የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት (31)

16. ዜማ

ዜማ በሰው ነፍስ ውስጥ የተቀመጠ ጥልቅ ፍላጎት ነው ። ዜማ ምድራዊውን ሰው ሰማያዊ የሚያደርግ ነው ። የነፍስ ሀልዎት መገለጫ ነው ። ነፍስ ስትታደስ ሥጋም አብሮ እንደሚታደስ ዜማ ይነግረናል ። ዜማ ሰዎችና እንስሳት የሚካፈሉት የጋራ ፍላጎት ነው ። ዜማ ሲሰሙ አደገኛ የሚባሉ አራዊት ይመሰጣሉ ። ዜማ ጨካኙን የማራራት አቅም አለው ። ቀሳውስት ቸገረኝ እንጂ ጨነቀኝ ሲሉ አይሰማም ። ጭንቀትም በጉልህ አይታይባቸውም ። የዚህ ምሥጢሩ ዜማ ነው ። ዜማ ያድሳል ። የከበደንን ደመና ያነሣል ። ዜማ ደስታን ፣ የአእምሮ መፍታታትን ፣ ጣዕምን ፣ ተደማጭነትን ፣ ተወዳጅነትን ያጎናጽፋል ። በዜማ ውስጥ ብዙ መልእክቶች አሉ ። ዜማ ምስጋናንና ትምህርትን በጣዕም ለማስተላለፍ የሚረዳ ነው ። ዜማ የታላቅ ፍልስፍና መገለጫ ነው ። ዜማ በሰማይ የሚጠብቀን ድግስ ነው ። ቅዱስ ያሬድ የዜማው ባላባት እስከ ዛሬ ድረስ ተሰምተው የማይጠገቡ ዜማዎችን ለቤተ ክርስቲያን አበርክቷል ። በርግጥ መንፈሳውያን እንደ መሆናችን እግዚአብሔር እንደ ገለጠለት እናምናለን ፤ የስጦታውን ምንጭም አንስትም ። ቅዱስ ያሬድ እንዲህ ተቀብሮ መቅረቱ ኢትዮጵያዊ መሆኑ ነው ። የሌላው ዓለም ሀብት ቢሆን ኖሮ የየቀኑ ርእስ ይሆን ነበር ።

ዜማ የትልቅ ሥልጣኔ መገለጫ ነው ። ዜማን በኖታ ዓለም ከማቅረቡ በፊት ቅዱስ ያሬድ አዘጋጅቶታል ። ዜማ ቋንቋ ነው ። ስብሐተ እግዚአብሔር የሚደርስበት ሰረገላ ነው ። ዜማ ክንፍ ነው ፣ ወደ ሰማየ ሰማያት የምንወጣበት ነው ። ጸሎታችንን በዜማ ብናደርስ የምንጸልየውን እናስተውለዋለን ፣ እንባ በዓይናችን ይሞላል ፣ ልባችን በመለኮት ፍቅር መቅለጥ ይጀምራል ። ጮክ ብለን ማዜምና መዘመር በጣም ወሳኝ ነው ። በሳምንት አንድ ቀን እንኳ አፍ አውጥተን ብናዜም የከበደን ነገር ይቀለናል ። ዜማ የነፍስ ምግብ ፣ የጭንቀት ዱላ ነው ። ማንጎራጎር የሚወድዱ ሰዎች ደስተኞች ናቸው ። እያንጎራጎሩ ሲያለቅሱ ይታደሳሉ ። እንባ ወደ ውጭ ካልፈሰሰ ወደ ውስጥ ይፈሳል ። ያን ጊዜ ሰባራ ሰው ያደርገናል ። ዜማ ስብሐተ እግዚአብሔር የሚቀርብበት መሠዊያ ነው ። እግዚአብሔርን የሚማርከው ዜማው ሳይሆን የልባችን መቃጠል ነው ። ዜማ ግን ምድራዊነታችንን ሰማያዊ ያደርገዋል ።

የሚያዜሙ ሰዎች ብዙ ጊዜ እውቀት አይወድዱም ። በዚህ ምክንያት “ድምፅና ቁንጫ ባዶ ቤት ይወዳል” እየተባሉ ይተቻሉ ። የሚያዜም ሰው ግጥም ፣ ቅኔ ፣ የንግግር ችሎታን ማዳበር አለበት ። በርግጥ የሊቃውንቱን ቅኔ ለዓለም የሚያደርሱት ዜመኞች ናቸው ። የሚያዜሙም ከእውቀት መራቅ አይገባቸውም ። ዜማ ሙያ ሲሆን ለጥቂቶች ነው ። አምልኮ ሲሆን ግን ለሰው ልጆች ሁሉ ነው ። አእዋፋት በማለዳ ያዜማሉ ። ባናያቸውም እንወዳቸዋለን ፣ ዜማ እንደሚያነቃም እንረዳለን ። የሚያዜሙ ሰዎች በሰው ነፍስ ውስጥ አሉ ። ሰው ከውጫዊ አካሉ ይልቅ ነፍሱ ስፋት እንዳላት ዜማና ተጽእኖው ይገልጥልናል ። ዜማ የተለያየ መልእክት አለው ብለናል ። የማኅበረሰብ መግባቢያ ቋንቋ ነው ። ሰርግን ፣ ጦርነትን ፣ ደስታን ፣ ኀዘንን በዜማ እንወጣለን ። ሥርዓት ያላቸው ዜማዎች ፣ የማኅበረሰቡ ግኝት የሆኑ ግጥሞች ለሰርግ መዋል አለባቸው ። ዜማ የዝሙት ማስታወቂያ ሲሆንና እጅና እግርን ማወደሻ ሁኖ ሲቀር ይተቻል ። መንፈሳዊነት ማኅበረሰብን የሚደፈጥጥ አይደለም ። በሰርጌ ጌታ ይክበር የሚሉ አሉ ፣ ጥሩ ነው ። ጌታ ግን የሚከብረው በሁለት ሰዓት ፕሮግራም ብቻ ሳይሆን በኑሮ ውስጥ ነው ። ሚስትህን በአጋፔ ፍቅር ስትወዳት ፣ ባልሽን እንደ ራስ ስታከብሪው ያን ጊዜ እግዚአብሔር ይከብራል ።

በዜማ መለቀስ ፣ ኀዘን መተንፈስ አለበት ። ያልወጡ ኀዘኖች ብዙዎችን ለድባቴ እየዳረጉ ይገኛሉ ። አገራችን ታላላቅ ሰዎች የነበሩባትና ያሉባት አገር ናትና ደስታንም ኀዘንንም መግለጫ አበጅተዋል ። ደግሞም የባሕላችን ማሳያ ነውና ሊከበር ይገባዋል ። አለማልቀስ ዘመናዊነትም መንፈሳዊነትም አይደለም ። ሬሳ አስቀምጦ አላለቅስም ማለት ጉራ ሲሆን አብረው የሚያላቅሱ ሲሄዱ ውጋቱ ይጀምራቸዋል ። እንዴት ሰው ሞትን እያስተናገደ ለማልቀስ ይሳሳል ?

አገርን የሚያወድሱ ፣ ጀግንነትን የሚያነሣሡ ዜማዎች አንድን ትውልድ የአገር ዘብ አድርጎ የማቆም አቅም አላቸው ። እዚህ የምንጽፈውና የምናመልከው በዳር ድንበር የሚጠብቅ ወታደር ስላለ መሆኑን ማወቅና ክብር መስጠት ይገባናል ። ከዜማ ጋር የዜማ መሣሪያዎችን መለማመድ ግድ ይላል ። ቢያንስ አንድ የዜማ መሣሪያ ማወቅ ለቀጣዩ ዕድሜ ፣ ለእርጅና ብቸኝነት ወሳኝ ነው ። ዜማ ለማኞች እንኳ ጨካኙን የሚያራሩበት ነው ። የዜማ ዕቃ ይዘው የሚያዜሙም ከመንገዳችን ቆም ያደርጉናል ። ዘወትር ከጸሎታችን ጋር ድምፅ አውጥተን ብንዘምር ላሉብን ውጥረቶች ቅለት ይሰጠናል ። ነገር ግን አጠገባችን ያለውን ሰው እንዳንረብሽ ፣ ተወዳጁን አምላክ በእኛ ረባሽነት እንዳናስጠላው መጠንቀቅ ያስፈልጋል ። ዜማ የራሱ ሥርዓት አለውና ሊጠና ፣ ሊያድግና ሊበረታታ ይገባዋል ። ከሕይወት ሥነ ሥርዓት አንዱ ዜማ ማዜም ነው ። በቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት የዜማ ዕቃ ጸናጽል ፣ መቋሚያና ከበሮ ነው ። የምእመናን የዜማ ዕቃ በገና ፣ መሰንቆ ፣ ክራር ፣ እንዚራ ተጠቃሽ ናቸው ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ