የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት 2

1- በማለዳ ተነሣ

በማለዳ ስትነሣ ቀኑ ይረዝምልሃል ። በጉልበት የምትሠራው እስከ ረፋድ አምስት ሰዓት ድረስ ሊሆን ይችላልና በማለዳ ተነሣ ። በማለዳ ስትነሣ ጨለማና ብርሃን ባንተ ላይ ጦርነት ስለማያካሂዱ አቅም ይኖርሃል ። ጨለማና ብርሃን ሲታገሉ በመኝታ ውስጥ ከሆንህ ጉልበትህ ይሰበራል ። ደግሞም ወፎች የሚዘምሩት አንተን ለመቀበል ፣ ለምስጋና ለመቀስቀስ ነው ። ላንተ ማንጋትን ያልረሳውን እግዚአብሔር ማልደህ አመስግነው ። መኝታ አስፈላጊ የሆነውን ያህል ከበዛም አካልን የሚያደቅቅ ፣ ሞራልን የሚነካ ነው ። “ሥራ የለኝምና በማለዳ መነሣት አልፈልግም” አትበል ። እግዚአብሔርን ከማምለክ የበለጠ ሥራ የለም ። ደግሞም ከራስ ፀጉራችን እስከ እግር ጥፍራችን ራሳችን ለራሳችን ሥራ ነን ። ፀጉርህ መበጠር ፣ ፊትህ መታጠብ ፣ ጥርስህ መቦረሽ.. ያስፈልገዋል ። ራስህ ለራስህ ሥራ ነህ ።

አንተ በማለዳ ትመጣለህ ብላ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ደጇን ከፍታለች ። የሰማይ አደባባይም መዝጊያ የለውም ። እግዚአብሔርም የሥራ ሰዓት የሌለው ንጉሥ ነው ። ሁልጊዜ በሥራ ላይ ነው ። ከንጉሥ ጋር ከመነጋገር የበለጠ ተግባር ፣ ከመጸለይ የበለጠ የነፍስ ትርፍ የለም ። በማለዳ ተነሣ ። ማለዳ የልጅነት ዘመን መጠሪያ ነው ። ማለዳ ልጅ የምትሆንበት ክፍለ ጊዜ ነው ።

ቀኑን የሚያልቀው ማለዳ ላይ ነውና የሰው ድምፅ ሳትሰማ የእግዚአብሔርን ድምፅ ስማ ። ዜና ሳታነብ ዜና ሥላሴ የሆነውን ወንጌል አንብብ ። ቀን ላይ የምታገኘው ሰው የሚወድህ ፊትህን ስለታጠብህ ፣ ጥርስህን ስለቦረሽህ ፣ ሽቱ ስላርከፈከፍህ ፣ ሱፍ ስለለበስህ ሊሆን ይችላል ። ባልታጠበ ፊትህ ፣ በተራቆተ ማንነትህ የሚቀበልህን አምላክ በማለዳ አነጋግር ። በማለዳ ለመነሣት የሚያግዝህ በጊዜ መተኛት ነው ። እንቅልፍህን ሊጋፉ የሚችሉ ስልኮችና ሰው ሠራሽ ዕይታዎችን በጊዜ አቁም ። የምግብ ሰዓትህን ካላከበርህ ብትበላም እንደምትታመም ፣ የእንቅልፍ ሰዓትህን አለማክበርህ ብትተኛም ጤነኛ አያደርግህም ። በማለዳ ተነሣ ። ይህች ቀን ከዛሬ በፊት አይተሃት አታውቅምና አዲስ ቀን ናት ። ፀሐይ በምሥራቅ ስትወጣ ይህን ውበት ለማድነቅ በጠዋት ተነሣ ። የማለዳ ጸሎት አለና ያንን ለማድረስ በጠዋት ተነሣ ። እንቅልፍ የሞት ፣ መንቃትም የትንሣኤ ምልክት ነውና በማለዳ ተነሣ ።

ቅዱሳን አባቶች ሁሉ በማለዳ የሚነቁ ነበሩ ። በዓለም ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጡ ሰዎች የማለዳ ሰዎች ናቸው ። ከእንቅልፍ ለመነሣት ስንፍና ሲጫጫንህ ድሀ ለመሆን ወስነሃል ማለት ነው ። ደግሞም ሌሊቱን በሙሉ ሲያመሰግኑ ያደሩ ካህናትን አስታውስና በማለዳ ተነሣ ። ሌሊት በሙሉ ሲጠብቁ ያደሩ ሠራዊትን አስብና በማለዳ ተነሣ ። ሌሊት በሙሉ ሲጓዙ ያደሩ ፣ ሲያመርቱ ያነጉ መንገደኞችና ሠራተኞችን አስብና በማለዳ ተነሣ ። ይህች ቀን አይተሃት የማታውቃት ብቻ ሳትሆን ላትደገም የምታልፍ ቀን ናት ። ስለዚህ ቀኑን ዋልበት እንጂ አይዋልብህ ። በማለዳ ተነሣ ብዙ ትርፍ ታገኛለህ ። ሱሰኞች ማለዳቸውን ይበላሉ ። በጉልበት ለመነሣት ይቸገራሉ ። ማለዳን ክፉ ባልንጀርነቶች ያበላሹታል ። ማለዳህ እንደ ማታህ ነውና በጊዜ ተሰብሰብ ፣ በጊዜ ንቃ ! ዶሮ ራሱ ሳይነቃ ሌላውን አያነቃምና የበታች ሠራተኞችህን ለማበረታታት በማለዳ ተነሣ ።

እግዚአብሔር ያግዘን

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ