የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት (14)

11- ቀጠሮ አክብር

እግዚአብሔር አምላክ ቀጠሮን በማክበር የታወቀ አምላክ ነው ። የ5550 ዘመንን ቀጠሮ ያከበረ ብቸኛ አምላክ ነው ። ሐዋርያው ይህን ሲገልጥ እንዲህ ብሏል፦ “ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤” (ገላ. 4 ፡ 4) ።
እግዚአብሔር በቀጠሮው ማርፈድ ወይም መዘግየት አያውቅም ። ይህንንም ነቢዩ እንዲህ ሲል ገልጧል፡- “ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፥ ወደ ፍጻሜውም ይቸኵላል፥ እርሱም አይዋሽም ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው እርሱ አይዘገይም ።” (ዕን. 2 ፡ 3) ።

ይህች ዓለም በእግዚአብሔር ቀጠሮ ተይዛ ያለች ዓለም ናት ። 5500 ዘመን የድኅነት ቀጠሮ ነበራት ። ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት የሚመጣውን ንጉሥ እየጠበቀች ነው ። የዚህች ዓለም ትልቁ እንግዳ የመጣውና የሚመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። እርሱ ከእኛ ሳይለይ እመጣለሁ ያለ ፣ መንበሩን ሳይተው በበረት የተወለደ ነው ። በኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ መቼ እንደሚመጣ ፣ መቼ እንደሚቆም ተናግሮ ፣ የተናገረውንም የፈጸመ አምላክ ነው።

አምልኮተ እግዚአብሔር ታላቅ ቀጠሮ ነው ። ከእግዚአብሔር ጋር ከመገናኘት የበለጠ ቀጠሮ የለምና ። በብሉይ ኪዳን በመገናኛው ድንኳን የጠዋትና የማታ መሥዋዕት በጊዜው ይቀርባል ። የሳምንትና የዓመት አገልግሎትም ከቀጠሮ ሰዓቱ ዝንፍ አይልም ። በዓላት የሰውና የእግዚአብሔር ቀጠሮ ናቸው ። ወላጅ ለበዓል ልጆቹን እንደሚጠበቅ እግዚአብሔርም በሰንበትና በበዓላት ልጆቹን ይጠብቃል ። በዓላት የቤተሰብ ፍቅርን እንደሚጠብቁ ፣ መንፈሳዊ በዓላትም ሃይማኖትን በሰዎች ልብ ትኩስ ያደርጋሉ ። የተደመሰሱ አብያተ ክርስቲያናት አንዱ ችግራቸው በዓላት የሌላቸው መሆኑ ነው ። ደግሞም በዓላት የአንድ ሕዝብ የነጻነት ምልክት ናቸው ።

ተፈጥሮ እግዚአብሔር የሰጠውን ቀጠሮ ያከብራል ። ተፈጥሮ በራሱ ቸር አይደለም ። አንዳንድ ሰዎች የተፈጥሮ ችሮታ እያሉ ያወራሉ ። በተፈጥሮ በኩል የቸርነት እጁን የሚገልጥ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ተፈጥሮ ራሱን የሚመራ ሳይሆን ፈጥሮ የሚያስተዳድር አምላክ አለ ። ይህ ሁሉ አስደናቂ ተፈጥሮ የታላቅ ፍንዳታ ውጤት አይደለም ። ታላቅ ፍንዳታ ይህን ውበት ከሰጠ ፣ ትንንሽ ፍንዳታ ያለባቸው የኢራቅና የጋዛ ከተሞች ውብ በሆኑ ነበር ። ተፈጥሮ ለእግዚአብሔር ቀጠሮ የተገዛ ነው ። ሌሊትና ቀኑ ክረምትና በጋው በሰዓቱ ይመጣሉ ። የመስቀል ወፍ ፣ አደይ አበባ በሰዓቱ ሲመጡ ሰው እንዴት ቀጠሮ የሚስት ይሆናል ?

ቀጠሮን አክብር ። ይበልጥ ለአምልኮተ እግዚአብሔር ወደ ቤተ ክርስቲያን የምትሄድበትን ቀጠሮ አክብር ። ምነው ከአምልኮተ እግዚአብሔር ውጭ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይኬዳል ወይ ? አዎ ጓደኛ ለማግኘት ፣ የወደዳት ልጅ ሰላም ማደሯን ለማረጋገጥ የሚሄዱ አሉ ። ለረብሻ ፣ ለፖለቲካ የሚሄዱ አሉ ። የዘር ዕድር ለመጠጣት ፣ የስለላ ተግባራቸውን ለማከናወን የሚሄዱ አሉ ። እግዚአብሔር ቤት ለመሄድ የምናረፍደው የሚመለከተንና የማይመለከተን አምልኮ ያለ ስለሚመስለን ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ሰው ጸሎቱ እንዳለቀ ስብከት ላይ መድረስ ይፈልጋል ። ሁሉም ግን ለእግዚአብሔር ክብር ፣ ለሰው ጥቅም የሚደረግ አገልግሎት ነው ።

ቀጠሮን በሚመለከት ራሳችንን የረገምን ሕዝቦች ነን ። “የሀበሻ ቀጠሮ” እንላለን ። የሚገርመው ያረፈደው ሰውዬ ሳይቀር “ያው የሀበሻ ቀጠሮ አይደል” ይላል ። ቀጠሮ የሰውነት እንጂ የሀበሻና የፈረንጅ መለኪያ አይደለም ። ወላጆቻችን ቀጠሮ በጣም ያከብሩ ነበር ። ጠዋት ቀጠሮ ካላቸው እንቅልፍ አይተኙም ነበር ። ባለፈው ዘመን ከሰዓቱ በፊት የሚደርስ ትውልድ ነበረ ፣ በመካከሉ አርፍዶ የሚደርስ ትውልድ ተፈጠረ ። አሁን ደግሞ አርፍዶ የሚቀር ትውልድ እየመጣ ነው ። የሚገርመው የቀጠርነው ሰው ሲቀር እንደ መገላገል እየቆጠርን መምጣታችን ነው ። በአሁን ዘመን ቅሬታም እያለቀ ነው ። ቀጠሮ ለራስና ለሰው ያለን ክብር መግለጫ ነው ።

ቀጠሮን ለማክበር መርሳትንም ለማሸነፍ የሚረዱን ነገሮች፦

የማንችል ከሆነ ቀጠሮ መያዝ አይገባንም። ቀጠሮው ከተሰረዘም ቀደም ብለን ማሳወቅ ይገባናል ። ሰውን ቀጥሮ ስልክ ማጥፋት ነውር ነው ። ነጻ ፍጡር ነንና መገኘት ካልፈለግን ቀድመን ማሳወቅ ይገባናል ። በማስታወሻችን ላይ ቀጠሮአችንን ማስፈር ተገቢ ነው ። ማስታወሻውን በሚታይ ቦታ ላይ ማስቀመጥ መልካም ነው ። የመንገድን ሁኔታ ታሳቢ አድርገን ቀድመን መውጣት አስፈላጊ ነው ። የማይካስ የሰውን ጊዜ እንዳንበላ መጠንቀቅ ይገባናል ። ከቤተሰብ ጋር ከሆነ ወደ ቀጠሮ ቦታችን የምንሄደው ፣ ሕፃናት ሊያስረፍዱ ይችላሉና ቀድመን ማዘጋጀት አለብን ። ልጆች ካሉ ሴቶች ጫና ስለሚበዛባቸው “ቶሎ በይ” ከማለት ማገዝ የተሻለ ነው ። የሚገርመው ሙሽራ ማርፈድን እንደ ክብር የሚቆጥርበት አገር መሥርተናል ። እድምተኛ እየበላ ሙሽራን መጠበቅ የቅርብ ጊዜ ልማድ ነበር ። አሁን ግን አትብሉም ፣ ቶሎ አልመጣምም የሚል ሙሽራ አፍርተናል ። ይህ የትውልዱ መውደቅ ምልክት ነው ።

በቀጠሮአችን መሠረት ስንገናኝም የምንነጋገርበትን ርእስ መያዝ ከመጋጨትና ከመሰለቻቸት ይጠብቀናል። ስንገናኝ ጥሩና ሞቅ ያለ ሰላምታ መለዋወጥ ፣ ስናወራ ዓይን ለዓይን ተያይተን ማውራት ፣ የአክብሮትን ቃላት መጠቀም መልካም ነው ። ስንለያይ በስስት ለቀጣይ ግንኙነት በር በመክፈት መሆን ይገባዋል ። ቀጠሮ ማክበር የትልቅነት መለኪያ ነው ። ሰዎችን ስንቀጥር ከአቅም በላይ በሆነ ጉዳይ ሊቀሩ ይችላሉና መቀየም አይገባንም ። ሰዎችን ስንቀጥር የሚነበብ መጽሐፉ መያዝ ጥሩ ነው ። ቢያረፍዱ ደግሞም ቢቀሩ ጊዜውን መጠቀም እንችላለን ። ጊዜ ክቡር ነውና ቀጠሮ አክብሩ!

እግዚአብሔር ዘመናችሁን ይባርክ !

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 15 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ