ሰኞ፣ መጋቢት 24 2004 ዓ.ም.
አካሉ ቢተኛም ልቡ ግን በንቃት
በቀንና ማታ ሳያውቅ መሰልቸት
መልካሙን በመግፋት ሞት እንዳያገኘው
ሊቅነቱን ንቆ በልጦ ትህትናው
ሌሊቱ እንደ ቀን አምሮ ተዋቅሮለት
በታላቁ ብርሃን ብርሃን ተገልጦለት
ተደንቆ ይመላለሳል
ትጋቱ ልብን ይሞላል
በድብቅ የሌሊት መጋረጃ
ተሰውሮ በውበት እየተሰራ
አለማወቁን በጌታ እውቀት
የአይሁድ አለቃ መባሉን ንቆት
እየጠየቀ በሞኝ ስብከት
ኒቆዲሞስ
የሌሊቱ ደቀመዝሙር
ሞገስ ሆነለት የጌታ ምክር
የሸመገለ ያረጀ ቀኑ
ስር የሰደደ አለማመኑ
በጌታ ስራ ድል ተመታለት
በበጉ ምክር ተሸነፈለት።
የስጋን ሀሣብ እየነቀሰ
የዳግም ልደት ረቂቁን ምሥጢር እየቀመሰ
በስራው እንጂ በማይታየው የንፋስ ጠባይ
የእስራኤል መምህር እየተማረ ከጌታ አዶናይ
ለመንፈስ አካለ መጠን
ደረሰ ልጁ በመሆን፡፡
ትልቁ የእስራኤል መምህር
እንደ ባዶ ራሱን በመቁጠር
ከእግሩ ዝቅ ዝቅ ብሎ
የወንጌል ፊደልን ቆጥሮ
ተማረ በጌታ ሆኖ
ቢያስፈራም ሌሊት ድቅድቁ
የቀኑ ውበት መድረቁ
ከታደልክ ይሁዳን ካልሆንክ
ምቹ ነው ጌታ ሊሰራክ
ሁንለት ኒቆዲሞሱ
የእውነት ህያው መቅደሱ
ደብቆ እሱ ሲሰራህ
በቃሉ ሲያበጃጅህ
ሰው ሁሉ ሸሽቶ ሲጠፋ
ጎልጎታ አለህ በተስፋ
ይነሳል ብለህ አምነሃል
ተነስቶ ድል ያሳይሀል፡፡