የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወቴ ሕይወት

የጽርሐ አርያም ጉልላቱ ፣ የጥልቀት መሠረቱ ፣ የአድማሳት ወደብ ፣ የሰማይ ሰማይ ፣ የሕይወቴ ሕይወት አንተ እግዚአብሔር ነህና አመሰግንሃለሁ ። በልብ ሙላት አንተን እንዳወድስ ፣ በውስጥ ቅንነት ወገኔን እንዳገለግል ፣ በመንፈስ ኅብረት እንድሰበሰብ ፣ በተባባሪነት መልካም ከሚሠሩት ጎን እንድቆም ፣ ከሁኔታዎች በላይ ያለውን እውነት እንዳይ ፣ ተራራውን በድል እንድወጣ ፣ በሸለቆውም ተስፋ እንዳደርግ ፣ በጸሎት እንድተጋ ፣ ከበዛ ዝና ጥቂት ትሩፋት እንዲኖረኝ እለምንሃለሁ ። ጸሎትን የሚያህል ሥራ እንደሌለ ፣ ሥራንም የሚቀድስ ጸሎት እንደሆነ ፣ እየሠሩ መጸለይ ፣ እየጸለዩ መሥራትን እንዳውቅ እለምንሃለሁ ። ለአዲሱ አዳም ፍቅር ብታሳየው አይደንቅም ፣ ለወደቀው አዳም ስላሳየኸው ፍቅር አመሰግንሃለሁ ። ከፍታም ዝቅታም አንተን አይለውጥህም ። ሰብአዊውን በአምላካዊ ፣ ቁሳዊውን በሰማያዊ ነገር እንድለውጥ እመኛለሁ ። የላቀ ክብር ላንተ በመስጠት የላቀ በረከት እንደማገኝ ተስፋ አደርጋለሁ ። ቆዳ ካልተወጠረ ተፍቆ ለስልሶ ልብስ አይሆንም ። ሸራውም ካልተወጠረ ሥዕል አይወጣውም ። አንተም በቅንዋት ተወጥረህ በቀራንዮ መብል ሆንከኝ ። እባክህን እንድወጠር ለሠዓሊው ግልጽ እንድሆን አስተምረኝ ። ሠዓሊ በሸራ ላይ ሲስል ፣ አንተ ግን በልብ ሰሌዳ ላይ ትስላለህ ። ሠዓሊ ፍጥረትን ሲስል አንተ ግን አንተነትህን በልቤ ትቀርጻለህ ። ሸራው ልቤ ውጥር ያለ የተገለጸ ይሁንልህ ። ሸራው የራሱን ቀለም ይዞ አይጠብቅም ፣ ባዶ ሁኖ ይጠብቃል ። እኔም ባዶነቴን ይዤ እጠብቅሃለሁ ፤ አንተነትህን በእኔ ላይ ሣል ። እኔን በእኔ ውስጥ ሲያገኙ የሸሹ ፣ አንተን በእኔ ውስጥ ሲያገኙ ይመጣሉ ። ደስ ላለመሰኘት ከወሰነ ማጉረምረም ፣ መኖርን ከተንገፈገፈ ምሬት ፣ የእብድ ጭምት ከሚያደርግ ማስመሰል ፣ አቅልን ከሚያስት ቍጣ ፣ ሁሉን ከሚያፈርስ ግንፍልተኝነት ፣ ሰውን ከሚያጠለሽ ሐሜት ፣ ራስን ከሚክብ ጉረኝነት አድነኝ ። በሰማይ የምለብሰውን ነጭ ልብስ ዛሬ በቅድስና አልብሰኝ ። በቤትህ እንድትጋብዘኝ በቤቴ እንድጋብዝህ አድለኝ ። አሜን ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 16 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ