የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት (29)

ቀጠሮ ያለማክበር ችግር

በዚህ ዓለም ላይ ብዙ ዓይነት ቀጠሮዎች አሉ ። ከወዳጅ ጋር ያለ ቀጠሮ አለ ። በዚህ ቀጠሮ ውስጥ ታማኝ አለመሆን ወዳጅን ሊያሳጣ ይችላል ። ወዳጅን ማጣት በፍቅር ረሀብ መቀጣት ነው ። በቤተ ክርስቲያን ውግዘት የሚባለው ተመክሮ ተዘክሮ እንቢ አልመለስም ያለውን ሰው መለየትና ፍቅር በማጣት እንዲቀጣ ማድረግ ነው ። ፍቅርን ማጣት ወይም ወዳጅን ማሳዘን ራስን እንደ ማውገዝ ነው ። የፍርድ ቤት ቀጠሮ አለ ። የፍርድ ቤት ቀጠሮ የሚያስጠይቅ ፣ በምክንያት የማይቀርበት ነው ። ወደ ፍርድ ቤት በሄድን ጊዜ እንፈራለን ። አንድ ቀን እንደ እኛ ችሎት ፊት የሚቆም ምድራዊ ዳኛ እንዲህ ካስፈራን ሰማያዊው ዳኝነት ብርቱ ነውና ከግፍ መራቅ ይገባናል ። የፍርድ ቤት ቀጠሮ በብዛት ይከበራል ። የሥራ ቀጠሮ አለ ። የሥራ ቀጠሮ አንድ ሠራተኛ የሚመዘንበት የመጀመሪያው መለኪያ ነው ። ለሥራ ቃለ መጠይቅ ቀጠሮ አርፍዶ የሚመጣ ራሱን በራሱ ከዚያ ዕድል ለይቷል ። በአንድ ቀን አቋሙ ቀጣይ ዘመኑን አውቀውታልና ሊቀጥሩት አይፈልጉም ።

ቀጠሮ ስንሰጥ የሰጠነው ቃላችንን ነው ። ቃል የእግዚአብሔር ስም ነው ። የወልድም የኩነት መጠሪያው ነው ። ቃል ብርቱ ነገር ነው ። ቀጠሮ ከመሐላና ከጥብቅ አንቀጽ ጋር የሚወዳደር ነው ። ቀጠሮዎች በተለያየ ምክንያት እንቅፋት ይገጥማቸዋል ። በዚህ ዘመን ላይ ያሉ ወጣቶች የሁሉም ነገር ሥርና ቅርንጫፍ ገንዘብ እየመሰላቸው ይሳሳታሉ ። ወዳጅንም በገንዘብ እንደሚያመጡት ያስባሉ ። በገንዘብ የሚያስቅ ሰው ይገኝ ይሆናል ፣ የሚያስደስት ወዳጅ ግን አይገኝም ። በገንዘብ የሚከብብ ሰው ማግኘት ይቻላል ፣ ውስጥ የሚገባ የልብ ወዳጅ ግን አይገኝም ። ቀጠሮዎች ከሚሰረዙበት ምክንያት አንዱ ገንዘብን ማስበለጥ ወይም ምን አገኛለሁ ብሎ ማሰብ ሊሆን ይችላል ። ፍቅር ግን ምን እሰጣለሁ እንጂ ምን አገኛለሁ ብሎ የሚያሰላ አይደለም ። ደስታ ያለው በመቀበል ሳይሆን በመስጠት ውስጥ ነው ። መርሳት የቀጠሮ እንቅፋት ነው ። መርሳት በዝንጉነት ጠባይ ፣ ብዙ አጀንዳና ወዳጅ በማብዛት ፣ ነሆለል ሰው በመሆን ፣ ሌላ ጊዜም በበሽታ የተነሣ የሚከሰት ነው ። መርሳትን ግን በጽሑፍና በደወል ማሸነፍ ይቻላል ። እየመረጥን የምንረሳ ከሆነም የእኛ ችግር ነው ። መርሳት ብዙ ጭንቀትና ውጥረት በማብዛት የሚመጣ በመሆኑ እኔ እኮ እረሳለሁ ብሎ የሚታለፍ አይደለም ። ያለ ዕድሜ የሆነ እንደሆነ ምንድነው ችግሬ ብሎ መጠየቅና መልሱን መፈለግ ያሻል ። አለማንበብ የመርሳትን ችግር ያመጣል ። ከሰዎች ጋር አለመገናኘትና አለማውራት መርሳትን ይወልዳል ።

ወዳጅን ቀጥሮ ማናገር ራስን የማከምና የመፈወስ ትልቅ ዘዴ ነው ። ብዙ ውጥረቶች ይቀላሉ ። የመኖር ፍላጎት እየጨመረ ይመጣል ። ያለንን ነገር በደስታ መጠቀም ይቻላል ። ተቀጣጥሮ ስልክ መዝጋት ይህ የጠባይ ዝቅታ ውጤት ነው ። ይህን የሚያደርጉ አገልጋይ ነን የሚሉም አሉ ። እንዲህ የኮሩበት አገልግሎት አንድ ቀን እየፈለጉም አያገኙትም ። አገልግሎትም ጡር አለው ። ሁልጊዜ ሊመቸን አይችልምና አስቀድመን ማሳወቅ ይገባናል ። ሰውን ከሰው አወዳድረን መቅረት ግን ነውር ነው ። የሁሉም ሰው ክብሩ እግዚአብሔር ነው ። ስለዚህ ሰው ሁሉ እኩል ነው ። አስድመን የሰጠነውን ቀጠሮ ማክበር ይገባል ። አንዳንድ ሰዎችን ተቀይመናቸዋል ወይም እነርሱን ማግኘት እየጎዳን ተቸግረን ይሆናል ። ይህንን በግልጥ ነግረን ማረም ወይም ቀጠሮ አለመያዝ ተገቢ ነው ። ሰው ለሰላሙ ዋጋ መክፈል አለበት ። ሰላማችንን ሠውተን የምናደርገው ግንኙነት ውስጣችንን እየጨረሰው ይመጣል ። ደግሞም የሚያኖረን እግዚአብሔር ነውና የሚያውኩንን የተቀየምናቸውን ሰዎች በግልጽ መንገርና መፍታት አስፈላጊ ነው ።

ቀጠሮአችንን ለማሳካት አለመቻላችንን መንገር ክብረት ነው ። እንዲሁ መቅረት ግን ያ ሰው ለእኛ ያለውን አመለካከት ዝቅ እንዲያደርግ ያስገድደዋል ። በመጀመሪያ ይበሳጭብናል ፣ ቀጥሎ ለእኛ ያሰበውን ትልልቅ ነገሮች መሰረዝ ይጀምራል ። ማንም ሰው ዋጋ የሚከፍለው ለአክባሪው ነው ። ሰዎች ቀጥረውን ቢቀሩ አንዳንድ ጊዜ ለበጎ ሊሆን ይችላል ። ሰብቅ ይዘውብን እየመጡ ከሆነ ለቀጣይ አንድ ዓመት ሰላማችንን ሊሰርቁት ነውና ቢቀሩ ይሻላል ። ወረኞችን አሉህና አሉሽ ማለት የሚወዱትን አለመቅጠርና አለማግኘት መልካም ነው ። ወሬውን እስኪነግሩን እንቅልፍ የላቸውም ፣ እኛ ሰምተን እንቅልፍ ስናጣ ግን ያን ጊዜ ይተኛሉ ። አምልኮተ እግዚአብሔርና ቃለ እግዚአብሔር በምንሰማበት ሰዓት ቀጠሮ መያዝ ክልክል ነው ። ካልሞትን በቀር ቤተ ክርስቲያን መቅረት የለብንም ። ስንሞትም የምንቀበረው እዚያው ነው ። በቀጠሮአችን ሰዓት ወዳጅነታችን እንዲቀጥል የማንስማማባቸውን ርእሶች መተው ይገባናል ። ክርክር አንዳንድ ጊዜ እኔ የበላይ ልሁን የሚያሰኝ የሥጋ ሥራ ነውና ፍቅርን ይጎዳል ። ቀጠሮን የሚጎዳው ሌላው ነገር ማርፈድ ነው ። አንዳንድ ማርፈድ የመቅረት ያህል ነው ። የአበሻ ቀጠሮ የሚባል የለም ። ቀጠሮ ፣ ቀጠሮ ነው ። ማርፈድን መዘናጋት ፣ መተኛት ፣ ጊዜን መለካት አለመቻል ፣ ወቅቱን አለማገናዘብ የሚወልደው ነው ። ማርፈድ ተጨማሪ ወጪ ነው ። አርፍደው አውሮፕላን ያመለጣቸው ተጨማሪ ወጪ ያወጣሉ ። ጓደኛቸው ተበሳጭቶባቸው የሄደባቸው ተጨማሪ ይቅርታና ማሳመን ያስፈልጋቸዋል ። ማርፈድ ጠባዩ ነው መባል ሞት ነው ። ሙሽሮች በሰዓቱ መድረስ የጠሩትን ሰው ማክበር ነው ። እስከማውቀው ድረስ ምግብ እያዩ ሙሽራን መጠበቅ የአገራችን ባሕል አይደለም ። እየበሉ እየጠጡ መጠበቅ ተገቢ ነው ። በሰርጉ ቀን ያረፈደ ፣ ትዳሩም ላይ ብዙ ማርፈድ ይገጥመዋል ።

ሰውን ማክበር ለራሳችን ያለን ክብር ውጤት ነው ። ቀጠሮ ማክበር ራስን ማክበር ነው ። ያደጉ አገሮች ሁሉ ያደጉት ቀጠሮን ወይም ሰዓትን በማክበር ነው ። ሰዓት ዋጋ ያጣው እኛ አገር ነው ። ማደግ ፈልገን በሰዓት ቀልደን አይሆንም ። ባለጉዳይ የቀደመው ሠራተኛ ማፈር አለበት ። አገር በዘፈን ሳይሆን በመሥዋዕትነት ታድጋለች ። ሌላ አገር ያለን ይመስል አንዷን አገራችንን ማጎሳቆል ሊበቃ ይገባዋል ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ