የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት (22)

13. ንግግርህ ብቁ ይሁን (ሰ)

12. መደምደሚያህ ተስፋ የሚሰጥ ይሁን

ይህ ዓለም ንጋትና ምሽት የሚፈራረቁበት ዓለም ነው ። ንጋቱን ምሽት ፣ ምሽቱን ንጋት ይከተለዋል ። ወጥ ጨለማ ወጥ ብርሃን በዓለም ላይ የለም ። ያለፈውን ለማመስገን የአሁኑ ጨለማ ፣ የሚመጣውን ተስፋ ለማድረግ ወጋገኑ አስተዋጽዖ ያደርጋል ። ንግግራችንም ከዓለም ወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታ ይነሣል ። የመለኮት ሥልጣንን በማሰብ ይዋባል ። በሰው ብንጀምርም በእግዚአብሔር አሳብ መቋጨት ንግግርን ወዝ ያለው ያደርገዋል ። ብዙ ዜናዎች ፣ ብዙ ግላዊና ማኅበራዊ ችግሮች በንግግር ይገለጣሉ ። ንግግር መተንፈስ ነው ። ሰው ካልተነፈሰ እንደማይኖር ነባቢ/ተናጋሪ ሁኖ የተፈጠረው ሰውም ሳይናገር መኖር አይችልም ። በመናገር ብቻ የሚድን ብዙ ሥነ ልቡናዊ ሕመም አለ ። ቃል የልብ መልእክተኛ ነውና በውስጣችን የታመቀውን ነገር መናገራችን ትክክል ነው ። መደምደሚያው ግን ተስፋ የሚሰጥ መሆን አለበት ። ተናጋሪ ሁነን ብንፈጠርም ሁሉን እንድንናገር ግን አልተፈቀደልንም ። “ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል” እንዲሉ ። ሆድ ብዙ ቆሻሻ ነገር ተሸክሞ የሚኖር ቻይ ነው ።

ምንጊዜም መጨረሻው መልካም ነው ። የዓመት ፍዳ መጨረሻ ዓመተ ምሕረት ነበር ። የአሁኑ ዘመን መከራ ማብቂያውም የጌታችን መምጣት ነው ። መጨረሻው መልካም ነው ። ከሌሊት ቀጥሎ ሌሊት አይመጣም ። እንደ ሰው ብናዝንም እንደ አማኝ በሚያጽናና የተስፋ ቃል ንግግራችንን መፈጸም አለብን ። ሰዎች የመጨረሻውን ይዘው ይሄዳሉና በጉልበት ይሰማራሉ። የዚህ ዓለም ወሳኞች ገዥዎች ወይም ግፈኞች አይደሉም ። በዕጣ ፈንታ ያልመጣ ዓለም ለዕጣ ፈንታ የተተወ አይደለም ። የመጨረሻው ዳኛ ክርስቶስ ነውና መጽናናት ይገባል ። የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ ቢታሰር ተፈታ ፣ አልዓዛር ቢሞት ተነሣ ። ሞት እንደ መጨረሻችን አይደለም ። የትንሣኤ ሕዝቦች ነን ። ደስ ይበለን ። ምንጊዜም ተስፋ ሰጥተን ንግግርን መፈጸም ተወዳጅ ያደርገናል ። ይህ ማለት እንደ ዘመኑ አማኝ ነን ባዮች የሚያመውን ሰው አላመመኝም በል ፤ ያመኛል ብለህ ስለምታስብ ነው እንጂ አላመመህም እንበል ማለታችን አይደለም ። እነዚህ ወገኖች ይህን ድህ ሕዝብ ለማደንዘዝ በበለጠጉት አገራት የተላኩ መርፌዎች ናቸው ።

ብዙ የተስፋ ቃላትን እናስታውስ ። እግዚአብሔር በጊዜው ይደርሳል ። ተስፋ ከሌለን አልተቀበርንም እንጂ ሞተናል ማለት ነው ። የምናመልከው አምላክ ሁሉን ይለውጣል ። ሳይለወጥ ሁሉን የሚለውጥ አምላክ አለና በርቱ ! ተጓዙ።

13. ጎሣ ጠቅሰህ አታውራ

አንዱ ጎሣ ወይም ነገድ ምናልባት 40 ሚሊየን ሕዝብ ሊሆን ይችላል ። ሌላው ሰባት ሚሊየን ይደርሳል ። አንድ መስመር በማትሞላ ንግግር አርባ ሚሊየን ጠላት ማትረፍ አላዋቂነት ነው ። እግዚአብሔር ትንሽ ወገን አልፈጠረም ። ሁሉም የሰው ልጅ በፊቱ ክቡር ነው ። ሰውን መናቅም እግዚአብሔርን መናቅ ነው ። በዓለም ላይ የብዙ እልቂቶች መነሻ መናናቅ ነው ። አንዱ ራሱን እንደ ወርቅ ያያል ። ማየቱ ክፉ አልነበረም ። ሌላውን እንደ ጉድፍ በመመልከቱ የማጽዳት ዘመቻ ይጀምራል ። በዚህ ምክንያት የጋራ ዓለም በጋራ ካልሆነ አይቆምምና መፈራረስ እንጀምራለን ። የሰው ልጅ ወራጁ ቢለያይም/ቢበዛም ምንጩ ግን አንድ አዳም ነው ። የሠራውም አንድ አምላክ ነው ። የአንድ አምላክ ፍጡር ፣ የአንድ አዳም ልጅ መለያየት አይገባውም ። በንግግራችን ብዙ ምሳሌዎቻችን ፣ ብዙ ጥቅሶቻችን ጎሣ ተኮር ሊሆኑ ይችላሉ ። ይህ መልካም አይደለም ። ፈጽመን ልናጠራው ይገባል ። የናቅነው ወገን ነገ በአናታችን ላይ ይመጣል ። የሰው ልጅ ሁልጊዜም በእንቅስቃሴ ላይ ነው ።

ነጮች ብንል ጥቁሮች ሁሉም ጋ ያለው አንድ የሰው ጠባይ ነው ። የሰው ልጅ በኃጢአት የወደቀውን አዳምን ወይም የጽቃችን ንጉሥ ክርስቶስን ይመስላል ። በዓለም ላይ ተከሥቶ የነበረውን ኮቪድ 19 የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው ። በዚህ በሽታ እንስሳት ጉዳት አልደረሰባቸውም ። ሁሉም የሰው ልጅ ግን ቍስሉንም ጠባሳውንም ተሸክሟል ። የሚያጠቃን በሽታ እንኳ ተመሳሳይ ነው ። ነጩ የበላውን ምግብ ጥቁሩ በድፍረት ይበላል ። ምክንያቱም የተፈጥሮ ዘመዱ ስለሆነ እንደማይጎዳው ያውቃል ። በሽታ በአንድነት የሚያውቀንን እኛ ግን በአንድነት መተዋወቅ አልቻልንም ። ሰይጣን አንድ ናቸው ብሎ ሲያጠቃን እግዚአብሔር ግን በአንድነት አያውቀንም ። ንግግራችን በምንም መንገድ ጎሣ ተኮር ባይሆን መልካም ነው ። ይልቁንም በዚህ ዘመን ሰው በጎሣው እንጂ በአእምሮው እያሰበ አይደለም ። ለመጋደል በመጠባበቅ ላይ ያለበት ዘመን ነውና የንግግራችን ማጠንጠኛ ሰው የሚለው የወል መጠሪያ ሊሆን ይገባዋል ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ