23. ከሰዎች ጋር ግንኙነትህን አሳምር
“ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።” ሮሜ. 12፡18 ። ሐዋርያው “ቢቻላችሁስ” አለ ። ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም መኖር ከባድ ነውና ። ቢቻለን ከሁሉም ነገድ ፣ ከሁሉም ሃይማኖት ጋር በሰላም መኖር ይገባናል ። ምድር የሁሉም እንጂ የአንድ ሃይማኖትና የአንድ ወገን አይደለችምና ። ለሁሉም እንደ ሥራው የሚፈርድ አምላክ አለና ሳንፈራረድ ከሁሉም ጋር በሰላም መኖር መታደል ነው ። በዚህ ምድር ላይ ልከኛ ነዋሪ የሚባለው ከሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያሳምር ነው ። ከሰዎች ጋር የዝምድና ፣ የሃይማኖት ፣ የጓደኝነት ፣ የሥራ ባልደረባነት ፣ የነጻነት ትግል ፣ የአገር ፍቅር ሊያገናኘን ይችላል ። መቼም ሃይማኖት ላለው ሰው ከዝምድና ሁሉ የሚበልጠው በክርስቶስ ያወቁት ወንድምና እኅት ነው ። ምድራዊ ዝምድና ሁሉ መቃብር ይገታዋል ። በክርስቶስ መዛመድ ግን ከሞትም ባሻገር የሚዘልቅ ነው ። በኖርኩበት ዘመን መንፈሳዊ ዝምድናን የሚያከብር ብዙ አላየሁም ። የሥጋ አባቱን ምሥጢር ደብቆ የሃይማኖት አባቱን እንከን በአደባባይ የሚያወራ ብዙ ነው ። የሥጋ ወንድሙ ቢበድለው ይቅር እያለ የሃይማኖት ወንድሙን ግን ጠልቶ የሚቀር አያሌ ነው ። የእግዚአብሔር ፈቃድ ሰው ከሰው ጋር እንዲኖር ነው ። ከሌላው ጋር ለማበር ሰው መሆን በቂ ነው ። በሽታው ሲመጣ ጥቁርና ነጩን በአንድነት ይፈጀዋል ። በአንድ ዓይነት በሽታ እየታመምን በአንድ ዓይነት ፍቅር መኖር አለመቻል ያሳዝናል ።
ከሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት ለማሳመር ከልብ ሰዎችን መውደድ ቀዳሚው ነው ። ልባዊ ፍቅር ባለበት የመለኮት መገኘት አለ ። በዚህ ዓለም ላይ ብዙ ዓይነት ፍቅሮች አሉ ። እግዚአብሔርን መነሻ ያደረገ የአጋፔ ፍቅር አለ ። ሥጋዊ ስሜትን መነሻ ያደረገ የወንድና የሴት ፍቅር አለ ። ይቅርታን ገንዘብ ያደረገ ጠላትን የምንወድበት ፍቅር አለ ። እኩያነትን ያገናዘበ የጓደኝነት ፍቅር አለ ። ሰዎችን ከልብ ስንወድድ ውስጣችን እውነተኛ እንደ ሆንን ይመሰክርልናል ። ሰዎች በዚህ ዘመን ሲወድዱን እንጠራጠራለን ፣ ሲጠሉን ግን ከልብ እናምናለን ። ፍቅርን መስጠት ብቻ ሳይሆን መቀበል አልቻልንም ። ደግነት እያጠራጠረን ፣ ለምን ቸር ሆኑ እያልን ነው ። መልሰን ደግ ሰው ጠፋ እያልን እናማርራለን ። ስለ ብርቅዬ እንስሳት መጥፋት የሚያለቅሰው ያጠፋቸው ያው የሰው ልጅ ነው ። የገፋነው ደግነት ዛሬ በስእለት የማይገኝ እየሆነ ነው ። ሰውዬው እኔን ከመውደዱ በፊት ቀድሜ መውደድ ታላቅነት ነው ። የእግዚአብሔር ፍቅር መፍሰሻ ይፈልጋል ፣ በእኛ ወደ ሌሎች ለመፍሰስ ይሽቀዳደማል ። ሰዎችን በሁለተኛ ደረጃ በግልጽነት መቅረብ ያስፈልጋል ። በዚህ ዓለም ላይ ተሸፍኖ የሚሰነብት እንጂ ተከድኖ የሚቀር ምንም ነገር የለም ። ግልጽነታችን ግን የእብደት ታናሽ ወንድም እንዳይሆን መጠንቀቅ አለብን ።
ለሰዎች መገኘት አለብን ። ይህ ሦስተኛው የግንኙነት መርህ ነው ። ሰዎች ለእኛ የሚያስፈልጉን ቀን እንዳለ ሁሉ እኛ በምናስፈልጋቸው ቀን ሳይጠሩን መገኘት አለብን ። እግዚአብሔር መከራችንን በተለያየ ቀን ያደረገው አጽናኝ እንዳይታጣ ብሎ ነው ። ሲታመሙ ፣ ሲታሰሩ ፣ እንግድነት ሲመጡ ፣ ኀዘን ላይ ሲቀመጡ አለሁ ማለት አለብን ። በዚህ ዓለም የቅርብ ዘመድ የሥጋው ሳይሆን የቅርብ ጎረቤት ነው ። ኑሮአችን ገለልተኛ መሆን የለበትም ። ማንም እንዳይደርስብኝ ብለን በር ዘግተን መኖር ሕይወትንም ሞትም የሚያበላሽ ነው ። የሰለጠነው ዓለም የፈጠረው የግለኝነት ኑሮ ሰውዬው ሞቶ እንኳ ሬሳው እንዲበላሽ ያደረገ ነው ። መሰልጠን የምንለው ገደብ ከሌለው ለዚህ የሚያደርስ ነው ።
ሁሉን ነገር ክፍት ማድረግ የለብንም ። ይህ ዓለም የልክ ዓለም ነውና ለወዳጆችም ልክ መስጠት አለብን ። ሁሉም ነገር የሚወራው ፣ ሁሉም ነገር ክፍት የሚደረገው ለእግዚአብሔርና ለእግዚአብሔር ሰው ብቻ ነው ። አንዳንድ ጊዜ የትዳር ጓድም የማያውቁትና የማይሸከሙት የሕይወት ምሥጢር ይኖረናል ። ሰዎች ሁሉንም ነገራችንን የማወቅ መብት የላቸውም ። ንስሐና ጸሎት የሰውን ምሥጢራዊ ሕይወት የሚያግዙ ናቸው ። ሄደው እንዲመለሱ መፍቀድ አለብን ። ሰዎች በጣም መልካም ስንሆንላቸው ከዚህ የተሻለ መልካም ሌላ ቦታ አለና ልሂድ ብለው ያስባሉ ። ሄደው እንዲመለሱ መፍቀድ አለብን ። አንዳንድ መልካሞች ግን ከሸኙ በኋላ በሩን ዳግም አይከፍቱምና መጠንቀቅና አክብሮ መያዝ ይገባል ። ሰዎች እንዲሄዱ ካልፈቀድንላቸው ብዙ ነገሮች ይከሰታሉ ። የመጀመሪያው በልቡ የሄደን ሰው በአካል መያዝ በድን ታቅፎ መኖር ነው ። ሁለተኛ እኛ በእግዚአብሔር ብቻ እንደምንኖር ሁሉም ማወቅ አለበት ። እየወደዱን እንጂ እያስፈራሩን መኖር የለባቸውም ። ይህ ልካቸውን አጥተው እንዲፋንኑና እንዲባልጉ ያደርጋል ።
ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት በእውነት ሲመለሱ በይቅርታ መቀበል ነው ። አንዳንድ ይቅርታዎች በውስጣቸው ክፋት ሊኖራቸው ይችላልና ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ። ያልጨረሱትን ክፋት ለመጨረስ በይቅርታ ስም የሚመጡ ፣ እኛን አባብተው ጥቅም ፍለጋ እንደ ድመት የሚመለሱ ይኖራሉ ። እውነተኛ ይቅርታዎችን መቀበል ተገቢ ነው ። እግዚአብሔር ከሰው ጋር የሚኖረው ሰውን ይቅር እያለው ነው ።
ግንኙነትን የሚጎዱ ነገሮች አሉ ። የጋራ ፍቅር አለመኖር የግንኙነት ጸር ነው ። በአንድ ሰው ፍቅር የሚቀጥል ወዳጅነት ፣ የሚቆም ቤት ፣ የሚሠራ ተግባር አይኖርም ። የእኔ ፍቅር ብቻውን በቂ ነው በማለት ወደ ትዳር መግባት ለመውጣት ነው ። ጠላትህን ውደድ በሚል ፍቅር ወደ ትዳር ቢገባ ጉዳቱ የከፋ ነው ። አለመከባበር የግንኙነት አፍራሽ ነው ። ሐሜት ግንኙነትን በብርቱ ይጎዳል ። ስለ ወዳጅህ መልካምነት በሌላ ቦታ ፣ ስለ ጉድለቱ ግን ለራሱ ተናገር ። ጥቅመኛነት ወዳጅህን ለጉዳይህ ብቻ መውደድ አንድ ቀን ለዘላለም እንድትለየው ያደርግሃል ። ሞኝም የሚነቃበት ቀን አለ ። ራስ ወዳድነት የግንኙነት ትልቅ ጸር ነው ። ራስን ብቻ ማዳመጥ ፣ የራስን ፍላጎት ብቻ መከተል ሌጣ ሰው ያደርጋል ። ጨካኝነት የግንኙነት ጎጂ ጠባይ ነው ። ወደቀ ብሎ ወዳጅን መርገጥ ፣ ተራቆተ ብሎ ለዓለም ማሳየት ይህ ከባድ ወንጀል ነው ። አላባብሶ ኑሮ የወዳጅነት ጸር ነው ። ተወው ተይው መባባል ግንኙነትን ይጎዳል ። በሁለት ዓይን መተያየት ፣ በሁለት ጆሮ መስማት የግንኙነት ጸር ነው ። አንዱ ዓይን ስህተትን ሲያይ አንዱ መጨፈን አለበት ። ሰዎች አንድ ጊዜ እንኳ እንዲሳሳቱ መፍቀድ አለብን ። የሃያ የሠላሳ ዘመን ጓደኝነትን በዛሬ ክስተት አፈር ማልበስ አንገት የለሽ መሆን ነው ።….
ይህን የግንኙነት አሳብ ብቀጥለው ደስ ባለኝ ነበር ፣ የአገሬ አንባቢ ስልቹ ነው ። የሚጠቅመውን ትቶ የማይጠቅመውን የሚያስስ ነው ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 12 ቀን 2016 ዓ.ም.