የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት (13)

10- ሥራህን ተግተህ ሥራ

ሥራ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሰጠው ጸጋ አንዱ ነው ። ሥራ ርግማን ሳይሆን በረከት ነው ። አዳም ሲፈጠር ገነትን እንዲያበጃትና እንዲንከባከባትም ነው (ዘፍ. 2 ፡ 15) ። ደግሞም ምድርን ግዛ ተብሎ ሥልጣን ሲሰጠው ትልቅ ሥራ እንደ ተሰጠው ያሳያል ። ምድር ለእርሱ ስጦታው ናትና እንደ ራሱ ገንዘብ አድርጎ መንከባከብ ይገባዋል ። ከበደል በኋላ ግን “በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ” ተባለ (ዘፍ. 3 ፡ 19) ። ይህ ሥራ ርግማን መሆኑን የሚያሳይ ሳይሆን ከበደል በኋላ አዳም ብዙ ልፋት ጥቂት ትርፍ ይገጥመዋል ማለት ነው ። በዚህም ምክንያት እርካታ እያጣ እንደሚመጣ የሚገልጥ ነው ። እያንዳንዱ ሰው ለሚኖርበት ዓለም የሚያደርገው አስተዋጽኦ አለው ። ሰው የሁለት ዓለም ፍጡር ነውና ለምድር ኑሮው መሥራት ፣ ለሰማዩ ኑሮ ማመን አለበት ። ሥራ በረከት ነው ።

በአእምሮ ላይ የሚነሣውን የሰይጣንን ፈተና ለማሸነፍ ሥራና ጸሎት ሁለቱ መሣሪያ መሆናቸውን አባቶች ተናግረዋል ። ሥራ የፈታ አእምሮ ለሰይጣን መናገሻ ከተማ ነው ። ነገረኛ ሰዎች ሥራ የማይሠሩ ወይም አጉል ትርፍ የሚያገኙ ወገኖች ናቸው ። በሥራ የተጠመደ ነገርን ይሸሻል ። ንጹሕ አእምሮ ለማግኘት ሥራ መሥራት መልካም ነው ። ተነፋፍቆ ለመገናኘት ሥራ አስፈላጊ ነው ። የሰው ልጆች ያለማቋረጥ ከተያዩ ግንኙነቱ ይደፈርሳል ። በዓለም ላይ በተነሣው የቅርቡ ወረርሽኝ ሰው ሁሉ እቤቱ እስረኛ ሁኖ ነበር ። ብዙ ትዳር ፈርሷል ። ብዙ ግንኙነት ተበላሽቷል ። ወንጀሎች ተፈጽመዋል ። ሰዎች ለአእምሮ ጭንቀት ተዳርገዋል ። እስካሁን ድረስም ጠባሳው እያወከ ይገኛል ። ሥራ በረከት ነው ። አሁንም በቤታቸው ተቀምጠው የሚሠሩ ሰዎችን በተለያየ ዓለም እንሰማለን ። የሰይጣን ትልቁ ውጊያው ሰውና ሰው እንዳይገናኝ ማድረግ ነው ። ሥራ ያገናኛል ። ሥራ ከቤታችን ውጭ ሲሆን ለብሰን እንወጣለን ። ለራሳችን እንክብካቤ እናደርጋለን ። ከሰዎች ጋር በማውራት ብቻ ነጻ አእምሮ እናገኛለን ። አአምሮአችን ትልቅ ኃይል የተሸከመ ነውና ማረፊያ ያገኛል ። ማረፊያ ያላገኘ አእምሮ ዓለምን ለማጥፋት አቅም አለው ።

ሥራው አለቃ የሆነለት ሰው ውጤታማ ነው ። ሥራ ብዙ እንቅልፍን የሚጠላ በመሆኑ ሠራተኛ ሰው ማልዶ መነሣት አለበት ። ሥራ አካላዊ ፣ ሥነ ልቡናዊና መንፈሳዊ በረከትን ይሰጣል ። አካላችን የሚጠነክረው በሥራ ነው ። የምድር ተግዳሮትን የሚቋቋሙ ሰዎች ሠራተኛ ሰዎች ናቸው ። የዓለም መንግሥታት ትልቅ ስኬታቸውን የሚለኩት የሥራ ዕድልን በመፍጠራቸው ነው ። በአጭር ቋንቋ እግዚአብሔር ሰነፍ ልጅ የለውምና ሥራን መውደድ ይገባናል ። የሐዋርያው ቃልም ቁርጥ ያለ ነው፡- “ሊሠራ የማይወድ አይብላ ።” (2ተሰ. 3 ፡ 10) ። ስብሰባ ፣ ኮሚቴ ፣ ቃለ ጉባዔ የሚሉ ሰዎች አብዛኛዎቹ ሥራ የማይወዱ ፣ ቁጭ ብለው መነዛነዝ የሚያፈቅሩ ናቸው ። ሕይወትን ቀለል አድርጎ መኖር የሚቻለው በስብሰባ ሳይሆን በሥራ ነው ። ጨካኝ መንግሥታት ሕዝባቸውን በስብሰባ ያደነዝዛሉ ። መሪ የሆኑት ደግሞ ሕዝባቸውን ለሥራ ያነሣሣሉ ። ሕዝብን በሥራ መወጠር ከሁከትም ይጋርዳል ።

አዎ ሥራህን በታማኝነት ሥራ ። ጸልየህ ያገኘኸውን ሥራ በትጋት አለመሥራት እግዚአብሔርን ማሳዘን ነው ። ሥራ ታማኝነትና ትጋት ይፈልጋል ። ታማኝነቱ ትጋት ከሌለው ፣ ትጋቱ ታማኝነት ከሌለው አደገኛ ነው ። ሥራህ የሃይማኖትህ ቦታ አይደለም ። በሥራህ ቦታ ሥነ ምግባርን እንጂ አምልኮን ልፈጽም አትበል ። ጉቦን ተጸየፍ ። ደመወዝህ እንዲባረክ ጸልይ ። ጉቦ ያለህንም ይዞት የሚሄድ ፣ ልጆችህንም የሚያሳብድ ነው ። ጉበኞች የብዙዎችን እንባና ደም ተሸክመው ይሄዳሉ ። ሰው ወዶና ፈቅዶ እንጂ ተጨንቆ የሚሰጠን ነገር ርግማን የሚያመጣ ነው ። የሥራ ሰዓትህን አክብር ። ደመወዝህ አነስተኛ በመሆኑ ባለጉዳዩን ማንገላታት አይገባህም ። ባለጉዳይህን ፣ ያንተን ሙያ የሚፈልገውን እግዚአብሔርን እንደምታገለግል አድርገህ አገልግለው ። የሙያህ ባለቤት እግዚአብሔር ነው ። በሙያህ ሰውን አታጉላላ ። አንድ ቀን ይህ አእምሮህ ላይሠራ ይችላል ። እጆችህ ላይሠሩ ይችላሉ ። በሚያልፈው አካልህ የማያልፍ ሥራ ሥራበት ። በሙያ ሰውን ማስደሰት መታደል ነው ። ካንተ የሆነ ምንም ነገር የለም ።

ሥራ የምትሠራው አሥራትህንም ለማውጣት ነው ። ባንተ የሥራ ትርፍ የእግዚአብሔር ቤት ይገነባል ። ብዙዎች ወንጌል ይሰማሉ ። ልጆችህ ጠግበው ያድራሉ ። ትዳርህ አይታወክም ። የብዙ ትዳር ሁከትም የገቢ ማነስ ነው ። ሥራ ትልቅና ትንሽ የለውም ። በምድር ላይ የሚያሳፍረው ቆሻሻ መጥረግ ሳይሆን ቆሻሻ ጠባይ መያዝ ነው ። ጌታችን ለእኛ አርአያ ለመሆን አናጢነትን ሠርቷል ። ቅዱሳን ሁሉ ሥራቸውን በትጋት ሲሠሩ ለሰማያዊ ግዳጅ የተጠሩ ናቸው ። ትጉ ሠራተኛ ትጉህ ሐዋርያ ሊሆን ይጠራል ። ትጋት ተወዳጅ ያደርጋል ። ለክብር ለመታጨት ያበቃል ።

እግዚአብሔር የእጅህን ሥራ ይባርክ !

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 12 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ