የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት 4

3- ንጽሕናህን ጠብቅ

ንጽሕና ከሃይማኖት ጋር በጣም የተያያዘ ነው ። በአይሁድ ፣ በክርስትና ፣ በእስልምና ሃይማኖት ንጽሕና ትልቅ መስፈርት የሚሰጠው ነው ። ሃይማኖት ስለ ሥጋና ነፍስ ንጽሕና የሚያስተምር ነው ። “ገላ ቢያድፍ በውኃ ፣ ነፍስ ቢያድፍ በንስሐ” እየተባለ የሚነገረው በሥጋም በነፍስም ንጹሕ መሆን ስለሚገባ ነው ። የብሉይ ኪዳን የሥርዓት ሕግ በዋናነት ንጽሕና ላይ አትኩሮት ያደርጋል ። ስለ ማኅበረሰብ ጤናም ግድ ይለዋል ። እግዚአብሔር ውኃን የፈጠረው እንድንታጠብ ነው ። እያንዳንዱ እስራኤላዊ ግላዊ ንጽሕናውን መጠበቅ እንዳለበት ትእዛዝ ተሰጥቶታል ። ተላላፊ በሽታ የያዘው እንደሆነው የማግለያ ቦታዎች ተለይተዋልና እስኪድን ድረስ በዚያ ማሳለፍ ነበረበት (ዘሌዋ. 15)። ዛሬ ወረርሽኝ ሲከሰት የማቆያ ጣቢያ ሲዘጋጅ እናያለን ። ይህ ግን ከዛሬ ሦስት ሺህ ዓመት ጀምሮ በእግዚአብሔር ሕዝብ የተለመደ ነበር ። የማኅበረሰብን ጤና መጠበቅ ተገቢ ነው ። ተላላፊ በሽታ ይዞ ፣ ያንን መደበቅና ሌላውን ሰው ተጠቂ ማድረግ እንደ መግደል ይቆጠራል ። እስራኤላዊ ሰፈሩን የማጽዳት መለኮታዊ ትእዛዝ ነበረበት ። ዛሬ ራሱን የሚያጸዳ ሰው ቤቱን ያዝረከርካል (ብዙ ጊዜ የቆንጆ ቤት ዝርክርክ ነው)። ቤቱን የሚያጸዳ ደግሞ ሰፈሩን ያቆሽሻል ። በየመንገዱ የበሉበትን ተወጋጅ ነገር የሚጥሉ ፣ ከቤታቸው ወጥተው ደጅ ላይ የሚሸኑ ብዙ ናቸው ። እኛ ያቆሸሽነውን የሚጠርጉ አንዳንድ ልበ ቅን ሰዎች በየሰፈሩ አሉ ። እነዚህን ሰዎች ከማመስገን ይልቅ እንደ ተለከፉና በየቆሻሻው እንደሚንከራተቱ መቍጠር ይቀናናል ።

ሰፈሩን የማያጸዳ ክርስቲያን በብሉይ ኪዳን ቢሆን ትልቅ ቅጣት ይጠብቀው ነበር ። የአንድ አገር ሥልጣኔ የሚለካው በንጽሕናው ፣ ቆሻሻን በሚያስወግድበት መንገድና ቆሻሻን እንደ ሀብት በሚጠቀምበት አሠራር ነው ። በእግዚአብሔር ድንኳን በሚቀርበው አገልግሎት ተረፈ መሥዋዕቱን የማስወገጃ ትእዛዝ ነበረው ። ከሰፈር ውጭ አውጥተው እንዲጥሉ ወይም እንዲቀብሩ ታዘዋል ። ንጽሕናን መጠበቅ ፣ ቆሻሻን በተገቢው መንገድ ማስወገድ አምልኮት ነው ። አምልኮ መዘመር ፣ መቀደስ ብቻ አይደለም ። ንጽሕናን መጠበቅም አምልኮ ነው ። ሥጋዊ ንጽሕና ማለታችን ነው ። ገላ መታጠብ ፣ ልብስ ማጠብ ፣ ቤት መጥረግ እያልን ነው ።

በቃና ዘገሊላ ስድስት የድንጋይ ጋኖች ነበሩ ። እንደ አይሁድ ልማድ የማንጻት ሥርዓት ለመፈጸም የተቀመጡ ነበሩ ። ሰርገኛው ሲገባ እየታጠበ መግባት ነበረበት ። ዛሬ እንኳ ሰርግ ቤት ውኃ አይቀመጥም ። ንጽሕና ትልቅ ዋጋ ያለው ነገር ነው ። ጌታችን ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ የለወጠው በእነዚህ ጋኖች ላይ ውኃ ከተጨመረ በኋላ ነው ። (ዮሐ. 2 ፡ 6 ።) በምሴተ ሐሙስ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቧል ። የቍርባን ቅዳሴ ሲከናወንም በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት መታጠብ ግድ ነው ። እየበረታን ስንመጣ እያንዳንዱ ቀዳሽ ልብሰ ተክህኖውን ከመልበሱ በፊት ሙሉ ገላውን ታጥቦ መሰየም አለበት ። ይህ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ይደረጋል ። በእስልምናም ከጸሎት በፊት መታጠብ ግዳጅ ነው ። በአላዋቂነት “እግዚአብሔር ያለው ልባችሁን ታጠቡ ነው ፣ እግራችሁን አይደለም” እያልን እንተቻለን ። እኛም እግር መታጠቢያ ቢኖረን ክብር እንጂ ውርደት አይደለም ። ጫማ አውልቀን ስለምንገባ ፣ ስለምንሰግድ መንጻት ግድ አለብን ። በእውቀትም በሕይወትም የበረቱ አባቶች ንጹሐን ነበሩ ። ለመጸለይም ንጹሕ አካልና አካባቢ ያስፈልገናል ። ተባይ እየጨፈረብን መጸለይና መመሰጥ ሊኖር አይችልም ። በግብጽ ላይ ከወረደው መቅሰፍት አንዱ ቅማል ነው (ዘጸ. 8 ፡ 16) ። ተባይን እንደ በረከት የሚያይ ካለ ጤንነቱ መገምገም አለበት ።

ንጹሕ ልብስ የሚለብስ ፣ ሽቱ የሚቀባ መነኵሴ ሲገጥመን እንደ ዓለማዊ ሰው ማየት የተለመደ ነው ። የሽቱ ቅመማውን ሳይቀር ለሙሴ ያስጠናው ራሱ እግዚአብሔር መሆኑን እንዘነጋለን (ዘጸ. 30፡23፣34)። ብፁዕ ቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሽቱ ተቀቡ ተብሎ መጽሐፍ ተጽፎባቸዋል ፣ ብዙ ስድብ አስተናግደዋል። ንጽሕናን መጠበቅ ዓለማዊነት ሳይሆን መንፈሳዊነት ነው ። ዓለምን ከንቱ ነው የምንለው ለገንዘብ ባለመስገብገብ ፣ ወንድምን ከወደቀበት በማንሣት እንጂ በመቆሸሽ አይደለም ። የክርስትናው ትእዛዝ ራስህን ካድ እንጂ ራስህን ጣል የሚል አይደለም ። መቆሸሽ መንፈሳዊነት ሳይሆን ስንፍና ነው ። ሁላችንም ብንሆን ንጹሕ ሰው ይማርከናል ። መልካም መዓዛ ያለውንም አንጠላም ። እኛም ተወዳጅ ሰዎች የምንሆነው ንጽሕናችንን በመጠበቅ ነው ። ልንሸት የሚገባው ቆሻሻ ሳይሆን ውኃ ፣ ውኃ ብቻ ነው ። ንጽሕናን አለመጠበቅ ድብርት ውስጥ ይከታል ። አጠገባችን ላለውም ሰው ፈተና መሆን ነው ። “ሰውን ሲወዱ ከነንፍጡ ነው” የሚባለው አይሠራም ። በዚህ ዘመን ሰውን መውደድ ንፍጡን ጠርጎ ነው ። እኛ ከነንፍጡ ልንስመው እንችላለን ። የሚበዛው ሰው ግን ይጸየፈዋል ። ይልቁንም ጓደኛ ሆኖ የጓደኛውን የንጽሕና ጉድለት የማይነግር ካለ ጓደኛ አይደለም ።

ዐፄ ቴዎድሮስ አንድ ባለጉዳይ በፊታቸው ቆሞ ንጽሕናውን በቅጡ ስላልጠበቀ ፣ “ጓደኛ አለህ ወይ?” ብለው ጠየቁት ። እርሱም ቢያዝኑልኝ ቢፈርዱልኝ ብሎ መልካም ጓደኛ አለኝ ብሎ ነገራቸው ። ያም ጓደኛ ተጠርቶ መጣ ። “እንዴት ጓደኛው ከሆንህ ንጽሕናውን እንዲጠብቅ አልመከርከውም ?” ብለው አርባ ጅራፍ ገረፉት ። ዛሬም ጓደኛው ራሱን ሲጥል ዝም ብሎ የሚመለከት ቅጣት ይገባዋል ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 12 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ