መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የሕይወት ሥነ ሥርዓት » የሕይወት ሥነ ሥርዓት (17)

የትምህርቱ ርዕስ | የሕይወት ሥነ ሥርዓት (17)

13. ንግግርህ ብቁ ይሁን (ለ)

1. አዳምጥ

ጥሩ ተናጋሪ ጥሩ አድማጭ ፣ ጥሩ ፀሐፊ ጥሩ አንባቢ ነው ። ሰውዬው ራሱን በልቶት እግሩን ብታክለት ከማስደሰት ይልቅ ታሳምመዋለህ ። ሳያዳምጡ መናገርም እንዲሁ ነው ። ማዳመጥ ሰዎችን ለመረዳትና ለመርዳት ጥልቅ ፍላጎት ማሳየት ነው ። ያልተረዳኸውን ሰው መርዳት አትችልም ። ሰዎች ከእርዳታ ይልቅ አሳባቸውን የሚረዳላቸው/የሚያውቅላቸው ሰው ይፈልጋሉ ። ብዙ ሰው ከአእምሮ ሕመሙ የሚድነው ስታዳምጠው ነው ። አዳምጠህ ስትናገር ርእስ ትጠብቃለህ ፣ ያንን ሰው ትማርከዋለህ ። ደግሞም የመጨረሻው ይጸናልና ኋላ መናገር መልካም ነው ።

2. ንግግር አታቋርጥ

ሰው አሳቡን መጨረስ አለበት ። ምንም ቢናገር ዓመት አያወራም ። ስለዚህ ንግግሩን አስጨርሰው ። አሳቡ እንዳይጠፋህ ማስታወሻ ያዝ ። የሰው ልጅ አስተማማኝ ሰላም እንዳለው ምልክቱ ታግሦ መስማት ሲችል ነው ። ለአንድ ሰዓት ስብከት የሚሰሙ ሰዎች አንድ ነገር አላቸው ። እርሱም የውስጥ ሰላም ነው ። እግዚአብሔርን የሚያህል ትልቅ አምላክ የሚሰማው ነውና ሰውን ለማዳመጥ አትፈተን ። የተጨነቁ ሰዎች ትልቁ ችግራቸው የሚሰማቸው ሰው ማጣት ነው ። በትክክል እንደ ሰማሃቸው ካወቁ ምንም ምክር ሳትሰጣቸው ይፈወሳሉ ። ማዳመጥም አገልግሎት ነው ። ጆሮውን ላልነፈገን ጌታ ውለታው የተጨነቁትን መስማት ነው ።

3. በአሉታዊ ንግግር አትጀምር

ሰዎችን ከጉድለታቸው ተነሥተህ ስታወራቸው ዋጋ የላችሁም እያልካቸው ይመስላቸዋል ። ዋጋ የለህም ያልከው ዋጋህን ያሳጣሃል ። እግዚአብሔር ሲናገር ሁልጊዜ ከመልካሙ ጀምሮ ነው ። ሙሴን አንተ ገዳይ አላለውም ፣ ነጻ አውጪ አለው ። ጌዴዎን የፈሪዎች ሊቀ መንበር ቢሆንም አንተ ጎበዝ አለው ። የሞተውን የናይን መበለት ልጅ አንተ ሬሳ ሳይሆን “አንተ ጎበዝ” አለው ። ሬሳን “አንተ ጎበዝ” የሚል የእኔ መድኃኔ ዓለም ብቻ ነው ። ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መልእክት ሲላክ ካላቸው ጥሩ ነገር ተነሥቶ የሌላቸውን ይናገራቸዋል (ዘጸ. 3 ፡ 10 ፤ መሳ. 6 ፡ 12 ፤ ሉቃ. 7 ፡ 14 ፤ ራእ. 2 ፡ 2-7) ። በንግግር መነሻ ላይ ከጉድለት መጀመር ግንኙነትን በዜሮ ማባዛት ነው ። ሰዎች የሚጠሉት ዋጋ የላችሁም የሚል ድምፅን ነው ። የምትነቅፋቸው ሊያጠፉህ ይችላሉና ተጠንቀቅ ። ከትዳር አጋር ጋር የማትግባቡት ከጉድለት ስለምትጀምሩ ነው ። ሰይጣን በወኪል ሳይሆን በቀጥታ የሚዋጋህ “ዋጋ የለህም” በሚል ድምፅ ነው ። ሰው ራሱን የሚያጠፋው የራሱ ዋጋ ሲወርድበት ነው ። “ብኖርም ብሞትም የምጠቅምና የማጎዳ ሰው አይደለሁም” ሲል በራሱ ላይ ይጨክናል ።
ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም