የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት 5

…. ንጽሕናን መጠበቅ

ነጻነትን ከሚሰጠን ነገር አንዱ ንጽሕናን መጠበቅ ነው ። ገላችን ከቆሸሸ ፣ ልብሳችን ንጹሕ ካልሆነ ራሳችንን እንኳ መውደድ እንቸገራለን ። አንድ የተሟላ ሰው ላዩም ውስጡም ፣ ሥጋውም ነፍሱም ንጹሕ ሲሆኑ ነው ። ቤተ መቅደስ ንጹሕ መሆን አለበት ። በየትኛውም ሃይማኖት በየትኛው አገር ያለ መቅደስ ንጽሕና ቀዳሚ መገለጫው ነው ። ሰው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነው ። በወርቅና በብር የተገዛ ሳይሆን በእግዚአብሔር ልጅ ክቡር ደም የተገዛ ሕንፃ ሥላሴ ፣ ታቦተ መንፈስ ቅዱስ ፣ ማኅደረ መለኮት ነው ። ስለዚህ ንጹሕ መሆን አለበት ። ይልቁንም የሃይማኖት አባቶች የንጽሕና ምሳሌ ናቸው ። ሕዝቡንም ስለ ንጽሕና ሊያስተምሩት ይገባል ። እግዚአብሔርን የሚወድድ እግዚአብሔር የፈጠረውን ይወድዳል ። ተፈጥሮ የእግዚአብሔር የፍቅሩ ውጤት ነው ። በንጽሕና ጉድለት ተፈጥሮ እየተጎዳ ነው ። ወንዞች ይበከላሉ ። ውቅያኖሶች በተለያዩ ዝቃጮች ምክንያት በውስጣቸው የያዙትን ፍጥረት እያጡ ነው ። ንጽሕና የፍጥረት ሕይወት ነው ። እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው ፍጥረትን ይወዳል ። የምድሪቱ ትልቅ ፍጡርና ባለ አደራ የሆነው ሰውም ተፈጥሮን የመጠበቅና የመንከባከብ ግዳጅ አለበት ።

ንጽሕናን ለመጠበቅ የተሻለ አስተሳሰብና የሞራል ግንባታ እንዳለን የሚጠበቅ ነው ። ነገር ግን መልእክትን ማስተላለፍ ስለሚገባ ስለንጽሕና ማስተማር ይገባናል ። በተለያዩ ትልልቅ ተቋማት ሠራተኞች ከመቀጠራቸው በፊት ይህ ትምህርት ይሰጣል ። የተከበሩ ሰዎች ሾፌር የሚሆኑ በታላቅ ጥንቃቄ ስለንጽሕና ትምህርት ይሰጣቸዋል ። ሕዝብን በማገልገል ላይ ያሉና ዓለም አቀፍ ተቋማት ትኩረት ሰጥተው ስለንጽሕና ያስተምራሉ ። እኛ ግን የእግዚአብሔር ቃል ስለ ሁሉም የሕይወት ክፍል የሚናገር ነውና መጽሐፉን መሠረት አድርገን እንናገራለን ። የቀደሙ አባቶችም ብሉያትና ሐዲሳትን ብቻ ሳይሆን ንጽሕናን መሠረት አድርገው ያስተምሩ እንደነበር እናውቃለን ።

አንተ ብርቱ የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ በምድር ላይ እንደ ተራ ሰው ፣ እንደ መንገደኛ ፣ እንደ ዘዋሪ ሳይሆን እንደ ልዑል የተቀመጥህ ነህ ። ኑሮ ከርታታ ቢያደርግህ እንኳ ግብህ ሰማይ ነው ። የንጉሥ ልጅ ነህና ራስህን መጠበቅ አለብህ ።

መኝታህ ንጹሕ ይሁን ። በዚህ ዓለም ላይ በትክክል የምትጠቀመው አልጋህንና መኪናህን ነው ። ስለዚህ መኝታህ ንጹሕ መሆን አለበት ። አልጋ ላይኖርህ ይችላል ። ባለጠጋ ስትሆን መሬት ተኛ ተብለህ ትታዘዛለህ ። ስላለህ ትጠቀማለህ ማለት አይደለም ። ብዙ ሰው የገንዘቡ ተመጋቢ ሳይሆን ተመልካች ነው ። ብቻ መኝታህ ንጹሕ ይሁን ። በየሳምንቱ አንሶላህን ቀይር ። የትራስ ጨርቅህ ውኃ ፣ ውኃ ብቻ መሽተት አለበት ። ከመኝታህ እንደ ተነሣህ ወዲያው አልጋህን አታንጥፍ ። ገልጠህ ቢያንስ ለአንድ ሰዓት ነፋስ እንዲያገኝ አድርግ ።

የራስህን ንጽሕና ጠብቅ ። ከመኝታህ እንደ ተነሣህ ታጠብ ። ጥርስህን አጽዳ ። የምንበላው ምግብ ቀለም ስላለው ያንን በመፋቂያ ፣ በጥርስ ክፍተት መሐል የሚጠቀጠቀውን ደግሞ በብሩሽ አጽዳ። ከመኝታ ስትነሣና ወደ መኝታ ስትሄድ ጥርስህን ማጽዳት አስፈላጊ ነው ። ማንኛውንም ምግብ ከበላህ በኋላ አፍህን በውኃ ተጉመጥመጥ ። እግዚአብሔር የማሽተት ጸጋን የሰጠን ራሳችንን እንድንቆጣጠር ነው ። ስለዚህ ገላህን ፣ ልብስህን በማሽተት ንጽሕናውን አረጋግጥ ። ሰዎች ቢታዘቡህ እንጂ አይነግሩህምና ራስህን አዳምጥ ። በየዕለቱ የጫማ ወይም የእግር ሹራብህን/ካልሲህን/ ቀይር ። በየዕለቱ እግርህን ታጠብ ። በቁም እያለህ እግርህ ሞቶ መሽተት የለበትም ። ንጽሕናን ለመጠበቅ እጮኛ መያዝ ፣ ስብሰባ መሄድ አያስፈልግህም ። ለራስህ ክብር ንጹሕ ሁን ።

እንደ ሥራህ ጠባይ መታጠብ አለብህ ። ቆሻሻ ለመንካት ቅርብ የሆነ ሥራ ከሆነ በየዕለቱ መታጠብ ግድ ይላል ። ሽቱም የሚጣፍጠው ንጹሕ ገላ ላይ ሲያርከፈክፉት ነው ። በቆሸሸ ገላ ላይ ሽቱ ቢቀቡ ይከፋል እንጂ አይሻልም ። አካባቢያችን ሲቆሽሽ ዝንቦች ተዋጊ ሆነው ይመጣሉ ። አጽዱ ማለታቸው ነው ። ጅቦች ቤታችን ድረስ አንኳኩተው የሚመጡት ቆሻሻ ካላነሣን ነው ። በደመ ነፍስ ያሉት ፍጥረታት ሳይቀር ስለ ንጽሕና እንድንተጋ ያደርጉናል ። ከሁሉ በላይ ጤናችንን ፣ ክብራችንን ፣ ተወዳጅነታችንን ለመጠበቅ ንጽሕና አስፈላጊ ነው ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 17 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ