የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሁሉ ቤዛ

 “ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ ፥ ይህም በገዛ ዘመኑ ምስክርነቱ ነበረ”
                                             1ጢሞ. 2፡6
ጠላትን ስለ መውደድ ያስተማረው ክርስቶስ ለጠላቱ ሞቶ ፍቅሩን የገለጠ ነው ። ኃጢአት ከእግዚአብሔር ጋር ጠላት ፣ ከዲያብሎስ ጋር ወዳጅ የሚያደርግ ነው ። የሰው ልጅ በልጅነት ጀምሮ በጠላትነት እንዳይፈጽም ጌታችን ልዋጭ ሁኖ ወደ ዓለም መጣ ። ልጅ ጠላት ሲሆን ምንኛ ከባድ እንደሆነ የደረሰበት ብቻ ያውቀዋል ። የገዛ ልጃቸው ያሳደዳቸውና በአፋር በረሃ ያሰራቸው አንድ ሰው፡-
አለህም እንዳልል እንዲህ ይደረጋል ፣
የለህም እንዳልል ይመሻል ይነጋል ፣
ልጅ እንዴት ባባቱ መድኃኒት ይምሳል ?

ብለዋል ። ነቢዩ ዳዊትም የገዛ ልጁ አቤሴሎም ባሳደደው ጊዜ፡- “አቤቱ የሚያስጨንቁኝ ምንኛ በዙ” የሚለውን መዝሙር ሦስትን ጸለየ ። ሳሚ የተባለ ሰውም በሰደበው ጊዜ የገዛ ልጄ እንዲህ ካደረገኝ ከአንተማ ምንም አልጠብቅም ብሎ ስድቡን ናቀው ። አዳም የእግዚአብሔር ልጅ ነው ። አዳም ግን ከዲያብሎስ ጋር ተሻርኮ የእግዚአብሔር ጠላት ሆነ ። እግዚአብሔር መንግሥቱን በቅጠል ያገኘው ይመስል እርሱም አምላክነትን በቅጠል ለማግኘት ሞከረ ። ውጤቱ ግን “የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች” ሆነ ።
ክርስቶስ ለጠላቶቹ ሞተ ብለን እየሰበክን የገዛ ወዳጆቻችንን መውደድ አቅቶናል ። ብዙ ሰው ጠላትን ለመውደድ ከራሱ ጋር ይታገላል ። ጠላትን የመውደድ መነሻው ወዳጅን መውደድ ነው ። ጌታችን ለሁሉ ራሱን አሳልፎ ሰጠ ። ለሁሉ መጸለይ አቅቶን ፣ የጸሎት አድልኦ የምንፈጽመው እኛ ክርስቶስ ለሁሉ እንደ ሞተ ብናውቅ ደስተኛ እንሆን ነበር ።
ክርስቲያን ነን የምንለው ሳይቀር ቅድሚያ የምንሰጠው ለሥጋ ዝምድና ነው ። መንፈሳዊ ወዳጅነትን በመዝሙር እንጂ በተግባር አናውቀውም ። የእኛ ለሆኑት እንኖራለን ፣ እንሞታለን ፣ እንዘርፋለን ፣ እንዋሻለን ። ከሚሰርቁ ሰዎች ጀርባ የሚሰረቅላቸው ሰዎች አሉ ። ሁሉንም መሣሪያ ተግባር ላይ የምናውለው ፣ “ጦርነት ሕግ የለውም” የምንለው ፣ “በቆሻሻ ውኃም ቢሆን እሳትን ማጥፋት ይቻላል” ብለን የምንፎክረው የእኛ ለምንላቸው ሰዎች ነው ። ታስረው ያልጠየቅናቸው ብዙ ወዳጆቻችን አሉ ። ምክንያቱ የእኛ ስላልሆኑ ነው ። የሥጋ ወንድማችን ቢሆን አንጨክንም ነበር ። ብዙ ድካማቸውን ያወራንባቸው ፣ ሲወራባቸው ለሌሎች ያስተጋባንባቸው ሰዎች አሉ ። ቤተሰቦቻችን ቢሆኑ አናደርገውም ነበር ። የምንኖረው በሥጋ አጥር ውስጥ እንጂ በመንፈሳዊ ከፍታ አይደለም ። አገር ጥለን ተሰድደን የምንረዳቸው ወገኖች አሉን ፣ ለቤተ ክርስቲያን ብለን ግን አገር ጥለን ላንሰደድ እንችላለን ። ከክርስቶስ ይልቅ እኛ የሚለው ወይም የእኔ የሚለው ነገር ይጎላብናል ። ሲወድቁ አልፈናቸው የሄድናቸው ብዙ ወገኖች አሉ ። የእኛ የምንላቸው ሰዎች ስላልሆኑ ነው ። ለራበው ባዳ እጸልያለሁ እንላለን ፣ ለራሳችን ሰው ግን እንጀራ ቆርሰን እንሰጣለን ። እኛ በመንፈሳዊ ዓለምም የምንኖረው ሥጋዊውን ቤተሰብ ነው ። ክርስቶስ ግን ለሁሉ ራሱን ሰጠ ።
“ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ” የሚለውን ቃል ደግመን እናስበው ። ብዙ ነገሮችን ለብዙ ሰዎች ሰጥተናል ። ለጥቂት ሰዎች ራሳችንን እንደ ሰጠን እንናገራለን ። ሲበድሉን ግን ባበላናቸው ልክ እናስተፋቸዋለን ። የኪሱን ገንዘብ ፣ የአእምሮውን እውቀት ፣ የሙያውን አሥራት የሚሰጥ ከተገኘ ቡሩክ ነው እንላለን ። ክርስቶስ ግን የሰጠው ራሱን ነው ። አስቀድሞ ሁሉን ሰጠን በመጨረሻ ራሱን ሰጠን ። ክርስቶስ ራሱን የሰጠው ለሁሉ ነው ። ለልጆቻቸው ሲሉ እሳት ውስጥ የገቡ ደግ እናቶች ፣ ለአገራቸው ሲሉ የተሠዉ ታማኝ ወታደሮች አሉ ። የክርስቶስ ግን ልዩ የሚያደርገው ቤዛነት ነው ። ቤዛ የሚሆን አምላክ ብቻ ነው ። ምክንያቱም በዚህ ልክ መውደድ የሚችል እርሱ ብቻ ነውና ። በስሜት የሚሞቱ ፣ ይህን ከማይ አብሬ ልለቅ የሚሉ አሉ ። ቤዛነት ግን የታሰበ ደግነት ነው ። ቤዛነት ስለ ጠፋ ንብረት የሚከፈል ንብረት አይደለም ። ቤዛነት ራስን መስጠት ነው ። ቤዛነት ሕጋዊ የማዳን መንገድ ነው ። ሕጋዊ ስንል የባሕር ላይ ወንበዴዎችን ፣ ዓለም አቀፍ ማፊያዎችን የሚያደራድሩ ሕጋዊ ተቋማት አሉ ። ቤዛነት ግን ከቅዱስ እግዚአብሔር የመጣ የተቀደሰ የማዳን መንገድ ነው ።
ቤዛ የሚሆን ዘመድ ነው ። ክርስቶስ ለእኛ ቤዛ ለመሆን በድንግል ማርያም በኩል ዘመዳችን መሆን ይገባው ነበር ። ጥቂት ሥጋ ከመርፌ ትወጋ እንዲሉ እንዲቆረቆርልን ፣ ሕጋዊ ከፋያችን እንዲሆን ዘመዳችን መሆን አስፈለገው ።የብሉይ ኪዳን የቤዛነት ፍቺ የተወሰደን ርስት ለማስመለስ የቅርብ ዘመድ የሚከፍለው ዋጋ ነው ። ወንድምህም ቢደኸይ ከርስቱም ቢሸጥ ፥ ለእርሱ የቀረበ ዘመዱ መጥቶ ወንድሙ የሸጠውን ይቤዠዋል” ይላል ። ዘሌዋ. 25፡25 ።
አዳም የሸጠው ልጅነት የተባለውን ርስቱን ነው ። ሁለተኛ ካልተወለድን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ላንገባ ወጥተን ነበር ። ሁለተኛ እንድንወለድ የእግዚአብሔር ልጅ ሁለተኛ መወለድ ነበረበት ። እኛ ከእግዚአብሔር እንድንወለድ እርሱ ከሰው ተወለደ ። ሰማያዊው ምድራዊ ካልሆነ አፈር ትሆናለህ የተባለው የሰው ልጅ ሰማያዊ መሆን አይችልም ። ርስት አስመላሹ የቀረበ ዘመዳችን ነውና ዋጋ ከፍሎ ተቤዠን ።
ሰው ቢታሰር በገንዘብ ይፈታል ። ቢበድል ንብረት ካሣ ይሆንለታል ። የጠፋቸው ነፍስ ግን ነፍሱን የሚሰጥ ካላገኘች ልትድን አትችልም ። ከጠቡ ያለበት አስታራቂ መሆን አይችልም ። ስለዚህ ነቢያት አበው ዋጋ ከፍለው ሊያድኑን አልቻሉም ። ክርስቶስ ግን ንጹሕ ነውና በሞቱ አዳነን ። መላእክት ምንም ቢወዱን ስለ እኛ ቤዛ የሚሆኑበት ሥጋ የላቸውም ። በተፈጥሮአቸው ረቂቃን ናቸውና ። ክርስቶስ ግን ሥጋ ለብሶ ቤዛ ወይም ልዋጭ ሆነን ። ሞታችንን ለራሱ ወስዶ ሕይወቱን ለእኛ ሰጠን ። አንድ መልአክ አስገድሎ ቢያድነን ኑሮ እግዚአብሔር ፍቅር ነው ብለን ለመናገር ባልበቃን ነበር ።
ጌታችን ይህን ማድረጉ በገዛ ዘመኑ ምስክርነቱ ነበር ። ቤዛነቱ የመሰከረው ማዳን የእግዚአብሔር መሆኑን ነው ። በእኛ ጊዜ ሳይሆን በገዛ ዘመኑ የሆነ ነው ። ያለ እግዚአብሔር ጊዜ ውብ የሚሆን የለምና ።
ክብር ምስጋና ሞቶ ላዳነን ክርስቶስ ይሁን ።
1ጢሞቴዎስ /27/
ታኅሣሥ 25 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ