21. አመስግን – ውለታ አይለፍብህ
ይህች ዓለም ለብዙ ሰው ከባድ የትግል ሜዳ ብትሆንም ለአመስጋኞች ግን ቀላል ናት ። ስናመሰግን ችግሩን ሳይሆን እግዚአብሔርን እናያለን ። ስናመሰግን ያጣነውን ሳይሆን ያተረፍነውን እናስባለን ። ስናመሰግን የሄደውን ሳይሆን ያለውን እንመለከታለን ። ማመስገን ዓይንን ያበራል ። ማመስገን ሁሉንም ነገር በዜሮ ከማባዛት ያድናል ። ማመስገን ከተራራው ጀርባ ያለውን መስክ ፣ ከዋሻ መጨረሻ ያለውን ቀና ማለት ያስተውላል ። ማመስገን ነገር ሁሉ ለበጎ ነው ብሎ ከማሰብ የመነጨ ነው ። ማመስገን እኔ ለእኔ ከመረጥሁት እግዚአብሔር ለእኔ የመረጠው ይበልጣል ብሎ መቀበል ነው ። ማመስገን አለማጣት ፣ አለመታመም ፣ አለመጎዳት አይደለም ። ደግ ደጉን የመቁጠር የሕይወት ጥበብ ነው ። የሚያመሰግኑ ሰዎች ልባቸውና ፊታቸው ይበራል ። በዚህ ጊዜ ሰይጣን ፈተና ይቀይራል እንጂ በቅድሙ ወጥመድ ላይ አይዘገይም ። ሰዎች እኛን የሚፈልጉት ብሩህ ፊታችንን ፣ ቅን ልባችንን በማየት ካለባቸው ችግር ለማረፍ ነው ። ምሬተኛ ስንሆን ሰላማቸውን ላለማጣት ይሸሹናል ። አሊያም ተጠንቅቀው ይቀርቡናል ።
የምናማርረው ምናልባት ችግርን በችግር ለመፍታት ተነሥተን ስላልተሳካልን ሊሆን ይችላል ። የምናማርረው ከመንቀሳቀስ ተአምር በመጠበቅ ደክሞን ሊሆን ይችላል ። የምናማርረው ትልቅ የምንለውን ነገር ጠብቀን ለዛሬ በሚበቃን ትንሽ ነገር ስላልረካን ሊሆን ይችላል ። የምናማርረው ከሰው የመላእክትን ግብር ጠብቀን ሊሆን ይችላል ። ማመስገን ሁሉንም ነገር በልኩ የማየት ውጤት ነው ። የምንፈልገውን ብናገኝም ሞት አይቀርም ። ከሞት የሚያድነው ግን አሁንም በእጃችን ነው ። በሕይወት ውስጥ አለኝ ከማለት አለሁ ማለት ይበልጣል ። የሚጎድልበትም በሕይወት ያለ ነው ። የለኝም ያልነው በሕይወት ስላለን ነው ።
ከሁሉ አስቀድሞ እግዚአብሔርን ማመስገን አስፈላጊ ነው ። ተኝተን የምንነቃው ጠባቂ ወታደር ስላለ ሳይሆን እግዚአብሔር በመንበሩ ስላለ ነው ። ዛሬን ያየነው ወጥተን የገባነው ፣ ዘርተን ያጨድነው ፣ ወልደን የሳምነው በእግዚአብሔር ቸርነት ነው ። ካሉት የሞቱት ቆንጆዎችና ጠቢባን ይበዛሉ ። በዚህ ቀን እንኳ ብዙ ደጋግ ሰዎች ይሞታሉ ። ክፉዎች ለጉድ ይቀመጣሉ ። ሞት በመንፈሳዊ ቋንቋ ምሕረት ነው ። እስረኛ በምሕረት ሲለቀቅ ደስ እንደሚለው በሰማይም የተጠራች ነፍስ በነጻነትዋ ደስ ይላታል ። ግን እስር ቤት ሰብሮ የወጣ ቅጣቱ ከባድ ነው ። እንዲሁም ራሱን ያጠፋ በሰማይ ስደተኛ ነው ። የሕይወት ባለቤት እግዚአብሔር ነውና ። እግዚአብሔርን ማመስገን ተገቢ ነው ። የዛሬው ስኬትህ ትልቅ ሰው የሆንህና አምላክ አያስፈልግህም የሚል እሳቤ አምጥቶ ከሆነ በጣም ልትጠነቀቅ የሚገባው ሰዓት ነው ። ምክንያቱም ቀጥሎ የሚመጣው ብልሽት ልክ የለውም ። ሰው መታበይ ሲጀምር ውድቀቱ በቅርብ ርቀት ላይ ነው ። እግዚአብሔር ትዕቢትን ፈጥኖ ይቀጣል ። ናቡከደነጾር በተመካበት ቅጽበት እንደ እንስሳ ሆነ ። ሄሮድስ ድምፁ የአምላክ ነው ሲሉት ስለሞቀው ወዲያው ተቀስፎ ሞተ (ዳዳ. 4፡30 ፤ የሐዋ. 12፡23)።
ብዙ ሰዎችን እንታዘባለን ። የእግዚአብሔርን ደጅ በእንባ ያጣበቡትን ሰዎች እናስታውሳለን ። የያዙትን ነገር በትክክል መጨበጣቸውን ሳያረጋግጡ እግዚአብሔርን ትተዋል ። ከቤቱ ርቀዋል ፣ ጸሎት አቁመዋል ። ለምን ሲባሉ ደርዘን ምክንያት ይደረድራሉ ። በምናመሰግንበት ቀን ከሀዲ መሆን ከባድ ኃጢአት ነው ።
ማመስገን አለብን ። በልጅነታችን በጣም የሚወዱን ፣ ይከብደዋል እያሉ የእኛን ሸክም የሚሸከሙልንን ፣ ትምህርታችንን ለማገዝ የሚያስጠኑንን ፣ ከረሜላ እየገዙ የሚስሙንን ፣ እናታችን ገበያ ስትወጣ የሚጠብቁንን ፣ ያሳደጉንን ሞግዚቶች ፣ ስለ እኛ ከሰዎች ጋር የተጣሉንን ተቆርቋሪዎች ዛሬ ማመስገን አለብን ። አዎ እኛ አድገን ሠላሳ ዓመታችን ነው ። እነርሱ ሃምሳ ገብተዋል ። ደግሞም ወልደው ከብደዋል ። ረስተውናል ። እኛ ግን አስታውሰን ምስጋና ማቅረብ አለብን ። ዕድሜ የሚሰጠን የምስጋና ዕዳችንን እንድንከፍል ነው ። እነዚያ ስንራብ ያጎረሱንን ፣ ከቤት ወጥተን ስንከራተት ያስጠጉንን ላንቀየማቸው መውደድ አለብን ። በሰማይ ስንሄድ ከሚያስፈሩ ጥያቄዎች አንዱ በጎ የዋሉልንን አለማመስገን ነው ። እነዚህ ሰዎች ዕድሜ ተጭኖአቸው ፣ ሁሉም ነገር ከብዷቸው ሊሆን ይችላል ። ያኔ በልጅነታችን ለእኛና ለቤተሰባችን ያደረጉትን ስንነግራቸው ደስ ይላቸዋል ። ደግሞም መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ስጦታችንን መስጠት አለብን ። ሁሉን ላፌ አይባልም ፣ የተሰጠን ልንሰጥም ነው ። እነዚህ ሰዎች የማይታወሱን ከሆነ አውሬ ነን ። እነዚህ ሰዎች የሚታወሱን ከሆነ አእምሮአችን ባለ ዕዳ ነው ። ከዕዳ ጋር መዋል ፣ ማደር ራስን በሰንሰለት አስሮ መግረፍ ነው ። ዛሬ ማታ ባለውለታዎቻችሁን አስታውሱ ። ያለፈውን ነገር አስታውሳችሁ ንገሩአቸው ። አመስግኑ ። አመስጋኞች ዕድሜአቸው ረጅም ነው
።
አንተ ግን ስሟ የእንጀራ እናት ቢባልም በጣም ትወድህ የነበረችውን አሳዳጊህን አስብ ። ዛሬ እናትህን በማግኘትህ እርስዋን አትርሳ ። ሲመሽ ምን ሆነህ ነው ያሉህን ፣ ለመሸጥ ካስቀመጡት ዳቦ እየሰጡ ያሳደጉህን እማማ እገሌን ፈልጋቸው ። ጀንበራቸው ልትጠልቅ እያዘቀዘቀች ነውና ቶሎ ብለህ ውለታህን መልስ ። እኒያ የሚወዱህ መምህር ፣ ከዚያ ሁሉ ተማሪ ላንተ ፍቅር ነበራቸው ። እርሳቸው ናቸው አስተማሪ ጥሩ ነው ብለህ እንድትደመድም የረዱህ ። ዓለምን በበጎ ያሳዩህን ፣ የፍቅር መምህሮችህን ፣. የጠዋት ወዳጆችህን ፣ ገና ነፍስህን ሳትረዳት ያፈቀሩህን ፣ ራስህን መውደድ ሳትጀምር አንተ የእኔ ነህ ያሉህን አመስግን ። ስለ አንድ አምላክ ብለህ ምክሬን ስማ ። ራስህን ከታላቅ ጸጸት ትፈታታለህ ። እኔ ቀኑን እየተሻማሁ ነው ። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን የወሰዱኝን ፣ ስማር ደብተር የገዙልኝን እያሰስሁ ነው ። አንዳንዶቹ ሞተዋል ። ልጆቻቸው ምስጋናውንና ውለታውን ለመቀበል እየጠበቁኝ ነው ። ግድ የለም የእኔን ልምድ ተወዉ እባክህን አመስግን ። ሰው ሐውልት አይደለም ቆሞ አይጠብቅህም ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም.