13. ንግግርህ ብቁ ይሁን (ረ)
10. ድምፅህን መጥን
ሰው ከሰው ከሚለይበት ስጦታው አንዱ ድምፁ ነው ። እግዚአብሔር አምላክ ዓይነ ሥውሮችን ጆሮአቸውን በጣም ንቁ አድርጎላቸዋል ። ሰውን የሚለዩት በድምፁ ነው ። ድምፅ መለያችን ነው ። የአንዳንድ ሰው ድምፁ በራሱ ሰላም ይሰጣል ። “ምነው ሰላም ባለኝ” የሚባሉ ፣ በድምፃቸው ፍቅርን ፣ በተግባራቸው ርኅራኄን የሚያስተላልፉ ልዑካነ ክርስቶስ የሆኑ ሰዎች አሉ ። ስለ እነርሱ እግዚአብሔር ይመስገን !! ንግግርን ውብ ከሚያደርጉ ነገሮች አንዱ ድምፅን መመጠን ነው ። ድምፅ ከመጠን በላይ ሆኖ እንዳይጮህ ፣ አንሶ ለመደመጥ እንዳያስቸግር መመጠን ይገባል ። በድምፃቸው ግርማዊ ለመሆን የሚጮኹ አሉ ። እንደ አንበሳ በመጮኽ አንበሳ መሆን እንደማይቻል ሁሉ በድምፅም ንጉሥ አከል መሆን አይቻልም ። ይልቁንም በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ወፍራም ድምፅ ሐኪም ያዘዘላት እስኪመስል ሰባኪ ሁሉ ድምፁን ባለ ገበር ማድረጉ መደረቡ እጅግ ይገርማል ። ራስን መሆን ረጅም ርቀት ያራምዳል ። እንደ ሌላው ሰው ለመሆን መሞከር ራስን የማጥፋት ጭካኔ ነው ። ከሰው የምንወስደው ነገር አለ ፣ ራሳችን የሆነው ነገር ደግሞ አለ ። ቢኮረጅም ወፍራም ድምፅ ሳይሆን ወፍራም ምግባር መኮረጅ አለበት ። አንዳንድ ቤተ እምነት ውስጥ ያሉ ሴት ሰባኪዎች በወንድ ድምፅ ሲሰብኩና ሲጸልዩ ይሰማሉ ። የመጀመሪያው ሴቶች እንዲሰብኩ መጽሐፍ አልፈቀደም ፣ በሁለተኛ ደረጃ የወንድን ድምፅ ማስመሰል ሴት አድርጎ የፈጠረውን እግዚአብሔር አለማክበር ነው ።
በትዳራቸውና በልጆቻቸው ላይ እንደ ጥይት የሚባርቁ ፣ የሰው ቀልብ ሲገፈፍ ትልቅ የሆኑ የሚመስላቸው ከንቱ ሰዎች አሉ ። ደግሞም ቅስስ ማለትን አሳዛኝ ለመምሰል የሚጠቀሙበት ሰዎች ይኖራሉ ። ቅስስ ማለት መንፈሳዊነት ፣ መባረቅ እውነተኛነት መስሎአቸው ተታለው የሚያታልሉ ብዙዎች ናቸው ። ሰባኪዎች ከመጠን በላይ በመጮኽ የሰበኩ ከመሰላቸው ተሳስተዋል ። መብረቅም በጣም ይጮኻል ፣ መልእክት የለውም እንጂ ። ድምፅ ማጉያ የተሠራው ለጉሮሮአችን ጤንነት ነው ። ድምፅ ማጉያውን ሥራ ፈት የሚያደርጉ ፣ በድምፅ ማጉያ ላይ የሚጮኹ አያሌ ወገኖች አሉ ። ዕድሜ ብቻ ሳይሆን በሽታም ሊያሰክናቸው ይችላልና ጥንቃቄ ቢያደርጉ መልካም ነው ። የሰባኪ መለያው የሻከረ ድምፅ መስሎአቸው ትኩስ ልቅሶ ላይ እንደዋለ ያንን የሻከረ ድምፅ እንደ ክብር ሲያሰሙ የሚውሉ አያሌ ናቸው ። መስፈርት ካጣ ዘመን ያድነን ከማለት ውጭ ምንም አይባልም ። አንተ ግን ድምፅህን መጥን ። ቀሰስተኛም ፣ ባራቂም አትሁን።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 3 ቀን 2016 ዓ.ም.