የመጣል ስሜት ሕፃን ፣ አዋቂ ፤ ምሁር ያልተማረ ፤ ሀብታም ድሀ ፤ ዝነኛ የተረሳን ብንሆን ሊገጥመን ይችላል ። ይህ ስሜት ሲሰማን ቀድሞ የሚያስደስተን ነገር አሁን የማያስደስተን ይሆናል ። ቤታችንን እንደ መቃብር ፉካ ፣ ንብረታችንን እንደ ወዳደቀና የዛገ ብረት ፣ ዝናችንን ራሳችንን እንዳታለልንበት አረቄ ፣ መወደዳችንን እንደ ተሳሳትንበት መንገድ አድርገን መመልከት እንጀምራለን ። የመጣል ስሜት ማሩን ማምረር ፣ ወተቱን ማጥቆር ይጀምራል ። በጊዜ ካልተገታ ዳርቻውን እያሰፋ ፣ ያለንን ነገር እንዳናይ ጥቁር መጋረጃ ማልበስ ይጀምራል ። ለነገሮች ትርጉም ማጣት ፣ ሁሉንም ነገር ምን ዋጋ አለው ? በሚል በዜሮ ድምር ውስጥ መክተት እንጀምራለን ። ተሻገርሁ ስንል መልሶ ይህ ስሜት ይይዘናል ። አንድ ሰዓት ስድሳ ሰከንዶች ሳይሆን ስድሳ ዓመቶች ያሉት ሁኖ ይረዝምብናል ። እጅግ ቆየሁ ብለን ሰዓታችንን ስናየው የተገፋው ገና አምስት ደቂቃ ብቻ ነው ። ሌሊቱን መፍራት ፣ ቀኑ እንዴት ይጋመሳል ? ብሎ መጨነቅ እንጀምራለን ። የሚፈልጉንን ሰዎች መሸሽ ፣ የማይፈልጉንን ማሳደድ የመጣል ስሜት የሚፈጥርብን አዙሪት ነው ።
የመተው ስሜት በውስጣችን እያደገ ሲመጣ ትላንት የምናልፋቸውን ነገሮች ዛሬ ማለፍ ያስቸግረናል ። ደስታችንም ሩቅ አገር ይቀመጣል ። ማልቀስም መሳቅም ፣ መውደድም መጥላትም እያስፈራን ይመጣል ። የማናውቀው የፍርሃት ስሜት ይከበናል ። የብቸኝነት ብርድ ያንጠረጥረናል ። ምዕራብና ምሥራቅ ተቀራርበው ቢያቅፉን እንመኛለን ። አዎ የመጣል ስሜት ሲቆጣጠረን ልባችን የከዳን ፣ የሕይወት ፍሬን የላላ ይመስለናል ። ድንገት ከፊት ለፊታችን ከሚገጥመን ጋር እንጋጫለን ። ሰዎች ብቻ ሳይሆን ግዑዛን ነገሮችም እያናደዱን ይመጣሉ ። ደስ የማይል ፣ ልብ ላይ የሚንቀዋለል ፣ የሕይወት ማጥወልወል ይገጥመናል ። ፈልገን ማጣታችን ፣ ያዝኩት ስንል ከእጃችን የሚያመልጠን ነገር ይህን ስሜት ይፈጥርብናል ። ስሜት ዕለታዊ ሲሆን ምንም አይደለም ። ኑሮ ሲሆን ግን እንደገና መታየት አለበት ።
የመጣል ስሜት በታላቅ ተቃውሞ ውስጥ በማለፍ የሚፈጥርብን መደፍረስ ነው ። ሕይወታችንን የሰጠናቸው ሕይወታችንን ሲጋፉ ፣ የኖርንላቸው ከማመስገን ወቀሳ ሲያበዙብን ፣ ልጆቻችን እንከናችንን ሲፈልጉ የመጣል ስሜት ይገጥመናል ። በምንሸለምበት ነገር ልብሳችን ሲገፈፍ ፣ በምንኖርበት ዕድሜ ሞት ሲታወጅብን የመጣል ስሜት ይጫጫነናል ። ያሳደግነው ሲነክሰን ፣ የተንከባከብነው እሾህ ሁኖ ካባችንን ሲይዝብን የመጣል ስሜት ውስጥ እንገባለን ። ለአንድ ነገር ሁለት ዋጋ አይከፈልም ። ምድር ከሸለመን ሰማይ በባዶ ይሸኘናል ። ሲያሳድዱአችሁ ደስ ይበላችሁ ያለው ክርስቶስ ፣ ሲያሞግሱአችሁ ወዮላችሁ ብሎናል ። ክርስቶስን የምንመስለው በመገፋት እንጂ በመሸለም አይደለም ።
የመጣል ስሜት ከማይለምዱ ሰዎች ጋር በመኖር የሚከሰት ነው ። ገቡ ሲባሉ ከሚወጡ ፣ ተገኙ ሲባሉ ከሚጠፉ ፣ ቀረቡ ሲባሉ ከሚርቁ ሰዎች ጋር መኖር የሕይወት ዝለት ያመጣል ። አቋም የሌለውን ሰው ተሸክሞ መኖር አቋምም መቆሚያም ያሳጣል ። በውድ የገዛናቸው ፣ በርካሽ የሚሸጡን ጊዜ ጥቂት አይደለም ። ያ የመጣል ስሜት ያመጣል ። ክዳት ለእውነተኛ አፍቃሪ የማይለመድ የሕይወት ቅንቅን ነው ። ዛሬ ነገሥታት ከሚገዙት ሕዝብ ወረት የሚገዛው ይበዛል ። ዘመናዊነት ወረት ነው ። ሰው ማለዋወጥ ሥልጣኔ ተደርጎ የሚታይ ነው ። በቃል ኪዳን አለመጽናት ፣ እንዴት እንኑር ሳይሆን እንዴት እንለያይ ብሎ የመውጫውን በር ሲቆፍሩ ማደር ፣ ሰውን ተጠቅሞ መጣል የጊዜአችን በሽታ ሆኗል ። ስለከዱን ሰዎች ሳይሆን ከእኛ ጋር ስላለው እግዚአብሔር ማሰብ ይገባናል ። ከአባት ከእናታችን በፊት የሚያውቀን ጌታ ዛሬም አለ ። ለቅጽበት ዓይኑን ከእኛ ላይ አንሥቶ የማያውቀው ጌታ ደስታችን ነው ። ሁሉ የራሱን ሥዕል ይሰጠናል ። በጥሩ ዓይኖቹ የሚያየን ክርስቶስ ግን አሟልቶ ያነበናል ። የዓለም አስቀያሚ ብንሆን እንኳ የክርስቶስ ውቦች ነን ። ውብ ልቦች ሁሉን ውብ አድርገው ይመለከታሉ ። በተቀደሰው በኢየሱስ ልብ መኖሪያ አግኝተናል ።
“ሰይጣን ተስፋ የለውም ፣ ግን ተስፋ አይቆርጥም ፤ ሰው ተስፋ አለው ፣ ነገር ግን ተስፋ ይቆርጣል ።” እግዚአብሔርን በሰው ሚዛን ይለካዋል ። ሰዎች አጠገባችን የሉም ማለት እግዚአብሔር ከሰው ጋር አደመ ማለት አይደለም ። እርሱ የራሱ ሚዛን አለው ። በእኛ ላይ ያለውን የራሱን ዓላማ ያያል ። እርሱ አይተወንም ። ሰዎችን ስንለካ ፣ ስንመዝን ፣ ስንመትር መኖር ዋጋ የለውም ። የማይታበል ፍቅር ከእኛ ጋር ነው ። ሊወድቅ ያለውን የሕይወት ምሰሶ እንደገና እናጽናው ። መተው የማያውቀው አምላክ ከእኛ ጋር ነው ። ታሪክ እገሌን ጣለ ብሎ አልጻፈለትም ፣ ክርስቶስ ሰውን መጣል በእኛ አይጀምርም ።
ምስጋና ለማይተው ፍቅርህ ! አሜን !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 23 ቀን 2016 ዓ.ም.