የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሐዋርያው የጳውሎስ መልእክት ወደ ሮሜ ሰዎች ትርጓሜ /ክፍል 5

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ቅዳሜ የካቲት 23/2005 ..
ወንጌል
(ሮሜ 1÷1-4)፡፡
አንድ ሊቅ፡– “ሃይማኖት ለእኛ መሰከረች፣ እኛም ለሃይማኖት እንመሰክራለንብለዋል፡፡ ሃይማኖት ወደ እኛ የደረሰችው በምስክርነት፣ ልብን በመማረክ እንጂ በጦር ኃይል አይደለም፡፡ ሃይማኖት ነጻ ፈቃድን የምታከብር፣ በፍቅርና በእውነት ቃል ብቻ የምትማርክ ናት፡፡ እንደ ነጻ አውጪዎች ገድሎ ነጻነት ስለሰጠ መሪ ሳይሆን ሞቶ ነጻ ስላወጣን ክርስቶስ የምትናገር ናት፡፡ ሃይማኖትም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ፡– “ሃይማኖት እንተ እምኅበ አብ ተፈጥረት፣ ሀበ ወልድ ታበጽሕ ወኀበ መንፈስ ቅዱስ ትትፌጸምትርጓሜሃይማኖት በአብ ተጀምራ ወደ ወልድ ታደርስና በመንፈስ ቅዱስ ትፈጸማለችብሏል፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስም ስለ መሰከረችለት ወንጌል ይመሰክራል፡፡ ወንጌልን እንዲህ በማለት ይገልጻታል፡– “… በነቢያቱ አፍ በቅዱሳን መጻሕፍት አስቀድሞ ተስፋ ለሰጠው ለእግዚአብሔር ወንጌል ተለየ፡፡ ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት
ዘር ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” (ሮሜ. 1÷ 1-4)፡፡
ወንጌል የሚለው ቃል የግሪክ ቃል ሲሆን ፍችውም የምሥራች፣ የድኅነት ዜና ማለት ነው፡፡ ወንጌል ራሱ ክርስቶስ ነው፡፡ ቀጥሎ ያሉት ንባባት ይህን ይገልጻሉ፡
ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት” 
                                 (የሐዋ.8÷35)
የጌታን የኢየሱስን ወንጌል እየሰበኩ…”
                                  (የሐዋ. 11÷ 20)
“… የኢየሱስንና የትንሣኤውን ወንጌል ስለ ሰበከላቸው…” 
                                   (የሐዋ. 17÷ 18)                           
        “የክርስቶስን ወንጌል ፈጽሜ እሰብክአለሁ
                                    (ሮሜ.15÷18-19)
        “የክርስቶስን ወንጌል…”
                            (1ቆሮ. 9÷12)
በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት ወንጌል ስለ ክርስቶስ የሚናገር የምሥራች መሆኑን ይገልጣሉ፡፡ ጳውሎስም በዚህ በሮሜ መልእክቱ፡– “ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነውበማለት በግልጽ ተናግሯል (1÷3-4)፡፡ ከአዲስ ኪዳን
መጻሕፍት ወንጌል የሚል ስያሜ የተሰጣቸው አራቱ ክፍሎች ናቸው፡፡ የማቴዎስና የማርቆስ፣ የሉቃስና የዮሐንስ መጻሕፍት ወንጌል ተብለዋል፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወትና አገልግሎት፣ ከልደት እስከ ዕርገት በሙሉነት ስለሚናገሩ ወንጌል የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል፡፡ አዎ ወንጌል ክርስቶስ ነው፡፡
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፡– “የስብከት ማዕከሉ ክርስቶስ ነው፡፡ ክርስቶስ ያልተሰበከበት ስብከት ሁሉ ተረት ነው፡፡ ከምንጩ ስበኩ፣ ከኩሬ ብትቀዱ ያልቅባችኋልይሉ ነበር፡፡ ሊቀ ሥልጣናት አባ ሀብተ ማርያም ወርቅነህም (የአሁኑ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ) “የስብከት ዘዴበተባለው መጽሐፋቸው ስለ ስብከት ጠባይ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፡

“… የእግዚአብሔር ቅዱስ ዓላማ ሰው ሁሉ እንዲድን፣ ሰው ሁሉ የመንግሥቱ ወራሽ እንዲሆን የታለመ ነው፣ ለዚህም ሁሉ መምህር ሆኖ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መጣ የስብከቱ ጠባይ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥራ የሚከተል፣ ራሱን ኢየሱስ ክርስቶስን ማዕከል አድርጎ የሚሄድ ይሆናል፡፡ ስለ ሰው ድኅነት ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ ሙቷል፣ እንግዲያውስ የስብከቱ ይዘት፣ የስብከቱም ጠባይ የተሰቀለውን ኢየሱስን የሚመለከት መሆን አለበት፡፡ምንም የስብከት ምንጩ ቅዱስ መጽሐፍ ቢሆንም፣ ጥቅሱም ከእርሱው ቢወጣም፤ ሐተታውና አገላለጡ ስለ አዳኙ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆን አለበት፡፡ ኢየሱስን ማዕከል ያላረገ የእርሱንም አዳኝነት የማይገልጥ ስብከት ሊሆን ሊባልም አይችልም፣የኢየሱስን ስም የአዳኝነቱንም ሥራ አይናገሩም እንጂ በጠቅላላው ስለ እግዚአብሔር በአይሁድ ምኩራብ፤ በእስላሞችም መስጊድ ሊነገር ይችላል፤ ሲነገርም ይሰማል፡፡ እኛ ክርስቲያኖች ግን መሪያችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሆነ የእርሱን የሕይወት ታሪክ፤ የማዳኑንም ተግባር መመስከር፣ መስበክ፣ መናገርም አለብን፡፡ማንኛውም እውነት፤ ነቢያት የተናገሩት ትንቢት፤ የሰው ልጅ ድኅነት በኢየሱስ ክርስቶስ መፈጸሙን፣ የሁሉም መፈጸሚያ እርሱ መሆኑን በመግለጥ የሚሰበከው እውነተኛው ክርስቲያናዊ ስብከት ነው፣ ሰባኪውም እውነተኛ ሰባኪ ነው” /”የስብከት ዘዴበሊቀ ሥልጣናት አባ ሀብተ ማርያም ወርቅነህ ገጽ 64-68/፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ወንጌል ክርስቶስ መሆኑን ያትታል፡፡ ስለ ወንጌልም ሦስት መግለጫዎችን ሰጥቷል፡
–      ወንጌል ዘመን አመጣሽ አለመሆኗን፣
–      ወንጌል የሰው ሳይሆን የእግዚአብሔር መሆኗን፣
–      ወንጌል ስለ ክርስቶስ የምትናገር መሆኗን ገልጧል፡፡
ወንጌል የዘመናት ተስፋና ፍጻሜ
ወንጌል ዘመን የወለደው ሰው የወደደው አይደለም፤ ወንጌል እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውሃ ፈሳሽ የመጣ ሳይሆን ወንጌል ዓለም ሳይፈጠር እግዚአብሔር እኛን ያየበት የማዳን መነጽር ነው፡፡ ወንጌል በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰውሮ የኖረ ምሥጢር፣ በክርሰቶስ ሞት የተገለጠ ዘላለማዊ እውነት ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ፡– “… በነቢያቱ አፍ በቅዱሳን መጻሕፍት አስቀድሞ ተስፋ ለሰጠው …” ይላል (ሮሜ. 1 ÷2)፡፡
መላው ብሉይ ኪዳን የክርስቶስ ምስክር ነው፡፡ ክርስቶስ በብሉይ ኪዳን በተስፋ፣ በምሳሌ፣ በሕግ፣ በፋሲካው በግ፣ በመሥዋዕት፣ በትንቢት ሲሰበክ ኖሯል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ለይስሐቅ ቤዛ በሆነው በግ ውስጥ፣ በመገናኛው ድንኳንና በመሥዋዕቱ እንዲሁም በፋሲካው በግ ጎልቶ ይታያል፡፡ ብሉይ ኪዳን የአዲሱ ኪዳን ዋዜማ ነው፡፡ በዓሉ ዐውደ ዓመቱ ግን ወንጌል ነው፡፡ ብሉይ ኪዳን የአዲሱ ኪዳን መግቢያ ነው፡፡ ምዕራፉና ፍጻሜው ግን ወንጌል ነው፡፡ ብሉይ ኪዳን የአዲሱ ኪዳን መነሻ ነው፡፡ ፍጻሜው መድረሻው ግን ወንጌል ነው፡፡ እንደ አባቶቻችን አገላለጽ ብሉይ ኪዳን ማጫ ናት፡፡ አንድ ሙሽራ እርሱ ከመምጣቱ በፊት ማጫ /ስጦታ/ ይልካል፡፡ የሠርጉ ቀን ግን ራሱን ይሰጣል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም ለወንጌል ሙሽራው ኦሪትን ማጫ አድርጎ ሰጠ፣ በሠርጉ ቀን በቀራንዮ ግን ራሱን ሰጣት፡፡ ማጫውን የላከ ሙሽራው እንደማይቀር እርግጥ ነው፡፡ ኦሪትም ክርስቶስ እንደማይቀር መያዣ/ዐረቦን/ ሆና ተሰጥታለች፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ከትንሣኤው በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ፡– “ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ አኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነውብሏቸዋል (ሉቃ. 24÷44)፡፡ በሙሴ ሕግ ሲል በአምስቱ ብሔረ ኦሪት፣ በነቢያት ሲል በትንቢት መጻሕፍት በመዝሙራት ሲል በመዝሙረ ዳዊት፣ በመጽሐፈ ምሳሌ፣ በመኃልየ መኃልየ መጻሕፍት
ማለቱ ነው፡፡ ስለዚህ በመላው ብሉይ ኪዳን ስለ ክርስቶስ ተነግሯል ማለት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመምጣቱ ለብሉይ ኪዳን ተአማኒነትን ሰጥቷል፡፡ ትንቢት እውነትነቱ የሚለካው በፍጻሜው ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን እውነትነቱም ፍጻሜ የሆነው ክርስቶስ ነው፡፡ አሁንም ሐዋርያው፡– “የሚያምኑ ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውናብሏል (ሮሜ. 10÷4)፡፡ አዎ ወንጌል ዘመን ያመጣው አይደለም፡፡ አስቀድሞ ተስፋ የተሰጠ ነው፡፡
ወንጌል የሰው አይደለም
ሐዋርያው ጳውሎስ፡– “ለእግዚአብሔር ወንጌል…” ይላል (ሮሜ. 1÷2)፡፡ ወንጌል የሰው አሳብ አይደለም፡፡ ወንጌል እግዚአብሔር እኛን ለማዳን በመለኮታዊ ክብሩ ያቀደልን መፍትሔ ነው፡፡ ሰባኪዎችን መግፋት፣ የሚናገሩትን የወንጌል ቃል አልሰማም ማለት ቅጣቱ ሰማያዊ ነው፡፡ ምክንያቱም ወንጌል በሰው አፍ ብትነገርም የፍጡር መልእክት ሳትሆን መለኮታዊ አዋጅ ናት፡፡ ወንጌልን እንኳን መግፋት ሰምቶ አለማሰማትም ዕዳ አለው (1ቆሮ. 9÷16)፡፡ በጥንቱ አገዛዝ አዋጅ ሲነገር፡– “ያልሰማህ ስማ፣ የሰማህ ላልሰማ አሰማይባላል፡፡ የአዋጅ ግዴታው መስማት ብቻ ሳይሆን ማሰማትም ነው፡፡ የጥንቱን ባሕል ካነሣን ዘንድ ሌላም እንጨምር፡፡ አንድ ንጉሥ ሲሞት ወዲያው አልጋ ወራሹ ዙፋን ናፋቂዎችን ፀጥ ለማሰኘት፡– “የሞትንም እኛ ያለንም እኛ ባለህበት እርጋይላል፡፡ ወንጌልም የሞተውም ያለውም ኢየሱስ መሆኑን በመናገር ሁሉ ለእርሱ እንዲገብር ግድ ትላለች፡፡ አዎ ወንጌል የሰው አይደለም፡፡ ወንጌል የእግዚአብሔር አዋጅ ናት፡፡
ወንጌል ስለክርስቶስ ትናገራለች
ስለ ተለያዩ ሃይማኖታዊ ዕውቀቶች ብንናገር ትምህርት ተብሎ ይጠራል፡፡ ወንጌል ሰበክን የሚባለው ግን የክርስቶስን አዳኝነት ማዕከል አድርገን ስንናገር ብቻ ነው፡፡ በዚህ ሚዛን ወንጌል ሰብከን እናውቅ ይሆን?
ሐዋርያው – “ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነውይላል (ሮሜ. 1÷3-4)፡፡
በዚህ ክፍል ላይ ኢየሱስ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ይናገራል፡፡ አዎ የሰው ዘር እንዲድን ከተፈለገ ሰውን የሚያድነው ወገን ሞቶ መቤዠት ያስፈልገዋል፡፡ በውኃ ዋና የሰጠመውን ሰው ለማዳን ነፍስ አዳኙ ጠልቆ ከሰጠመው ሰው ሥር ገብቶ ወደ ላይ ያወጣዋል፡፡ እንዲሁም በሞት ሰጥሞ የነበረውን የሰውን ልጅ ለማዳን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ መቃብር ወረደ፡፡ ያለ ልክ ከፍ ሊያደርገን ያለ ልክ ተዋረደ፡፡ ኢየሱስ መለኮት ብቻ ቢሆን ስለ እኛ መሞት አይችልም ነበር፤ ምክንያቱም መለኮት በባሕርይው አይሞትምና፡፡ ኢየሱስ ሰው ብቻ ቢሆንም ዓለም አይድንም ነበር፡፡ ምክንያቱም በፍጡር ዓለም አይድንምና፡፡ ነገር ግን ሰው በሆነው በእግዚአብሔር ቃል መዳናችን ተፈጸመ፡፡
ኢየሱስ የተወለደ ብቻ ሳይሆን የሞተም ነው፡፡ የተወለደ መሞቱ የተፈጥሮ ሕግ ነው፡፡ ክርስቶስ ለተፈጥሮ ሕግ አልተወለደም፣ አልሞተም፡፡ እርሱ የተወለደውና የሞተው ለእኛ ነው፡፡ ሞቼ ነበርኩ ብሎ ፈርዖን አልተናገረም፣ ናቡከደነፆርም አልተናገረም፣ እስክንድርም አልተናገረም፡፡ ሞቼ ነበር ብሎ ሞትን ከጀርባው አድርጎ የተናገረው ነባቢ /ተናጋሪ/ መሥዋዕት ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡

ያጋሩ