የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት 8

መልካም ልማድን አዳብር

ዕለታዊ ማስታወሻ የመጻፍ ልማድ ፣ ውሎህ እንዴት እንደ ነበር የመመዝገብ ሥርዓት ይኑርህ ። የእጅና የእግር ጥፍርህን ተከታትለህ ቍረጠው ። ብዕር ወይም ጣትህን አፍህ ውስጥ አታስገባ ። ሁልጊዜ መስተዋት ተመልከት ። በዛሬ ጊዜ የገጽህን/የፊትህን ሁኔታ በትክክል የሚነግርህ መስተዋት ነው ። መስተዋት ላይ ብዙ አትቆይ ። ነገ አፈር መሆንህን እያሰብህም ሁልጊዜ ካልተሽቀረቀርኩ ብለህ አትጨነቅ ። ወዳጅህ የሞተ ቀን ባሕር አቋርጠህ ፣ አውሮፕላን ተሳፍረህ ከምትመጣ በቁሙ ብትጠይቀው የተሻለና እውነተኛነት ነው ። የመቃብር ላይ ድራማ መቆም አለበት ።

ከሌለህ ነገር ላይ አትቆጥብምና ካለህ ነገር ላይ አስቀምጥ ። መጽሐፍ ስጡ አለ እንጂ በትኑ አላለም ። ለልጆችህ ቤት ለመሥራት ፣ መኪና ለመግዛት ፣ ንብረት ለማስቀመጥ ፣ በስማቸው አክስዮን ለመግባት አትጨነቅ ። ልጆችህ የሚኖሩበትን መንገዱን አሳያቸው ። ልጆችህ በምትሰጣቸው የገንዘብ ብዛት የሚወዱህ እየመሰለህ ትታክታለህ ፣ ልትገዛቸው የፈለግህ ስለሚመስላቸው የበለጠ ይጠሉሃል ። ልጆችህን አስተምራቸው ፣ ሕይወትን እንዲጋፈጡ ጨክነህ ልቀቃቸው ።

ሕፃናትን አትጥላ ። በአሁን ጊዜ የማይበድሉን ምድራውያን መላእክት እነርሱ ናቸውና ። ዝም ብሎ የተቀመጠን ውሻ አትደብድብ ። አህያ ብዙ ዋጋ የከፈለች ፣ ነገር ግን ስሟና ሥራዋ ክብር ያላገኘ እንስሳ ናትና እርስዋንና እንስሳትን ስለማሳረፍ ሥራ ። አላዋቂ ሰው ቢበድልህ እንደ አዋቂ አድርገህ ግብግብ ውስጥ አትግባ ። ሰው የሚሰጥህ የልኩን ነውና አትደነቅ ። ቀጥሎ ምን ይሆን ብለህ አትጨነቅ ፤ ከዚህ በላይ የሚያስጨንቅ ነገር ቀጥሎ አይሆንም ። የታሸጉ ምግቦችን አታዘውትር ። ጣፋጭ ነገሮችን ቀንስ ። የተለያዩ ጥራጥሬዎችን በአንድነት ደባልቀህ አብስለህ ተመገብ ።

ለሰዎች ገንዘብ ስትሰጣቸው ከግንዛቤ ጋር ይሁን ። ከበርህ ስትወጣ ጀምሮ ላለው ድሀ ፣ ለሚጠብቀው ዘበኛ ትንሽ ትንሽ እየሰጠህ ሂድ ። ካላካፈልህ ነገ ተደራጅቶ ሙሉ ንብረትህን ያወድመዋል ። ስጡ ይሰጣችኋል የተባለው ጠላት ለመቀነስም ነው ። ስትሰጥ ሰላም ይሰጡሃል ። ስትራመድ ለየት ያለ ቄንጥ አትጠቀም ። ቀና ብለህም ሂድ ። አንገትህን መስበር ያለብህ ለአምልኮ ብቻ ነው ። ስትተኛ በግራ ጎንህ እግርህን ዘርግተህ መተኛትን አዘውትር ። በጾም ወራት መሬት ላይ መተኛት ትሕትናም ጤናም ነው ። ጾም ነው ብለህ አፍን ሳትታጠብ ፣ ጥርስህን ሳትቦርሽ እየሸተትህ አትውጣ ። ጾመኛ ይቀባባ ተብሎአልና (ማቴ. 6 ፡ 18) ።

ሌሊት ነቅተህ እንቅልፍ እንቢ ካለህ ቃለ እግዚአብሔር ከፍተህ ስማ ። አሳብህን ሰማያዊ አሳብ ይቆጣጠረዋል ። ሰላም ስለምታገኝ ትተኛለህ ። የምትበላውን ምግብ አስቀድመህ እየው ። ለመቆጣጠር ብቻ ሳይሆን ምግብ ቀለም አለውና የዓይን ጥጋብ ነው ። ቀጥሎ አሽትተው ። ምግብ መዓዛ አለው ። ተበላሽቶ እንደሆነም ትለየዋለህ ። በጥቂት ቅመሰው ። ከዚያ በኋላ ተመገበው ።

የሳምንት መርሐ ግብርህን አውጣ ። ከመርሐ ግብርህ አንድ መጽሐፍ ለመጨረስ እቅድ ይኑርህ ። አንድ ታማሚ ወይም እስረኛ ለመጠየቅም ለራስህ ግዳጅ ስጠው ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ