22. ልጆችን በሥርዓት አሳድግ
ምናልባት እኔ ልጅ የለኝም ይህ ምክር እኔን አይመለከተኝም እያልህ ይሆናል ። ልጆች ከእግዚአብሔር የምንቀበላቸው እንጂ የምንቀማቸው አይደሉም ። ሴት ልጅም የልጅ መንገድ እንጂ የልጅ ፈጣሪ አይደለችም ። መውለድ ጸጋ እንደሆነ አለመውለድም ስጦታ ነው ። አብርሃምና ሣራ እስከ መቶ ዓመት ልጅ አልወለዱም ። እግዚአብሔርን በአንድ ልብ ሁነው ለዘጠናና ለመቶ ዓመት ካገለገሉ በኋላ እግዚአብሔር ልጅ ሰጣቸው ። ልጅ የተቀበሉበት ዓላማም የመሢሑን መምጫ መንገድ ለማሳለጥ ነው ። በሌላ አነጋገር ልጅን ለክርስቶስ ወለዱ ። ለጧሪ ለቀባሪ ሳይሆን ልጅን ለሃይማኖት ወለዱ ። እኛ በልጆቻችን ላይ ካለን ዕቅድ እግዚአብሔር በልጆቻችን ላይ ያለው ዓላማ ይበልጣልና ። ነቢይት ሃና ብዙ ዘመን ልጅ በማጣት አልቅሳለች ። በእግዚአብሔር ቤት ባሉ ምእመናን መሳለቂያ እስክትሆን ድረስ ተሸማቃለች ። እግዚአብሔር ልጅ የሚሰጠን ልጅ ያልወለዱትን እንድናሳቅቅበት አይደለም ፤ ልጅ ችሎታ ሳይሆን ስጦታ ነው ። እመ ሳሙኤል ሃና ለራስዋ ልጅን ስትመኝ ዘገየባት ፤ የዘገየው ልጅ ሲመጣ ግን ለእስራኤል ሕዝብ ትልቅ መልስ የሆነው ሳሙኤል ሆነ ። ዘካርያስና ኤልሳቤጥ የወለዱትን ልጅ አላሳደጉትም ። በበረሃ ያደገው ዮሐንስ መጥምቅ ከመሸ የመጣ ነው ። የእነርሱ ደስታ የእግዚአብሔርን ክንድ ማየትና ነቀፌታቸው ሲወገድ መመልከት ነው ። ያልወለዱ የተመሰገኑበትና ብፁዓን የሚባሉበት ዘመን እንዳለ በማሰብ በመውለድ ብቻ መደሰት እንደሌለ እናስተውል ።
አዎ ልጅ ባትወልድም የምታየው ልጅ በሙሉ ያንተ ነው ። ብዙ ደናግልና መነኮሳት የብዙዎች አባትና እናት ናቸው ። እማሆይ ትሬሣን ታውቃቸዋለህ ። የሚሊየኖች እናት የሆኑ መነኵሲት ናቸው ። ልጅነት ብዙ እንደሆነ ፣ ወላጅነትም ብዙ ነው ። ይህ ዘመን የወለዱ ካልወለዱት በላይ የሚጨነቁበት ነው ። በአጭር ቃል ዘመኑ ልጅ ነጣቂ ነው ። ልጅ የወላጆቹን አሳብ ከሚያንጸባርቀው ይልቅ የዘመኑን አሳብ ማንጸባረቅ ይቀለዋል ። አውቃለሁ ባይነት ስለ ነገሠና በዕድሜ የገፉ የሚናቁበት ባሕል ስለ ተመሠረተ ወላጆች በልጆቻቸው ተከድተዋል ። ወላጅ ልጁን መገሠጽና መቅጣት የማይችልበት የሚያለያይ ዘመን ላይ ደርሰናል ። አዎ ልጆች ተሸማቀው ፣ እንዳይጠይቁ ተደርገው በፍርሃት ማደግ የለባቸውም ። በመኖር ፣ በማፍቀርም ከቀደሙአቸው ወላጆች ግን መማር አለባቸው ። ልጆች ቀለብ ከቤት ፣ ምክር ከደጅ ካደረጉ ቆይተዋል ። ወላጆቻቸውን አንሰማችሁም ተስፋ ቍረጡ እያሉ ነው ። አንዳንድ ጊዜ እኛም በወላጆቻችን ላይ የፈጸምነውን ዓመፃ በልጆች ልንቀበል እንችላለን ። ሌላ ጊዜም ልጅ እንደ ራሱ እንጂ እንደ እኛ አይደለም ። ነጻ ፈቃድ አለውና በራሱ መንገድ ቢሄድ የበደለኝነት ስሜት ሊያሰቃየን አይገባም ። የነቢዩ ፣ የቡሩኩ የዳዊት ልጆች አብዛኛዎቹ ክፉዎች ነበሩ ።
ልጅን ስለቀጣነው ብቻ አይታረምም ፣ ልጅ ከቃል ይልቅ በሕይወታችን የምናስተምረው አዳሪ ተማሪ ነው ። ልጅ ከእኛ ጋር ከሚያሳልፈው ዕድሜ ይልቅ ከሰፊው ዓለም ጋር የሚያሳልፈው ሰዓት ይበልጣል ። ንጹሕና ጉልበት ያለበት ሰዓቱን ቢያንስ ለስምንት ሰዓት በትምህርት ቤት ያሳልፋል ። ቤትን ከማሳመር አገርን ማሳመር ለልጆች ወሳኝ ነው ። አገሩ ከወደቀ ምንም ብንጠነቀቅ ልጆቻችን ገንዘብ አይሆኑንም ። አገርን እየዘረፈ ለልጆቹ የሚቀልብ ብዙ ወላጅ አለ ። በጉቦ ያደጉ ልጆች አእምሮአቸው ጤነኛ አይሆንም ። የሚበሉት ደም እንጂ እንጀራ አይደለምና ። የሰለጠነ አገር ልከን ብናስተምራቸው የሰለጠነ ሱስ ውስጥ ይገባሉ ።
የመጀመሪያ ልጅ የደስታችን መነሻ ነው ። ከዚህ በፊት በልጅ ተደስተን ስለማናውቅ የመጀመሪያው ልጅ ትልቅ ፍስሐ ያመጣልናል ። የመጀመሪያው ልጅ ከልምድ ማነስ የተነሣ በጣም ስለምንጠነቀቅለት ነጻነት የሚያጣ ይሆናል ። እርሱን የሚመስል ልጅ እቤት ውስጥ ስለሌለ ውሎው ከእኛ ጋር በመሆኑ ያለጊዜው ይበስላል ። ፍጹም እንዲሆን ወይም እንደ ትልቅ እንዲያስብ ስንፈልግ ብዙ ዱላ ልናበዛበት እንችላለን ። የመጀመሪያ ልጅ ፈሪ ወይም ቂመኛ መሆኑ የተለመደ ነው ። አሊያም የራሳቸው ጉዳይ ብሎ ቤተሰቡን ችላ የሚል ራስ ወዳድ ይሆናል ። ሌላ ጊዜ ደግሞ እንደ ወላጅ ራሱን ቆጥሮ ቀንበር የሚሸከም ይሆናል ። ሁለተኛው ልጅ ሲመጣ ዓይን ሁሉ ከእርሱ ላይ ይነሣል ። በዚህ ምክንያት በቅንዓት ውስጡ ይጎዳል ። አልበላም እያለ የሚያምፀው የራሱን ጨርሶ የሌላውንም ቢበላ ደስ ይለዋል ። ራሱንም በገዛ ቤቱ ባዕድ ያደርጋል ። አንዳንድ ጊዜ የመጀመሪያ ልጆች ወላጆቻቸውን ክደው አባትና እናቴ አይደሉም እያሉ በደጅ ያወራሉ ። ፍቅር የተነፈጉ ፣ የመጀመሪያውን እንክብካቤ ያጡ ሲመስላቸው የደጅ ኀዘኔታ ለማግኘት በፈጠራ ታሪክ ራሳቸውን ያስተዋውቃሉ ። የሚገርመው የፈጠራ ታሪካቸውን እያመኑት ይመጣሉ ።
የመጀመሪያ ልጅ ላይ ሥራ መሥራት ቀጣዮቹ እንዲባረኩ ያደርጋል ። ቀጣዮቹ ከወላጆቻቸው ይልቅ የበኵሩን ልጅ መከተል ይወዳሉ ። ስለዚህ የመጀመሪያ ልጅን ከመጠን በላይ መንከባከብ ተገቢ አይደለም ። ምክንያቱም አይዘልቅምና ። “የማይዘልቅ ጸሎት ለቅስፈት” እንዲሉ ። ይልቁንም በኵሩ የእግዚአብሔር ነውና ለእግዚአብሔር መስጠት ፣ አገልጋይ ማድረግ ይገባል ። በኵርን ለእግዚአብሔር መስጠት ስንከለክል 12 ወልደን አንዱም የማይወደን እየሆነ መጣ ። ሰንበትን ለእግዚአብሔር ስንከለክል በሰንበት እየሠራንና እየተማርን በረከትና እውቀት የለሽ ሆንን ። እግዚአብሔርን ሰርቆ የበለጸገ ማንም የለም ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 5 ቀን 2016 ዓ.ም.