የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሀገር ሽማግሌ፣ ደራሲ፣ ጋዜጠኛና ተርጓሚ የነበሩትን አቶ ማሞ ውድነህን በጨለፍታ ስንዘክራቸው፡፡

‹‹የክርስቶስ ቤተሰቦች ከሆን፣ መሆናችንንም ካመንበት በኅብረተሰቡ ጉዳይ ገለልተኞች መሆን አንችልም፡፡››
/የደረስኩበት (ክፍል 2) ፣ ማሞ ውድነህ፣ እኔና ትዝታዎቼ፣
ገጽ 72፡፡
ለምዶብን እኛ ኢትዮጵያውያን ስንባል በየትኛውም መስክ ያሉንን ጀግኖቻችንን በሕይወት ሳሉ የማመስገንና ሥራቸውን ቦታ ሰጥተን የመዘከሩ ባሕል ብዙም የለመድነው አይደለም፤ ስለዚህ ብዙ ጊዜ ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ብዙ ውለታን የዋሉ የሀገራችን ሰዎች በመጨረሻው የሕይወታቸው ዘመን እንዲያም ሲል ከሞቱ በኋላ ነው ሥራቸውን እንዲሁም ለሀገራቸውን ያደረጉትን ውለታ ለማውራትና ሥራዎቻቸውንም ሌሎች እንዲያውቁት የምንተጋው፡፡ ለአብነትም ያህል አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንኳን በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ የነበራቸውን ክቡር ሐዲስ ዓለማየሁንና ክቡር ከበደ ሚካኤልን ለሥራቸው ዕውቅና በመስጠት የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የሰጣቸው በዕድሜያቸው ጀንበር ማዘቅዘቂያ ላይ መሆኑን ታዝበናል፤ ይሄም ቢሆን መቼም ከምንም ሳይሻል ይቀራል ብላችሁ ነው?! ከዚህ ባሻገር ግን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ የቀድሞ ደራሲዎቻችንን ሥራዎች እንደ ገና በማሳተም ትውልዱ ከቀደሙት አባቶቹ ሥራ ጋር ይተዋወቅ ዘንድ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው፣ የቀድሞ ጸሐፊዎቻችንንም በሚገባ እንድናውቃቸው እያደረገ ነውና ሊመሰገን ይገባዋል፡፡
ይህ ባሕላችን ግን ተቀይሮ ጀግኖቻችን በሕይወት ዘመናቸው እያሉ ጭምርም ሥራዎቻቸውንና ለሀገራቸው ያደረጉትን ውለታ የምንዘክርበት ሁኔታ ቢመቻች መልካም ነው እንላለን፡፡ ለዚህም የበኩላችንን ጥረት ሁሉ እናደርጋለን፡፡ እንደ ክርስቲያንም አመስጋኞች፣ ለአባቶቻችንና ለወንድሞቻችን ድካምና ልፋት የሚገባቸውን ክብርና ዕውቅና ልንቸራቸው እንደሚገባን ልናስታውስ እንወዳለን፡፡ ዛሬ ዛሬ ትውልዳችን በቀደሙት አባቶቹ ላይ ልቡ የተቀየመበት፣ ዋ! ነዶ የሚል፣ አባቶቹን በሆዱ የሚያማና የሚወቅስ፣ ለቀደሙት አባቶቹ ሥራና ልፋት ብዙም ዋጋ የሚሰጥ እንዳልሆነ እየታዘብን ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ በአብዛኛው የሚሰጠው ምክንያት በስልጣኔዋና በታሪኳ ገናና የሆነች ሀገር በሚል ያለ መጠን የተጋነነ ስምና ኩራት  ያስረከቡን ነገር ግን ሀገራችን ትክክለኛ ማንነቷ ሲገለጥ በድህነትና በኋላ ቀርነት የዓለም ጭራ የሆነች፣ በከንቱ ውዳሴና በአጉል ትምክሕት የትናንትናው ትውልድ ‹‹የነበር ታሪክን›› እሳት በመሞቅ ተደላድሎ በመተኛቱና የበኩሉን ድርሻ ባለመወጣቱ ለዚህ ድቀትና ውርደት ዳርገውናል፣ ለትውልዳቸው የሥራን ክቡርነትና ፍቅርን ሳይሆን ያወረሱን ዳቦ ሊሆነን ያልቻለ ‹‹ባዶ ኩራትንና የጦርነት ታሪክ ነው›› በማለት ያለፈውን ትውልድ የሚያብጠለጥል እንዲሆን ሆኗል አብዛኛው የዛሬ ወጣት፡፡
ይህ በትናንትናውና በዛሬው ትውልድ መካከል ያለው መወቃቀስ ባለ ብዙ መልክ ነው፤ አባቶች ልጆቻችን ያለ ፍሬ መከኑብን፣ ገና በቡቃያነታቸው ተቀጩብን፣ መልካሙን መንገድ ለመማር በቀናው መንገድ ለመሄድ አልታደሉም እያሉ በአብራኮቻቸው ክፋይ ያለ ፍሬ በከንቱ መቅረት ሲያማርሩና ልባቸው ሲያዝን፤ ልጆች ደግሞ ‹‹ያልዘሩት አይበቅል›› በሚል በራሳቸው በአባቶቻቸው ተረት ‹‹ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል›› እንዲሉ በማለት ዘራችሁ መልካም ቢሆን እኛም ፍሬያችሁ እንዲህ ባላሳማናችሁ የሚል የመከራከሪያ ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡ ርዕሰ ጉዳዩ እኛም የትውልዳችን አንድ ክፍል እንደመሆናችን መጠን ብዙ ሊያነጋግረን ብዙ ሊያወያየን የሚችል ቢሆንም፤ እኛ ግን እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታችንና አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠንም ልናስተላልፈው የምንፈልገው መልእክት አለን ይኸውም፡-
ኃላፊነት የሚሰማው፣ አባቶቹን የሚያከበር ለሀገሩ፣ ለወገኑ ባለ ራእይ የሆነ፣ በተስፋና በፍቅር ቃል ኪዳን፣ በታማኝነትና በሞራል ሕግ የሚኖር የተባረከ ትውልድን በመፍጠር ረገድ ቤተ ክርስቲያን የምታደርገውን ጥረት በሐሳብ፣ በጸሎትና በተግባርም ጭምር ማገዝ ነው፡፡ ስለዚህም ትውልድ በመቀባበል በቅንነትና በሥራ ፍቅር ለነገ የሚገነባትን ሀገር በማሰብ ትውልዱ ከትላንትናው የአባቶቹ ብርታትና ድካም በመማር የዛሬ ሕይወቱ ያማረና ነገው ደግሞ ለሚመጣው ትውልድ ጭምር መልካም የሆነ ታሪክን ጥሎ እንዲያልፍ ለማድረግ በማሰብ በሀገራችን የሥነ ጽሑፍ ታሪክ፣ በጋዜጠኝነት፣ በሀገር ሽማግሌነት፣ በመልካም ቤተሰባዊ ኖሮአቸውና የሕይወት ምስክርነታቸው ለብዙዎቻችን ምሳሌ የሆኑትንና ትላንት ረፋዱ ላይ ያረፉትን ዕውቁን ደራሲ፣ ተርጓሚና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህን በጥቂቱ ልንዘክራቸው ወደድን፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት ስለ ራሳቸው የሕይወት ታሪክ የጻፉትን መጽሐፋቸውን ለማስመረቅ በአዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ ራስ መኮንን አዳራሽ በተደረገው ዝግጅት ላይ ተገኝተን ነበር፡፡ በዚሁ ዝግጅት ላይ ክቡር አቶ ማሞ ውድነህ ትሕትና እና ጥበብ በተሞላበት ንግራቸው፡- ‹‹በእግዚአብሔር ፈቃድ 50ኛው ልጄ እንዲህ ከዓመታት ልፋት በኋላ በእጃችሁ እንዲገባ ሆኗልና አንብባችሁ ከሕይወቴ ውጣ ውረድና ልምዴ እንድትማሩበት ይሁን…›› ነበር ያሉት በአዳራሹ ለተገኙት እንግዶች ሁሉ፡፡
አቶ ማሞ ውድነህ በዘመናቸው እንደነበሩት እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ብላቴና በቤተ ክርስቲያናችን፣ በየኔታ እግር ሥር ቁጭ ብለው ነው ፊደል በመቁጠር የመሃይምነትን የጨለማ መጋረጃ ከዓይናቸው የከሉት፤ በዚሁ በቤተ ክርስቲያናችን በቆሎ ተማሪነት መቆየታቸውን ‹‹የደረስኩበት›› በሚል የጻፉት የሕይወት ታሪካቸው መጽሐፍ ያትታል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ፊደል ቀርፃ፣ ቀለም በጥብጣና ብራና ዳምጣ በየአብያተ ክርስቲያናቱ እና በየገዳማቱ በየአጸዱና በሚያመች ሥፍራ ሁሉ ሰዎች ሁሉ ከዕውቀት ማዕድ ይካፈሉ ዘንድ ለከፈለችው ዋጋ የሀገራችንና የትውልዶች ባለውለታ በመሆኗ አድናቆትና ምስጋና ሊቸራት የሚገባት መሆኑንም እግረ መንገዳችንን መጠቆም እንሻለን፡፡
አቶ ማሞ ውድነህ በሀገራችን የጋዜጠኝነት ሙያ ባልዳበረበት ዘመን በጋዜጠኝነት ከዛም አልፎ በደራሲነትና በተርጓሚነት ከ53 በላይ መጻሕፍቶችን ያበረከቱልን ታላቅ ባለውለታችን ናቸው፡፡ ከዚያም በላይ በመልካም ቤተሰባዊ ሕይወት ለመኖራቸው ብዙዎች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ይኸው ‹‹የደረስኩበት›› የሚለውን መጽሐፋቸውን ከዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የራስ መኮንን አዳራሽ ባስመረቁበት ወቅትም ለረጅም ዘመናት በትዳር የተሳሰሯቸው ባለቤታቸው ከእሳቸው ጋር በአካል ተገኝተው በትዳር ዘመናቸው ያለፉበትን መልካም ልምዳቸውን በማካፈልና ማሞ ውድነህም አሁን ለደረሱበት ሁሉ የሚስታቸው በዋጋ የማይተመን ድጋፍና እንክብካቤያቸው እንዲሁም በአብሮነታቸው ጊዜ ያፈሯቸው ልጆቻቸው ትልቅ የሆነ የሞራል ድጋፍና ብርታት እንደሆኗቸው በምረቃው ሥነ ሥርዓት ገልጸው እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ከእኚህ ሰው ከድርሰቶቻቸው ብቻ ሳይሆን ከሥራ አክባሪነታቸው፣ ከሀገር ወዳድነታቸው፣ ለትውልድ ካላቸው መልካም ራእይና መቆርቆር በተጨማሪም ለብዙዎቻችን ምሳሌ ከሚሆነው ትዳራቸውና ቤተሰባዊ ሕይወታቸው ልንማራቸው የሚገቡን አያሌ ቁም ነገሮች እንዳሉ ልንገልጽ እንወዳለን፡፡
በሀገራችን ያለው የማንበብም ሆነ የመጻፍ ባሕል ገና በሁለት እግሩ ባልቆመበት ማኅበረሰብ ከ1950ዎቹ ጀምረው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ከ53 በላይ መጻሕፍትን በመተርጎምና በመድረስ በኢትዮጵያ የደራሲያን መካከል የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት አቶ ማሞ ውድነህ በተለይም ደግሞ የውጭ ሀገራት የስለላ መጻሕፍትን በብዛት በመተርጎም አንባቢዎች ከውጭ ሀገራት ደራሲያን ጋር እንዲተዋወቁ የተጫወቱት ሚና እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ደራሲያን ታሪክም አቶ ማሞ ውድነህ የዚህን ያህል በርካታ መጻሕፍት ከሳተሙ በጣት የሚቆጠሩ ደራሲያን አንዱ ያደርጋቸዋል፣ ይህም ትልቅ ክብርን ያሰጣቸዋል፡፡
ገና የንባብ ልምድ ባልዳበረበት ሀገር ውስጥ ተስፋ ሳይቆርጡ ተግተው በመጻፍ ካነበቡትና ከሕይወት ልምዳቸው በርካታ ቁም ነገሮችን አካፍለውናል፡፡ እንግሊዛውያን በመጻፍ/በድርሰት ዙሪያ አንዲት የቆየች ድንቅ አባባል አላቸው፣ እንዲህ የምትል፡- ‹‹If you want to change the world pick up your Pen›› ‹‹ዓለምን ለመለወጥ ከፈለግህ ብዕርህን አንሣ›› በእርግጥም ሕዝባቸውንና የሀገራቸውን እድገትና መሻሻል የሚፈልጉ ሁሉ በብዕራቸው የድርሻቸውን በመወጣት ላይ ናቸው፡፡ በሕይወት የተለዩን ደራሲ፣ ተርጓሚና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህም በዘመናቸው ሁሉ ይሄን ትልቅ የታሪክ አደራ ተወጥተዋልና፣ ዘመናቸው በከንቱ አልባከነም፡፡ በብዕራቸው የሚያውቁትን ሁሉ ሊያሳውቁን ደክመዋል፣ ለፍተዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በብዙ ክርስቲያኖች ዘንድ የተወደደላቸውና ብዙ አንባቢን ካተረፉላቸው መጻሕፍቶች መካከል ‹‹ምጽአት እሥራኤል›› እና ‹‹መጪው ጊዜ›› ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ መጻሕፍቶቻቸው የመጨረሻው ዘመን ምልክቶችንና የጌታችንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ዳግም ምጽአት በተመለከተ ሰፊና የተብራራ መረጃዎችን የሚሰጡ ናቸው፡፡ ስለዚህም እኛም ለእነዚህ ሥራዎቻቸውና የሀገር ባለውለታነታቸው እኚህን ታላቅ ደራሲና ተርጓሚ ልናከብራቸውና ልንዘክራቸው ወደድን፡፡
ይሄ ለእኚህ የዕድሜ ባለጸጋ የሀገር ሽማግሌ፣ ደራሲ፣ ተርጓሚና ጋዜጠኛ አድናቆታችንና ሥራዎቻቸውን ማሰባችን በሕይወት በነበሩበት ሰዓት ቢሆን እንዴት ጥሩ በሆነ ነበር ብለን አሰብን፤ ግና እኛም በሀገራችን የቆየው ባሕል ተጭኖን ነው መሰል ለሕክምና በገቡበት ሆስፒታል በትላንትናው ዕለት ረፋድ ላይ የማረፋቸውን ዜና ስንሰማ ሐዘን ተሰማን፣ እናም ቢያንስ በዚህች አጠር ያለች መጣጥፍ ሥራዎቻቸውንና መልካም ምግባራቸውን ልንዘክረው ወደድን፡፡ የደራሲ፣ ተርጓሚና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህን ነፍሳቸውን የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር በአብርሃም፣ በይስሐቅና በያዕቆብ አጠገብ ያኑርልን፡፡ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለሙያ አጋሮቻቸው፣ ለሚያከብሯቸውና ለሚወዷቸው ሁሉ መጽናናትን ይስጥልን! እኛም ለጸሐፊዎቻችን የሞራል ስንቅ ይሆናቸው ዘንድ የደራሲዎቻችንን ሥራዎቻቸውን ልናነብ፣ ልናበረታታቸውም ይገባናል ስንልም መልእክታችንን ልናስተላልፍ እንወዳለን፡፡
                                         እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ