የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሐሜት ቀን ቢታወጅስ ?

አንድ አባት ፡- “በማንሾካሾክ እባብ ሔዋንን ከገነት አስወጣት ፤ ወንድሙንም በሌለበት የሚያማው ልክ እንደዚሁ ነው ፡፡ የሚሰማውን ነፍስ ያጠፋል ፣ የራሱንም ነፍስ ደህና አድርጎ አይጠብቅም” ብሏል ፡፡
ዝም ብለህ ሥራህን ከመሥራት ውጭ ከሰዎች ነቀፋ ነጻ ለመሆን የምታደርገው ጥረት ከንቱ ነው ፡፡ የሚያወሩ ሰዎች የሚሠሩት የሌላቸው ሰዎች ናቸው ፡፡ ቆም ብለህ መልስ መስጠት እነርሱን መሆን ነው ፡፡ ሰዎች ቅዱስ ቢሉህ ቅዱስ አትሆንም ፣ ርኩስ ቢሉህም ርኩስ አትሆንም ፤ የምትሆነው ያው የሆንከውን ነው ፡፡ ሰይጣን ከቻለ ሊያስቀርህ ፣ ካልቻለ ሊያዘገይህ ይፈልጋል ፡፡ ሐሜተኞች የሚያዘገዩ የሰይጣን ካድሬዎች ናቸው፡፡ ማማትን ተጠየፍ ፣ መታማትን ግን ውደደው ፡፡ ስሙ የሚነሣ በሕይወት ያለ ሰው ብቻ ነው ፡፡ የሞተን የሚያማው የለም ፡፡ “ድንጋይ አይነከስ ፣ ሙት አይወቀስ” “ሙት መውቀስ ድንጋይ መንከስ” ይባላል ፡፡ ሰዎች የራሳቸው አመለካከትና አስተዳደግ አላቸውና የወደዱትን ስም ሊሰጡህ ፣ የተመቻቸውን ታርጋ ሊለጥፉብህ ይችላሉ ፡፡ አዎ “ሰዎች ስምህን ሊያጠፉት ይችላሉ ፣ ጠባይህን የምታጠፋው ግን አንተ ነህ ፡፡” ሐሜተኞች የሚያሙህ በተለያየ ምክንያት ነው ፡-

1-  በእነርሱ አሳብ ስለማትሄድና ስለማታጎበድድ ነው ፡፡ ቸግሮህ እንኳ ስለማትለምናቸው ሊናደዱብህ ይችላሉ ፡፡ የበታችነትህን ይመኙታልና፡፡

2-  አንተን የሚሉህን እነርሱ ስለሆኑት ነው ፡፡ ጽድቅም ሆነ ኃጢአት ባልንጀራ ይፈልጋል ፡፡ ስህተታቸውን ባንተ ስህተት ውስጥ በመደበቅ ለማረፍ ስለሚፈልጉ ነው ፡፡ ወይም ቀድሞ ለመጮህ ነው ፡፡

3-  አንተን በማኮሰስ የራሳቸውን ጽድቅ መገንባት ስለሚፈልጉ ነው ፡፡ ጽድቅ የሌላውን ክብርና ስም በመግፈፍ የሚገኝ አይደለም ፡፡ እንደውም ወንድምን በማላቅ ራስን ግን ትሑት በማድረግ የሚገኝ ነው፡፡

4-  ስለበለጥካቸውና ስለተናደዱብህ ነው ፡፡ በዓለም ላይ የአፍን መሳሪያ የሚጠቀም የተሸነፈ ሰው ብቻ ነው ፡፡

5-  ድንበራቸውንና የሚመለከታቸውን የማያውቁ ስለሆነ ነው ፡፡ አጥር በሌለው ሕይወት ስለኖሩ በሁሉ ጉዳይ የእነርሱ አስተያየት አስፈላጊ ይመስላቸዋል ፡፡ አግድም አደግ ቀና ባይልም ቀና ያሉትን አይወድም፡፡ “በቅሎ አትወልድም የሚወልድም አትወድም” እንዲሉ ፡፡

6-  የወሬ ሱሰኞች ስለሆኑ ነው ፡፡ ስቃያቸውን የሚያስታግሥላቸው አንተን አሳንሰው ሲናገሩ ነው ፡፡ ብዙ ጥናቶች እንደሚያሳዩት እነዚህ ሰዎች በቤተሰብ ፍቅር ያላደጉ ናቸው ፡፡

7-  ማንም አይወደኝም ብለው ስለሚያስቡ ነው ፡፡ ከሰው የተቀበልኩትን ለሰው መስጠት አለብኝ እያሉ በሽታ የሚያራቡ እንዳሉ እንሰማ ነበር፡፡ ማንም አይወደኝም ብለው የሚያስቡም የተቀበሉትን ጥላቻ ወይም ያመኑትን ስሜት ሰው ላይ ይለጥፋሉ ፡፡

8-  ከፍተኛ የሆነ የአካልና የሥነ ልቡና በሽታ ስላለባቸው ነው ፡፡ ብዙ ሐሜተኞች በመድኃኒት ኃይል የሚንቀሳቀሱ ናቸው ፡፡ ያለባቸው ውስጣዊ ምሬት ሌሎችን እንዲጠሉ አድርጓቸዋል ፡፡ ሌላውን ለመውደድ ራስን መውደድ ይቀድማልና ፡፡

9-  የእነርሱ ዕድል ያለው ባንተ እጅ ላይ ይመስላቸዋል ፡፡ ሐሜት አቅሙ ትንሽ ቢሆንም በቀል ነው ፡፡ የሚበቀሉት ደግሞ የእኔን ወሰደብኝ ብለው የሚያስቡትን ሰው ነው ፡፡ “ጉንዳን የሚነክሰው ተሸክሞ ለመሄድ ነው ፡፡” አቅሙ ስላልፈቀደ ግን መሸከም አልቻለም ፡፡ ጉንዳን የሚነክሰው ለመግደልም ነው ፡፡ አቅሙ ስላልፈቀደ ነው ፡፡

10-  የእነርሱ ሀብት የግላቸው ያንተ የጋራቸው ስለሚመስላቸው ነው ፡፡  
      የዐረቦች ተረት አለ፡- “ግመሎቹ ይሄዳሉ ፣ ውሾቹም ይጮኻሉ፡፡” አስተውል፡- “የሚቀብሩ ምስጋናዎች እንዳሉ ሁሉ ፣ ከፍ የሚያደርጉ ተቃውሞዎች አሉ ፡፡” በሰለጠኑ ዓለማት እንዲህ ያለው የሐሜት ሱስ ይታከማል ፡፡ በመንፈሳዊ ዓለም ግን የክርስቶስ ፍቅር ሲገዛን ከምንድንባቸው በሽታዎች አንዱ ሐሜት ነው ፡፡ በሽታዎች አደገኛ ፣ ተስፋፊ ደግሞም መድኃኒት የማይገኝላቸው ሲሆኑ በየዓመቱ ይከበራሉ ፡፡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንደ በዓል ይዘከራሉ ፡፡ ሐሜትም ትልቅ በሽታ ፣ ተስፋፊና መድኃኒት እያጣ ነውና ቀን ተቆርጦ ቢከበርለትስ ? መች እናድርገው ? ምን ዓይነት ጥናቶች ይቅረቡ ?
      በመግቢያችን ላይ የጠቀስናቸው አባ ሃይፐርቺዮስ፡- “የወይን ሐረግ እሾህ አያበቅልምና አፋችሁ ክፉ የሆነን ነገር አይናገር ፡፡ … ሥጋ መብላትና ወይን መጠጣት መልካም ነው ፡፡ የወንድምንም ሥጋ በሐሜት አለመጉዳት የበለጠ መልካም ነው” ብለዋል ፡፡ አዎ ሥጋና ቅቤ ቅበላና ፋሲካ አለው ፡፡ የሰው ሥጋ ቅበላና ፋሲካ የሌለው ጾም ነው ፡፡ ደግሞም በባሕላችን አነጋገር፡- “የሰው ሥጋ እርም ነው ፡፡” ስላዳመጣችሁኝ አመሰግናለሁ ፡፡
የደስታ ቋጠሮ/10
ተጻፈ አዲስ አበባ
ሐምሌ 4/2010 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ