዕለተ ዓርብን ዛሬ አድርጋ ፣ በእግረ ሕሊና ቀራንዮና ሰማይ አማኞቿን የምትወስድ ሕያዊት ቤተ ክርስቲያን ናት ።

የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /13

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 23 ቀን 2014 ዓ.ም.

እባካችሁ ለሌሎች አካፍሉት

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ