የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት (30)

15. የሰውን ነጻነት አክብር

አንዳንድ ገዥዎች ተነሥተው ነጻነት ሰጠናችሁ ይላሉ ። ሰው ለሰው ነጻነት መስጠት አይችልም ። የሰው ልጅ በተፈጥሮው ነጻነት ያለው ፍጡር ነው ። ደጋግ ነገሥታት ይህን ነጻነት ያከብሩ ፣ ያስመልሱ ይሆናል እንጂ ሊሰጡ አይችሉም ። የነጻነታችን ጌታ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ነጻነት ነጻ መሆን እንደ ልብ መፋነን አይደለም ። ነጻነት የሥጋን ፣ የነፍስን ፣ የመንፈስን መንሰራፋት ማክበር ነው ። ሰው ወደ ወደደው አገርና ግዛት ሂዶ መኖር ፣ መንቀሳቀስና መነገድ ፣ ማተረፍና መውለድ ይችላል ። ይህ የሥጋ ነጻነት ነው ። የነፍስ ነጻነቱ የማሰብ ፣ የመናገርና የመኖር መብት ነው ። የመንፈስ ነጻነቱ የወደደውን አምላክ የማመን ፣ የማምለክና የመደሰት ልዕልና ነው ። ነገሥታት ይህን ነጻነት በበላይነት መጠበቅና ማስጠበቅ ይገባቸዋል ። እኔ እንደማስበው አስብ ማለት ሳይሆን ወደ እኛ አሳብ ሰዎችን በፍቅርና በአመክንዮ መሳብ እርሱ ነጻነትን ማክበር ነው ። እኛ እንደምናምነው የማያምን ሰውን ላጥፋህ ልደምስስህ ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት ነው ። ይህች ዓለም የሰዎችም የእንስሳትም ዓለም ናት ። የጋራ ዓለም ናትና በጋራ ጉዳይ አንድ እየሆንን የሌላውን የግል መብት ማክበር አለብን ።

ስለ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ብዙ ሰምተናል ፣ ብዙ ተናግረናል ። ዲሞክራሲ ባለመምጣቱም ኀዘን ገብቶናል ። የምንመኘውና ለዘመናት አትመጣም ወይ ? ብለን የምንጣራው ዲሞክራሲ የሌላውን መብት ማክበር ነው ። የራስን ግዴታ አውቆ የሌላውን ድንበር አለመዳፈር እርሱ ዲሞክራሲ ነው ። የሰዎችን የማመን ፣ የመናገርና የመኖር መብት ማክበር እርሱ ዲሞክራሲ ይባላል ። ዲሞክራሲ እንደ ምርት ከውጭ አገር ተጭኖ የሚመጣ አይደለም ። ዲሞክራሲ በመካከላችን ያለ ከራስ ወዳድነት ወጥተን ስለሌሎች በማሰብ ተግባራዊ የምናደርገው ነው ። ለራሳችንና ለወገናችን የነፈግነውን ዲሞክራሲ ማንም ሊሰጠን አይችልም ። ሁልጊዜ ተሸማቀን ከመኖር አንድ ጊዜ ተስማምተን ነጻነትን ማስፈን ይገባናል ። በኑሮአችን ውስጥ ሁሉም ሰው የራሱን ነጻነት ማስከበር ይፈልጋል ። ዲሞክራሲ ግን የሌላውን ነጻነት ማክበር ነው ። ዲሞክራሲን ለማስፈን ሰው ከራሱ ውጭ የሚታገለው ነገር የለም ። የነጻነታችን ትልቁ ጠላት እኛው ነን ።

ሰዎች የተለያየ ፖለቲካዊ አመለካከት ይኖራቸዋል ። እንደ እኔ አስቡ ብሎ መጫን ግን አትኑሩ ብሎ መፍረድ ነው ። እንጨትና እንጨት ሲፋተግ እሳት ይወጣዋል ። የሰዎችም መነጋገርና መከራከር እውቀትን ይፈነጥቃል ። አንድነት ማለት አንድ ዓይነት መሆን አይደለም ። የተለያየን መሆናችን ውበትን እንጂ ጭንቀትን የሚፈጥር አይደለም ። ሰዎች የራሳቸው ሃይማኖት አላቸው ። ከምናምነው ተቃራኒ ነገር ቢያምኑም የመኖር መብት አላቸው ። በምንም መንገድ አገር የዜጎች እንጂ የአንድ ሃይማኖት መሆን የለባትም ። ይህ የዜጎችን መከራ ያበዛል ። የነገሥታትም ድርሻ ሃይማኖትን ማስፋፋት ሳይሆን ሰላምና ዕድገትን ማስከበር ነው ። ሰዎች በመሰላቸው መንገድ ራሳቸውን በተለያየ ሱስ እየጎዱ ሊሆን ይችላል ። መጥላትና ማሳደድ ግን አንችልም ። ወደ ቀናው መንገድ በፍቅር መመለስ እንችላለን ። በምድር ላይ ለሃይማኖት ሰው የተሰጠው ትልቅ መሣሪያ ፍቅር ብቻ ነው ።

አንተ ግን የሌላውን ነጻነት አክብር ። ፍላጎታቸውን ተጭነህ ወዳጆችህ የምታደርጋቸው የሉም ። ለጊዜው ያደፍጡ ይሆናል ፣ አቅም ሲያገኙ ግን ጥለውህ ይሄዳሉ ። ሰዎች የራሳቸው የሆነ ጊዜ ሊፈልጉ ይችላሉ ። ለፍላጎታቸው ተዋቸው ። ዛሬ አንተን ማግኘት አይፈልጉ ይሆናል ። ከራሳቸው ችግር ጋር እየታገሉ እንጂ አንተ ርካሽ ሰው ስለሆንህ አይደለም ። ሁለት ጊዜ ያህል ደውለህ መልስ ካልሰጡህ ተዋቸው ። ስላልፈለጉህ በማትፈለግበት ቦታ ጊዜ አታጥፋ ። አንተን የሚፈልጉህ “በመጣልኝ” ብለው የሚሳሱልህ ብዙ አሉ ። ሰው የሚጠሉትን ሲያሳድድ ፣ የሚወዱትን ይከስራል ። ራስህን ዝቅ ማድረግ ተገቢ ነው ። ራስህን ርካሽ ማድረግ ግን እንድትጣል ያደርግሃል ። በመገኘትህ የምትጠቅማቸው ሰዎች ይኖራሉ ፣ መገኘትህንና ቅርበትህን ካቃለሉ ግን ራቃቸው ። ክብር በሌለበት ፍቅር የለም ፣ ፍቅር በሌለበትም እግዚአብሔር የለም ። ማንንም ሰው አሳምን እንጂ አትለማመጥ ። የሰውነት ክፍሎችህ ካንተ ጋር ናቸው ። በሰው እጅ አትጎርስም ፣ በሰው ትንፋሽ አትኖርም ። የራስህን ሕይወት የሰጠህን ጌታ አክብር ።

ሰዎች የሚወድዱት አለባበስ ፣ የኑሮ ዘይቤ ፣ የቤት አሠራር ፣ የትዳር ምሪት ፣ የልጆች አስተዳደግ አላቸው ። ቋሚውን እውነት አሳውቃቸው እንጂ በእኔ መንገድ ካልሄዳችሁ እያልህ አትጎትታቸው ። የጣሉህ ሰዎች የጎተትካቸው እንቢተኞች ናቸው ። እገሌ ይጾማል አይጾምም ፣ እገሌ በቅድስና ነው ያለው በርኵሰት እያለህ በሰው ጓዳ አትዋል ። ይህ ርካሽነት ነው ። የራስህን ኑሮ ኑር ። ካንተ የሚፈልጉ ከሆነ እንኳን በወዳጆችህ በጠላትህም አትጨክን ። እንኳን አንተን ሰጪ አደረገህ ። የማይፈልጉ ሰዎችን ካልመከርኩ አትበል ። እርዳታህን የሚሸሹ ሰዎችን በግድ ካልረዳሁ አትበል ። የከበረውን ነገር ዋጋ በማይሰጡ ሰዎች ፊት አትጣል ። ውድ ጊዜህንም ተራ ነገርን ከሚፈልጉ ሰዎች ጋር አታባክን ። በማትፈለግበት ቦታ አትገኝ ። ምንም ነገር ስታደርግ ሰዎችን አስፈቅድ ። ያለ ፈቃዳቸው የምታደርገው ነገር ላንተም ለእነርሱም ደስታ አይሰጥም ። በጣም ጥንቃቄም ለስህተት ይዳርጋልና እጅግም ጠንቃቃ ፣ እጅግም ጻድቅ አትሁን ። ወደ ጓደኛህ ቤት እግር አታብዛ ። ወዳንተ ቤት እግር ቢያበዙ ግን ክርስቶስን እንደምትቀበል አድርገህ ተቀበላቸው ። የልብህን ሁሉ ፣ ለሁሉ አትናገር ። ሰዎችም ሁሉን እንዲነግሩህ አትፈልግ ። ባለትዳሮች ካልጋበዙህ በቀር ልዳኛችሁ አትበል ። ባልዬው በሌለበት ቤት ሚስቲቱ ብትቀጥርህ አትሂድ ።

በአገራችን በሰው ገላም ካላዘዝን የምንል ደፋሮች ነን ። የምንኖረውም በመጠባበቅ እንጂ ያመንበትን አይደለም ። በገዛ ሕይወታችን ላይ ድራማ የምንሠራ ምስኪኖች ነን ። ማኅበራዊነታችን መልካም ነው ። የሌላውን መብት መጋፋት ግን ነውር ነው ። በሁሉም ነገር ላይ አስተያየት መስጠት ግዴታችን ይመስለናል ። ለሁሉም መልስ አይሰጥም ። ብቻ የሰዎችን ነጻነት አክብር። ሊሄዱ የሚፈልጉትን በሰላም ሸኝ ። የሚመጡትን ደጎች ተቀበል ። በትዝታ ታስረህ የዛሬን ኑሮ አትሰርዝ ። ጨርሻለሁ ብለው መሄድ የማያውቁ ሰዎችን አጨራረሱን አሳያቸው እንጂ እንዲያውኩህ አትፍቀድላቸው ። ምክንያቱም ያንተ ኑሮ ይህ ነው ፣ እነርሱ ግን አማራጭ አላቸውና ። ርቀውህ የነበሩ ሰዎች እንደገና ሲመጡ በጥንቃቄ ተቀበል ። ምናልባት ያልጨረሱትን ተንኮል ለመጨረስ ይሆናል ። መጠንቀቅ ይቅር አለማለት አይደለምና ። ዕድሜህ እንዳያጥር ለአልምጦች ጋር አትኑር ! ከራስህ ጋር መሆን ጣፋጭ ነው ፣ ሰዎች ካልመጡ ሕይወትህ የተሰረዘ አይምሰልህ ! ሁልጊዜ ሰዎች አይገኙምና ከራስህ ጋር ልታደርግ የሚገባውን ዛሬውኑ አቅድ ! የምትፈልገውን በትክክል እወቅ ፤ ሕይወትህ መደሰት ትጀምራለች!

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሰኔ 7 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ