መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የሕይወት ሥነ ሥርዓት » የሕይወት ሥነ ሥርዓት 1

የትምህርቱ ርዕስ | የሕይወት ሥነ ሥርዓት 1

…. አለባበስህን ጠብቅ (ሐ)

ልብስን በሚመለከት ሰዎች የተለያየ አመለካከት ይኖራቸዋል ብለን ሁለቱን አይተናል ። ሰዎች ልብስን የሚለብሱት ሦስተኛው ብዙዎች ስለለበሱት ሊሆን ይችላል ። የብዙኃን ድምፅ ያሸንፋልና ለምን? ሳይባል የሚለበሱ ልብሶች አሉ ። የተጣበቀ ጠባብ ልብስ ሁሉ ሰው ስለለበሰው እኛ መልበስ ላያስፈልገን ይችላል ። የፋሽኑ ኢንዱስትሪ ትልቁንም ትንሹንም ወጣት ማስመስል የሚፈልግ ነው ። ሽምግልናም የራሱ ውበት አለው ። የራሱ አለባበስም አለው ። ይልቁንም በዕድሜ ከፍ ያሉ ወጣትነትን አይተውታልና ወጣት ለመምሰል ባይሞክሩ የተሻለ ነው ። ወጣቶች ሽምግልናን አላዩትምና ቢናፍቁት ወግ ነው ።

አራተኛ፡- ብዙዎች ስለማይለብሱት ሊሆን ይችላል ። አንዳንድ ሰዎች ብዙዎች የለበሱትን ይጠሉታል ። ከፋብሪካው በራሳቸው ስም የታተመ ልብስ ያሠራሉ ። ከጀማው ጋር መጋፋት ድሀ መሆን ይመስላቸዋል ። በእውነት ልብስ የሀብት ማሳያ መሆኑ ዕድሜ ለቻይና ጊዜው ያለፈ ሆኗል።

አምስተኛ፡- ለማጭበርበር ሊሆን ይችላል ። ሙሉ ልብስ ለብሰው ፣ ፕሮቶኮላቸውን ጠብቀው ፣ እንግሊዝኛ እያወሩ ፣ ትልልቅ ሀብትን እየተነተኑ የሚዘርፉ ብዙዎች ናቸው ። ለእነዚህ ሰዎች ልጃቸውን መዳር የሚፈልጉ ብዙ ሴት ወይዘሮዎች አሉ ። እነዚህን ማግባት የሚፈልጉ ብዙ ሀብታም ሴቶች ሊኖሩ ይችላሉ ። “እህ ትበል እናትሽ ልብሴን አይታ የዳረችሽ” የሚባለው ታሪክ የደረሰባቸው ሴቶች ብዙ ናቸው ። ውድ መኪኖችን ተከራይተው የሚያጭበረብሩ አያሌ ናቸው ። የትልልቅ ተቋማት መኪኖችን በመያዝ ባለሥልጣን ነኝ እያሉ ሞኞችን ገደል የሚከትቱ የተካኑ ሌቦችን ይህች ከተማ ይዛለች ። ቤቶቹና ፎቆቹ አፍ ቢኖራቸው ብዙ ይናገሩ ነበር ።

ስድስተኛ፡- ከማኅበረሰቡ ላለመለየት መናኛ የሚለብሱ አሉ ። አንዳንድ ሀብትና ሥልጣን ያላቸው ሰዎች “ልብስ ስመርጥ ጊዜ አላጠፋም” ብለው የወደዱትን አንድ ቀለም ያለውን ልብስ ስድስት ይገዛሉ ። ዓመት ሙሉ አንድ ዓይነት ኮት ስለሚለብሱ ልብስ የማይቀይሩ ይመስለናል ። ዛሬ በአንዳንድ ከተሞች የሚታገቱ ሰዎች ለየት ያለ ልብስ የለበሱ ናቸው ። “በሮም ሲኖሩ እንደ ሮማውያን” የሚባለው ለዚህ ነው ። ዓለም ከጉልበት ይልቅ ለጥበብ እጅ ትሰጣለች ። ስንኖር ጠቢብ መሆን መልካም ነው ። የቆዩት ሀብታሞች ብዙ የሚለብሱ አልነበሩም ። በዚህ ምክንያት አንድ ዓይነት ጨርቅ ስለሚለብሱ “ልብሳቸው ላይ አስደግመው ነው” የሚላቸው ብዙ ነበር ።

ሰባተኛ፡- የሥራ ጠባያቸው ስለሚያስገድዳቸው የሚለብሱ አሉ ። የባንክ ፣ የሆቴል ፣ የተለያዩ ተቋማት ሠራተኞች ሙሉ ልብስ እንዲለብሱ ይገደዳሉ ። ባንኮች አንድ ተራ አለባበስ የለበሰ ሠራተኛ ቢያስቀምጡ ኖሮ ማንም አምኖ ገንዘብ አያስቀምጥም ነበር ። ትምህርት ቤቶች የተማሪዎችን አንድ ዓይነት ልብስ መደንገጋቸው ያስመሰግናል ። በቤተ ክርስቲያንም ሁሉም ነጭና ርካሽ ነጠላ ለብሶ ማስቀደሱ ትልቅ ጥበብ ነው ። በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የልብስና የጫማ ውድድር አድክሞአቸዋል ። አስተማሪያቸውም የሚያወራው ልብሱን ከየት አገር እንዳስመጣው ነው ። ድሀ እዚህ መሐል ምን ይሠራል !

ስንለብስ በአቅማቸው አነስ ያሉ ሰዎች ያሉበት ከሆነ እንዳናሳቅቃቸው መጠንቀቅ ያስፈልጋል ። ያላቸውን አጥበውና ለብሰው በመጡበት ስፍራ ደግሞ ዝቅ ያለ አለባበስ ብንለብስ ይሸማቀቃሉ። ስንለብስ አካባቢውንና ሁኔታውን ማገናዘብ አለብን ። የኀዘንና የሰርግ ልብስ መለየት አለብን። ልቅሶ ቤት ነጭ ለብሰን ብንሄድ “የደስ ደስ መጣ” ብለው ይዘምቱብናል ። ጥቁር መልክ ካለን ነጭ መልበስና ቀይ ከሆንን ጥቁርን ብንለብስ የተሻለ ነው ። ልብሳችን ብዙ ዓይነት ቀለም መከተል የለበትም ። ቢያንስ ከሁለት ቀለም ማለፍ የለብንም ። ጫማችን የልብሳችንን አንደኛውን ቀለም ቢከተል መልካም ነው ። የቀለም ምርጫችን በራሱ የውስጣችንን ማንነት ይገልጣል ።

ልብሳችንን ማጠብና መተኮስ ግድ ነው ። ድሀ የሆነው ወታደር ይህንን የሚያደርግ ከሆነ ሌላው ጎበዝ መሆን አለበት ። ስለ ቆሸሸን ሰው ይሸሸናል እንጂ አያዝንልንም ፣ መንፈሳዊ አድርጎም አይመለከተንም ። በትዳር ላይም አንዱ ወገን ንጽሕናውን የማይጠብቅ ከሆነ መራራቅን ይወልዳል ። እስከ ፍቺም እንደሚደርስ ከልምዳችን መናገር እንችላለን ። ትዳር መግባት ገደል መግባት አይደለምና ራስን መጣል ተገቢ አይደለም ። ራሳችሁን ስትጥሉ እንኳን ሌላው ሊወዳችሁ ራሳችሁንም መቀበል ያቅታችኋል ። ውኃን ርካሽ አድርጎ የሰጠን ጌታ ለንጽሕና ብሎ ነው ። የሥራ ልብስ ፣ የስፖርት ልብስ መለየት አለብን ። ልብሳችንን በመልክ በመልኩ ማስቀመጥ በቀላሉ አይቶ ለመልበስ ይረዳናል ። ብዙ ጨርቅ ማብዛትም በሽታ ነው ። ከሁሉ በላይ እኛ ለምናየው ለውስጥ ልብሶቻችን ዋጋ መስጠት አለብን ። አደራ ሙሉ ልብስ ለብሰን ፣ የተቀደደ ካልሲ ማድረግ ራስን መናቅ ነው ። ያየ ሰውም ይንቀናል ። “ውስጡን ለቄስ “ ብሎ ይተርትብናል ። ለውስጥ ልብሶቻችን ንጽሕና ትልቅ ዋጋ መስጠት አለብን ።

ሰማይን በከዋክብት ፣ ምድርን በአበባ ያስጌጠ እግዚአብሔር እኛም በሥርዓት እንድንለብስ ይፈልጋል ! አልባሽ እርሱ ነውና “የዕለት ጉርሴን ፣ የዓመት ልብሴን ስጠን” እንለዋለን ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 5 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም