የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት (25)

13. ንግግርህ ብቁ ይሁን (በ)

20. ኃይለ ቃል አትጠቀም

“እፍ ያነዳል ፣ እፍ ያጠፋል” ይባላል ። እሳቱን የምናቀጣጥለው እፍ በማለት ሲሆን የምናጠፋውም እፍ በማለት ነው ። ንግግር የተኛውን በሬ ቀስቅሶ አውሬ ያደርገዋል ፣ በተቃራኒው ንግግር የተመዘዘ ሰይፍን ወደ አፎቱ ይመልሳል ። ናባል ያነደደውን እሳት ፣ አቢግያ አጠፋችው (1ሳሙ. 25)። እፍ ያነደደውን እፍ ባያጠፋው ኖሮ ዳዊት የብዙ ንጹሐንን ደም ያፈስስ ነበር ። አቢግያን የመሰለች የኋላ ሚስቱንም ይገድል ነበር ። ባለጌዎች የሚኖሩት እጅግ መልካም በሆኑ ሰዎች መካከል ነው ። ባለጌውን ላጥፋ ስንል ብዙ መልካሞችን እናጠፋለን ። አንዳንዴ ስለምጣዱ አይጧ ትለፍ ትክክለኛ መርሕ ይሆናል ፤ ባለጌዎች ይህን ስለሚያውቁ ጨዋውን ወገን ይጠጋሉ ። ጨዋ ሰውን የሚያስተዋውቀን ባለጌ ነው ። ባለጌ እንኳ የሚፈራው ባለጌን ነው ። ባለጌው ስለሚያውቅበት ፣ ከእርሱ የባሰ ክፉ ምላሽ ስለሚሰጠው ባለጌ ባለጌን ይሸሻል ። እጅግ ነውረኛ የሚባሉ ሰዎች የሚያገቡት ሚስት በጣም መልካም ሴትን ነው ። ጨካኝ ነገሥታት ሚስቶቻቸው ጸሎተኛ ፣ ግፍን የሚፈሩ ነበሩ ። ናባል እፍ ብሎ ያነደደውም አቢግያ ባታጠፋው ኖሮ የዳዊት የወደፊት ዘመኑ በጸጸት የተሞላ ይሆን ነበር ። ናባልና አቢግያ ባልና ሚስት ነበሩ ። እሳትና ውኃ አንድ ላይ አደሩ ። እስከ ዕለተ ሞቱ የአቢግያ ጠባይ ናባልን አለወጠውም ፣ እስከ ዕለተ ሞትዋ የናባል ጠባይ አቢግያን አለወጣትም ። እንደ ውኃና ዘይት ሳይዋሐዱ አብረው የኖሩ ነበሩ ።

ባልና ሚስት ብዙ ጊዜ በሥጋ ይዋሐዳል ፤ በነፍስና በመንፈስ ግን ሳይዋሐዱ እስከ ዕለተ ሞት ይዘልቃሉ ፣ ግማሽ ጋብቻ ማለት ይህ ነው ። የሥጋ ውሕደት የባልና የሚስት ነው ። ይህ ከባልና ሚስት ውጭ ለማንም አይፈቀድም ። የነፍስ ተዋሕዶ የአሳብ መግባባት ፣ የመንፈስ ተዋሕዶ በአምልኮተ እግዚአብሔር አንድ መሆን ነው ። ይህ የነፍስና የመንፈስ አንድነት ከሰው ዘር ሁሉ ጋር ሊሆን የሚገባው ነው ። የሰሎሞን ልጅ ሮብዓም ለእስራኤል መከፋፈል ምክንያት የሆነው በኃይለኛ ንግግሩ ነው (1ነገሥ. 12)። ሕዝቡን በእውነት ብቻ አይደለም ፣ ቢሸነግለውም ለጊዜው እስራኤል ለሁለት ከመከፈልና ከማነስ ይድኑ ነበር ። መከፋፈሎችና የአገር መሰንጠቆች የሚገጥሙት በኃይለ ቃል ነው ። ቃል ረቂቅ ሲሆን ግዙፉን አገር ማፍረስ አቅም አለው ። ይልቁንም በነገሥታት አንደበት የሚወጣው ኃይለ ቃል ፣ ቃል ብቻ ሳይሆን አንቀጽም ፣ ሕግም ሆኖ ለብዙዎች መነሣትና መውደቅ ምክንያት ይሆናል ። የብዙ ትዳር መራበሽ ምክንያት ኃይለ ቃል ነው ። ሰው አንደበቱን መግዛት ከቻለ ሌላው ኃጢአት ቀላል ነው ። አንደበታችንን ስንገዛ ዝሙትም ስርቆትም እየደከሙ ይመጣሉ ።

አንዳንድ ሰዎች ድንገት እንደሚባርቅ መሣሪያ ኃይለ ቃል ያወጣሉ ፣ መልሰው ሲጸጸቱ ይኖራሉ ። መሣሪያ የሚባርቀው መጠበቂያው ካልተዘጋ ነው ። ነቢዩ፡- “አቤቱ ፥ ለአፌ ጠባቂ አኑር” ያለው ለዚህ ነው ። (መዝ. 140 ፡ 3።) ተፈጥሮአቸው እንደ ግስላ ፣ እሳት የሆነ ፍቅራቸውንም ጠባቸውንም የሚገልጡት በኃይለ ቃል ነው ። በአካባቢ ፣ በአስተዳደግ ፣ በሃይማኖት ሰዎች ቍጠኛ ሊሆኑ ይችላሉ ። ከተቆጣ ልብ ውስጥ ኃይለ ቃል ይወጣል ። በውስጣቸው ፍርሃት ያለባቸው ሰዎች ፍርሃታቸው በሰዎች ታውቆ እንዳይናቁ በቍጠኝነትና በኃይለ ቃል ራሳቸውን ለመሸፈን ሙከራ ያደርጋሉ ። ሰው ሁሉ ሲርድላቸው የነገሡ የሚመስላቸው ሰዎች ኃይለ ቃል መናገር ይወዳሉ ። በደጅ ኃይለ ቃልን ሲያስተናግዱ መልስ ለመስጠት የሚፈሩ ቤታቸው ሲደርሱ ኃይለኛ ይሆናሉ ። ሰውዬው ማንን ታሸንፋለህ ? ቢሉት ሚስቴን አለ ይባላል ። የበላይ አለቆችን ቍጣ በሥር ሠራተኞች ላይ የሚገልጡ ብዙ ኃላፊዎች አሉ ። ግን ስሙም “ኃላፊ” ነውና እንደሚያልፉ አውቀው ዝቅ ማለት ይገባል ። የመውጣት ሁሉ መጨረሻው መውረድ ነው ። አንድ ቀን የረገጡት ሕዝብ እጅ ላይ ይወድቃሉ ። በሌላ በኩል በራሳቸው የሚናደዱ ለመለወጥ አቅም ያጡ ሰዎች ቍጡና ኃይለ ቃል የሚያወጡ ይሆናሉ ።

አንተ ግን ኃይለ ቃል አትጠቀም ። የመናገርህ ዓላማ ለመግባባት እንጂ ለመባላት መሆን የለበትም ። “ምክርና ቡጢ ለሰጪ ቀላል ነው” እንዲሉ ኃይለ ቃልህ ልጆችህን የሕሊና እስረኛ ሊያደርጋቸው ፣ ትዳርህን ጨለማ ውስጥ ሊከተው ይችላል ። ኃይለ ቃልህ አገር ሊያፈርስ ፣ ቤተ ክርስቲያንን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል ። በዚህ ዘመን ባለሥልጣኖች እንደ ወንደ ላጤ ይናገራሉ ፣ ወንደ ላጤው ደግሞ እንደ መንግሥት ያወራል ። በዚህ ምክንያት ተከታዩ ሕዝብ መሪ ያደረገው ራሳቸውን የማይመሩ አላዋቂዎችን ነው ። “አውራ ዶሮ ራሱ ሳይነቃ ሰው አያነቃም” ይባላል ። ሳይነቁ የሚያነቁ ሰዎችን ሕዝብ እየተከተለ ይገኛል ። ንጉሥ እንደ አባት መናገር አለበት ። ዜጋም እንደ ዜጋነቱ መናገር አለበት ። ኃይለ ቃል ፣ ኃይለ ቃልን ይወልዳል ። ዘር ነውና ዓመፅን ያበቅላል ። ብሽሽቅን ፣ ፌዝን ፣ ጦርንና ጠብን እየወለደ ይመጣል ። ስለዚህ ስትናገር ኃይለ ቃል አትጠቀም ። እውነት ያለ ቍጣ ብቻዋን ኃያል ናት ። በዓለም ላይ ለማሸነፍ ከፈለግህ ተሸነፍ ፣ ለመሸነፍ ከፈለግህ አሸንፍ የሚባለው ለዚህ ነው ። ይልቁንም አንተ ስለተቆጣህ ሰው ኃጢአት ትቶ ጽድቅን አያደርግምና ሰባኪ ስትሆን አትቆጣ ። እግዚአብሔር የሚያፈቅርለት እንጂ የሚናደድለት አገልጋይ አይፈልግም ። “የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና።” (ያዕ. 1 ፡ 20) ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም.

ያጋሩ

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።