የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የመኖር ኃይል

ቤተ ጳውሎስ ቅዳሜ ሰኔ ፲/፳፻፬ ዓ.ም.
መኖር ኃይልን ይጠይቃል፡፡ መኖር ጦርነት ነው፣ ትጥቅ ይፈልጋል፣ መኖር ጥያቄ ነው መልስ ይፈልጋል፡፡ መኖር ትግል ነው፣ ገላጋይ ይፈልጋል፣ መኖር ክስ ነዉ ፈራጅ ይፈልጋል፡፡ መኖር ዕዳ ነው፣ ከፋይ ይፈልጋል፡፡ መኖር ጉዞ ነው፣ ጀልባ ይፈልጋል፡፡ መኖር ናፍቆት ነው፣ ማግኘት ይፈልጋል፡፡ መኖር ጥማት ነው፣ እርካታ ይፈልጋል፡፡ መኖር መራቆት ነው፣ ሸማ ይፈልጋል፡፡ መኖር ዱር ነው፣ መንገድ ይፈልጋል፡፡
የጦርነቱ ድል፣ የጥያቄው መልስ፣ የትግሉ ዕረፍት፣ የክሱ ፍርድ፣ የዕዳው ክፍያ፣ የጉዞው ታንኳ፣ የናፍቆቱ ግኝት፣ የጥማቱ እርካታ፣ የራቁትነቱ መሰወሪያ፣ የዱሩ ፈለግ እምነት ነው፡፡ እምነት ያለው ብቻ ስለ ድል ያወራል፣ በመልስ ይኖራል፣ በመቤዠቱ ይደላደላል፣ ስለ መንገዱ ሳይሆን ስለ ግቡ ይናገራል። ስለ ሁኔታው ሳይሆን ስለ እውነታው ያስባል፣ ናፍቆቱ ይታገሣል፣ ጥማቱ ይረካል፤ በዱር መንገድ ያገኛል። ሁልጊዜ ጦርነት ከሆነ ሕይወት ያለ ድል አስደሳች አይደለችም። የድሉ ምሥጢር እምነት ነው።

እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝበትን ነገር ስንመርጥ ውስጣዊ ብርታት እናገኛለን። የእግዚአብሔር ደስታ ኃይላችን ነው ተብሎ እንደ ተጻፈ እግዚአብሔር ከአገልግሎታችን፣ ከገንዘባችን ይልቅ በእምነታችን ደስ ይለዋል። /ነህ ፰፣፲፤ዕብ.፲፩፣፮/። ቁሳዊውን ዓለም፣ ምድራዊውን ጌጣጌጥ፣ የሚታየውን ክብር፣ የሚያልፈውን የሥጋ ትግል የምናሸንፈው በእምነት ነው። የማይታየው እምነት የሚታይ ድል አለው። የማይታየው የእምነት አጥር የሚታየውን ጠላት ይመልሳል።
ሰዎች ለመኖር አቅም ያስፈልጋቸዋል። የኃይል ምንጩ ደግሞ በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት ነው። ለሚያምን ሁሉ ይቻላል ተብሎ እንደ ተጻፈ በእምነት ባሕር ተከፍሎአል፣ በእምነት መሐን አፍርታለች፣ በእምነት ከሞተ አካል ሕይወት ተገኝቷል፣ በእምነት የአንበሶች አፍ ተዘግቷል፣ በእምነት ነገሥታት ተማርከዋል፣ በእምነት ተቃዋሚዎች ደጋፊዎች/ሰባኪዎች ሆነዋል፣ በእምነት እሳቱ መናፈሻ ሆኗል፣ በእምነት ባሕር የሚረገጥ ጎዳና ሆኗል፣ በእምነት ተራራ ተነቅሏል፣ በእምነት የወኅኒው ደጃፍ ተከፍቷል፣ በእምነት ዓለም ተሸንፏል፡፡ ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፣ ኃይልን ተሞልቶ መኖር፣ ተግባርን በውበት መፈጸም አይቻልም።
ዛሬ ብዙ የከበቡን ነገሮች አሉ፣ በየዕለቱ የምንሰማውም አቅም የሚጨርስ ነው። ከንጉሥ እስከ ጳጳስ፣ ከጌታ እስከ ሎሌ፣ ከምሁር እስከ መሃይም፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከሽማግሌ እስከ ሕጻን… ሁሉም በክፋት አንድ የሆኑበት፣ መልካምነት የቀሚሳቸውን ዘርፍ ሲነካ እንኳ የሚያራግፉበት፣ ቅንነት ለምኔ የሚሉበት፣ ዓለም ለእኔ እያሉ የሚዘፍኑበት ነው። በሚታየውና በሚሰማው የሰው ውስጡ ደክሟል። እምነት ግን ከሚሰማው ባሻገር የምትሰማ የአምላክ ዜማ፣ ከሚታየው ጀርባ ያለች የክርስቶስ ውበት ናት። ሳናስበው ከእምነት ወጥተን በማየት ሕግ ተቀምጠናል። የሚታየው አድካሚ፣ የማይታየው የኃይል ምንጭ ነው። የሚታየው ተስፋ ቢስ፣ የማይታየው የፍቅር ሙላት ነው።
እምነት ሦስት ዓይነት ነው ብለን መክፈል እንችላለን፡-
፩. የሚያድን እምነት፡– « በወልድ ያመነ የዘላለም ሕይወት አለው።» /ዮሐ.፫፣፴፮/
፪. የሚያኖር እምነት፡- «ጻድቅ በእምነት ይኖራል።»/ሮሜ.፩፣፲፯/
፫. የስጦታ እምነት፡- «እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥…» /ሮሜ ፲፪፣፫/
የሚያድን እምነት
ኢየሱስ ክርስቶስ የነፍሴ ጌታ እና መድኃኒት ነው ብሎ ማመን ይህ የሚያድን እምነት ነው። «ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤» እንዳለችው ቅድስት እናት ክርስቶስን ጌታ እና አዳኝ ብሎ መቀበል፣ ሞቱ ሕይወቴ ነው ብሎ መደላደል ይህ የሚያድን እምነት ነው/ሉቃ.፩፣፵፯/። በምድር በሰማይ የምንኖርበት ምሥጢሩ ይህ በክርስቶስ ያለን እምነት ነው። ስለ አንዱ አምላክ አይሁድ በምኩራብ፣ እስላሞች በመስጊድ ያምናሉ። ክርስትናን ልዩ የሚያደርገው በክርስቶስ ማመን ነው።
የሚያኖር እምነት
መኖርና በትክክል መኖር ልዩነት አለው። በዓለም ላይ ያሉ ነገር ግን የማይኖሩ ቋጥኞች አሉ። ሰው ግን ያለ ብቻ ሳይሆን የሚኖር መሆን አለበት። ለመኖር እምነት ያስፈልጋል። ለመቀደስ፣ የዓለምን ፈተና ድል ለመንሣት፣ የክፋት ሠራዊቶችን ለማሸነፍ እምነት ያስፈልጋል። በክርስቶስ የጸደቀ ሰው የሚኖረውም ከእርሱ በሚያገኘው ኃይል ነው።
የስጦታ እምነት
ይህ እምነት ተራራን የሚያፈልስ፣ በባሕር ውስጥ ጎዳና፣ በጨለማ ውስጥ ብርሃን ይገኛል ብሎ የሚፎክር ነው። ይህ የስጦታ እምነት ሁሉ ሰው የለውም። የተሰጣቸው ግን እኛ ስለ ጦርነት ስናወራ እነርሱ የድሉ መዝሙር ይደርሳሉ፣ እኛ ስለ ችግር ስናወራ እነርሱ መፍትሔው ይታየኛል እያሉ ይዘምራሉ። ወደ ኋላ ስንል ያደፋፍራሉ። እኛ ምን መጣብን? ስንል ነገር ሁሉ ለበጎ ነው እያሉ ያበረቱናል።
የእምነት ጥቅም
እምነት ጥቅም አለው። የእምነት ጥቅሙ፡-
፩. ለመዳን
፪. የጸሎትን መልስ ለማግኘት
፫. የመኖርን አቅም ለመሞላት
፬. ዓለምን ለማሸነፍ
፭. ፈተናን ድል ለመንሣት
፮. በማያቋርጥ ተስፋ ለመኖር
፯. ርኩሳን መናፍስትን ድል ለመንሣት
፰. በማያምኑ መካከል ለማመን
፱. እውነትን ለመመስከር
፲. ለእውነት ዋጋ ለመክፈል እምነት አስፈላጊ ነው።
የእምነት ማጠናከሪያዎች
እምነትን የጣለ ሰው መነጽሩን የጣለ የዓይን በሽተኛን ሰው ይመስላል። የሚታየው የለውም። በቅርብም በሩቅም የሚታየው ነገር እያጣ ይጨነቃል። ሰዎች እዚያ ማዶ ያለው ተፈጥሮ አቤት ውበቱ ቢሉትም በዓይን የሚያዩትን ነገር በጆሮ ማጣጣም ከባድ ነውና ማጣጣምና መጥገብ አይችልም። አንዳንዶች እምነት የላቸውም፣ ሌሎቹ እምነታቸው ጎደሎ ነው፣ ጎደሎ ነገር እንደሚንቦጫቦጭ እንዲሁም ሙሉ እምነት የሌለው ሰው እንደተንገላታ የሚኖር ነው። የማያምኑ እየተኙ ጎዶሎ እምነት ያላቸው ግን እንቅልፍ ያጣሉ። ጎዶሎ እምነት ካለማመን በላይ ያሰቃያል። መሐል ላይ ያለ በሁለቱም እንደሚጠቃ እምነተ-ጎዶሎም በግራና ቀኝ ውጊያ የሚሰቃይ ነው።
የፍርሃት ምንጩ ጠላትን ማተለቅ ሲሆን የእምነት ምንጩ የእግዚአብሔርን ታላቅነት ማየት ነው። እምነትን ለማግኘት፡-
፩. ቃሉን መስማት ያስፈልጋል፡- የምንሰማው ነገር እምነታችንን ይወስነዋል። ቃሉም ትክክለኛውን እምነት ይወልዳል፤ ትክክለኛው እምነትም በቅድስት ሥላሴ ማመን፣ ወልድ ዋሕድ በሆነው አዳኝ ክርስቶስ ማመን ነው።
፪. ያለፈውን መዝገባችንን ማገላበጥ ያስፈልጋል፡- እስራኤላውያን ከኋላቸው ቀይ ባሕርን መሻገራቸውን ቢያስቡ ኖሮ ከፊት ለፊታቸው ያለው የኢያሪኮ ግንብ አያስጨንቃቸውም ነበር። ፈርዖንና ሠራዊቱ እንደ ተሸነፉ ቢያስቡ ስለ ኢያሪኮ ረጃጅም ሰዎች ባላወሩ ነበር።
፫. መጸለይ፡- «አለማመኔን እርዳው» እንዳለው ሰው ጌታ ሆይ እንዳምንህ እርዳኝ፣ ጉልበት ጨምርልኝ ማለት ይገባል/ማር.፱፣፳፬/። ያለ እምነት ሕይወት ከባድ ነውና እምነትን መለመን አለብን።
 
፬. የእምነት ሰዎችን ማሰብ፡- ነቢያትን፣ ሐዋርያትን፣ አበውንና የእምነታቸውን ተጋድሎ ማሰብ እምነትን ይጨምራል። እግዚአብሔር በእነርሱ ሕይወት የሠራውን ተአምር ለእኛም እንዲፈጽምልን ያነቃቃል።
፭. በየቀኑ ቃሉን መሞላት ያስፈልጋል፡- ቃሉ ለማያምኑ ማሳመኛ ብቻ ሳይሆን ለአማንያንም የሚያጸና ነው። ቃሉ ይተክላል፣ ያሳድጋል፣ ለፍሬ ያበቃል።
፮. እምነታችንን ከሚያግዙ ሰዎች ጋር መሆን ይገባል፡- የማያምኑ ሰዎች ያስክዱናል፣ አማንያን በእምነት ያጠነክሩናል። ከእምነት አብሳሪዎች ጋር ማሳለፍ እምነትን ይጨምራል።
እንግዲህ ምእመናን እምነት ልምምድ ነው። በእምነት መጸለይ፣ በስሙ መዋጋት እነዚህን ነገሮች በጥቂቱ ስንለማመድ እምነታችን ከፍ እያለ ይመጣል። የሙላት ምንጩ ልምምድ ነው።
ክፉ ቃልን፣ የክህደት መንፈስን ዝም ብለን መስማት ተገቢ አይደለም። ለእነርሱ የመናገር መብት ማን ሰጠ? እኛም የእምነት ቃላችንን መናገር አለብን። አሊያ በዝምታ ስንሰማ ጋሻ ስላልጋረድን በውስጣችን ገብቶ ይዋጋናል። እግዚአብሔር የለም ለሚሉ «ያንተ ሕልውና መሠረቱ የእግዚአብሔር ሕልውና ነው፣ እግዚአብሔር ይህን ካንተ ያርቅ» ልንላቸው ይገባል። አሊያ የሰይጣን አድማጭ ከሆንን ያለ ጋሻ ከቀስት ጋር የምንፋጠጥ እንሆናለን።
እምነት የመኖር ኃይል ነው! 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ