19. ጨዋታ ልመድ
ጨዋታ ማለት ጨዋዊ ፣ ጨው የሆነ ፣ ጣዕም ያለው ፣ ንግግርን የሚያጣፍጥ ፣ ተወዳጅ የሚያደርግ ማለት ነው ። ጨዋታ የጨዋ ሰው ስልት ፣ ሌላውን ለማስደሰት የሚደረግ ቅዱስ መንገድ ነው ። ሰዎች ሰዎችን ለማስደሰት ያሰክራሉ ፣ ለዝሙት ይዳርጋሉ ። ጨዋታ ግን የጨዋ ሰው መንገድ ሲሆን በቅዱስ ነገር ያንን ሰው ማስደሰት ነው ። ቀንበር የበዛበት ይህ ዓለም ያለ ጨዋታ አይዘለቅም ። እስከማውቀው ካህን ችግረኛና ረሀብተኛ ነው ። ዛሬ ላይ የሚታዩ ጥቂት መሳፍንት አከል ካህናት ቢኖሩም አሁንም ድረስ ካህን ኑሮው የጭንቅ ናት ። ካህን ከአገልግሎት መልስ የሚያገኛትን ጥሬ በጨዋታ ጮማ ያደርጋታል ። ጨዋታው ስልት አለው ። የራስንም ክብር መጠበቅ አለውና ነውረኛ ቃላት አይነገሩበትም ። ያ ሰው ስለ ራሱ ይነገረዋል ፣ የሚነገረው ግን ራሱ የሚስቅበትን ክስተት ነውና ይስቃል ። ካህን ያንን የችግር ዘመን በጨዋታ አጣፍጦታል ። ጨዋታ ሰው ራሱን የሚያክምበት ትልቅ ፈውስ ነው ። የሰው ልጅ በመተንፈስ የሚኖር ፍጡር ነው ። ሲተነፍስ የተቃጠለው አየር እየወጣ አዲሱ ይገባል ። ሲጫወትም ብሶቱ እየተነነ ተስፋ በውስጡ እየሞላ ይመጣል ።
መጫወት በፍቅር መሠረት ላይ የሚታነጽ የደስታ ቤት ነው ። ለመጫወት መፋቀር ፣ መጣጣም ፣ መቀራረብ ፣ አብሮ መኖር ፣ መገጣጠም ፣ መፈቃቀድ ያስፈልጋል ። ጨዋታ ፀጥታን ይሽራል ። በዓለም ላይ በገንዘብ የሚገዙ ፀጥታዎች አሉ ። ሰዎች የጽሞና ቦታዎችን ፣ ውድ ሆቴሎችን የሚመርጡት ጸጥታን ለመግዛት ነው ። አስፈላጊ ጸጥታዎች አሉ ። ሰውን ከችግሩ ጋር እንዲያወራ ፣ እንዲተክዝ ፣ ውስጡ እንዲያልቅ የሚያደርጉ ጸጥታዎችም አሉ ። መንፈሳዊነት ማለት ማኩረፍ ፣ ወይም ሁሉንም ነገር እየገሠጹ መሄድ አይደለም ። መንፈሳዊነት ራስን ማስጨነቅ ሳይሆን ራስን መካድ ነው ። ራስን ማስጨነቅ ስቃይን መጋበዝ ነው ። ራስን መካድ ግን ራስን በቅጡ መመልከት ፣ ቀለል አድርጎ መኖርና ኅብረት መፍጠር ነው ። ጨዋታ አጉል ጸጥታን ይሽራል ። ሰዎች የሚወለዱትም የሚሞቱትም አንድ ቀን ነው ። አንድ ቀንና አንድ ሰዓት ዋጋው ብዙ ነው ። ይህችን ሰዓት ማለፍ ባለመቻል ብዙዎች ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠዋል ። ስንጨነቅ ለአንድ ሰዓት ከሚያጫውተን ወዳጅ ጋር ማሳለፍ መልካም ነው ። ልብ አድርጉ በቅጽበት ስህተት ሾፌር ራሱንም ሰዎችንም ይገድላል ። በቅጽበት ትዕግሥት ማጣት አንድ ሰው ዕድሜ ልክ እስራት ይገጥመዋል ። የጨዋታ ሰዓቱ ትንሽ ቢሆን እንኳ የሚያሳልፈው ነገር አለ ።
በአገራችን በመንገድም ይሁን በቤት ፣ ሰው ከሰው ሲገናኝ ሰላምታ ይሰጣጣል ። ሰላምታ ለመሰጣጠት መተዋወቅ መስፈርት አልነበረም ። ዛሬ እንዲሁ መቀላቀል ፣ ዘመናዊ ኩርፊያ በዝቷል ። ስለዚህ ላያችን ጨርቅ ደርቦ ውስጣችነ ተራቁቷል ። ጨዋታ ግን ኑሮን ያቀላል ። በመንገድም ጨዋታ ካለ መንገዱ ያጥራል ። በተለያዩ መዝናኛዎች ጨዋታ ካለ ሰውዬው የከፈለውን በትክክል መጠቀም ይችላል ። ጨዋታ የወሬ ቅመም ፣ የኑሮ መርዝ ማርከሻ ፣ ሰውና ሰው የልብ ስጦታ የሚለዋወጡበት ነው ። አንዳንድ ሰዎች ራሳቸውን ደረቅ አድርገው ገንብተውታል ። ስለዚህ ሲናገሩ እንኳ የሚጠቀሙአቸው ቃላት ሥራ ላይ መዋል የሌለባቸው እንደሆኑ እያሰብን ለእነርሱ እናፍርላቸዋለን ። ጨዋታ የሚያውቅ ሰው ግን ብዙ ከመናገር ንግግሩ የጠራ ይሆናል ። መናገር ባያስፈልግ ኖሮ አንደበት ባልተፈጠረ ነበር ። የተከለከለው ማውራት ሳይሆን ሁሉን መናገር ነው ፣ መጫወት ተገቢ ነው ። “የዘመድ ጨዋታ ቆራጣ ቆራጣ” እንዲሉ ! ርእስ የለውም ፣ አጀንዳ አይያዝም ፣ ብዙ ነገሮችን ይነካካል ፤ ግን ደስ ይላል !
ሰዎች እንስሳትን የሚያረቡት አንዱ ለመጫወት ነው ። እንስሳት ያጫውታሉ ፣ ያነጋግራሉ ። ዝም በማለት አእምሮ በድን እንዳይሆን ዶሮ በየሰዓቱ እሽ ሲሏት ፣ ውሻን ተዉ ሲሉት ፣ ድመት ክፍ ስትባል ጨዋታ ይኖራል ። የሰውን ልጅ ብቸኝነት እየተካፈሉ ያሉ ፣ ይበልጥ በሰለጠነው ዓለም እንስሳት ናቸው ። የሚገርመው ሰው ለሰው ያለው ግንኙነት ፈርሶ ሰውና እንስሳት የጠበቀ ግንኙነት ጀምረዋል ። በአሜሪካ ምድር ዓመታዊ የውሻ በጀት ኢትዮጵያ ለሕዝብዋ እስካሁን መድባው አታውቅም ። ባል አለኝ ፣ ልጅ አለኝ ወይም ውሻ አለኝ የሚል መልስ በዘመናዊው ዓለም ተለምዷል ። ሥልጣኔው ትዳርን በወራት ዕድሜ ውስጥ አስገብቶታል ። በትዳር ቢያንስ ሦስት ዓመት ብቆይ ነው ፣ እርሱም ከተሳካ ፣ ከውሻዬ ጋር ግን አሥራ ሁለት ዓመት እቆያለሁ እያሉ ከሰው ውሻ መምረጣቸውን ይናገራሉ ። ሰው ጨዋታ ፣ አነጋጋሪ ይፈልጋል ።
ጨዋታ የሚያውቁ ሰዎች ምነው በመጡ የሚባሉ ናቸው ። እነዚህ ሰዎች የሰውን ጭንቀት ያለ ኪኒን ለማስወገድ የሚጥሩ ናቸው ። የጎንዮች ጉዳት የሌለበት የአእምሮ መድኃኒት ጨዋታ ይባላል ። ጨዋታ ለማወቅ ማንበብ ፣ ታሪክ ማወቅ ፣ ትልልቅ ሰዎችን መጠየቅ ፣ ተጨዋቾችን ማዳመጥ ይገባል ። ልብ አድርጉ ጨዋታ ማለት ሐሜት ፣ ሽሙጥ ፣ ሌላውን ዝቅ ማድረግ ፣ አሽሙር ፣ በጎን ሰውን መውጋት በፍጹም አይደለም ። ይህ የሚፈስስ ደም ባይታይም ጦርነት ነው ። ጨዋታ ግን አእምሮን ማፍታታት ነው ። ጨዋታ አካላዊ ሲሆን የተለያዩ ስፖርቶችን ማዘውተር ሊሆን ይችላል ። ጨዋታ አእምሮአዊ ሲሆን አንደበትን በመጠቀም ሰውን እያስደሰቱ ማስተማር ነው ። ጨዋታ መንፈሳዊ ሲሆን ነገረ እግዚአብሔርንና ተፈጥሮን እየተገረሙ ማስተንተን ነው ። በየለቅሶ ቤት አጫዋቾች አሉ ። ለቀስተኛውን በግድ ያስቁታል ። የእነዚህ ሰዎች ዋጋ ትልቅ መሆኑ አይገባንም ። “ጥርስ ባዳ ነው” የሚባለው ሬሳ አስቀምጦ ስለሚስቅ ነው ። ጨዋታ ከሞት በላይ ይሆናል ማለት ነው ።
ጨዋታ ፖለቲካ ካለበት ጥሩ አይደለም ። ምክንያቱም የእኛ አገር ፖለቲካ በአምስት ዓመት አንዴ ሳይሆን የዕለት ኑሮ ሆኗል ። ፖለቲካውም በአሳብ ላይ ሳይሆን በጎሠኝነት ላይ የተመሠረተ ነው ። ስለዚህ ፖለቲካና የዘረኝነት ወሬ ጨዋታን ይጎዳሉ ። በቅርቡ የበቀለ ሕዝብና ጎሣ የለምና ዘመን ያመጣውን ዘረኝነት መጣል ያስፈልጋል ። እሳት የማይታይበት ቃጠሎ ዘረኝነት ነውና ። ሰው ሁሉ እኩል ነውና ሌላውን ጎሣ የሚያሳንስ ቀልድ እንኳን ለመናገር ለመስማት አትፍቀድ ። ጨዋታ መልካም ነው ። ጨዋታ ጨው ነው ፣ ኑሮን ያጣፍጣል ። ጨዋታ የጨዋ ሰው ግብዣ ነው ። “ተገናኝተን ስንጫወት እንደር” ይል ነበር የድሮ ሰው ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሰኔ 21 ቀን 2016 ዓ.ም.