የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ ጥቅምት ፱፣፳፻፭ ዓ/ም
ቀዳሚ ቃል
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
በዓለም ላይ ከሚገኙት ኃይላት ይልቅ የፍቅር ኃይል ይበልጣል፡፡ ኃይል ጉልበትን ይገዛል፣ ፍቅር ግን ፈቃድን ይገዛልና ሁሉን የራሱ ያደርጋል፡፡ በዓለም ላይ ዕዳውን ሳያስመልስ የማይተኛ ነገር ቢኖር ፍቅር ነው፡፡ ይህም ፍቅር መለኮታዊ ወንዝ ነው፡፡
ድሆች ፍቅርን ይፈልጋሉ፤ ባለጠጎች ይበልጥ መወደድን ይሻሉ፡፡ እነርሱነታቸውን የሚወድ ሰው ያለ አይመስላቸውምና፡፡ እንኳን ለቆሙት ለሚያጣጥሩትም የሚያነቃ ኃያል ድምጽ አንድ ነው፡፡ « እግዚአብሔር ይወድሃል» እግዚአብሔር ማንንም ስለማይጠላ አይደለም የሚወደን፤ በተለየ ፍቅር ነው የሚወደን፡፡ አጠቃላይ የሰው ዘርን መውደድ ቀላል ነው፣ አንድን ሰው መውደድ ግን ከባድ ነው፡፡ እግዚአብሔር እያንዳንዳችንን ይወደናል፡፡ በትእዛዝ ማፍቀር አንችልም፤ እግዚአብሔር እንዴት እንደወደደን ስናውቅ ብቻ እንወደዋለን፣ እርሱንም ስንወድ ሌሎችን እንወዳለን፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ በኑሮውና በሞቱ የእግዚአብሔርን ፍቅር ገለጠ፡፡ ፍቅርን በሚዳሰስ አካል የተረከ ክርስቶስ ነው፡፡ አሊያም አካላዊ ፍቅር ክርስቶስ ነው፡፡ ደግ ለመሆን ምቹ ጊዜን የማይጠብቀው ይህ ፍቅር ሲገዛን መለወጥን እናገኛለን፡፡
ብዙ ሰዎች ክርስቲያንነትን የሚፈልጉት ገንዘባቸውን ለመቆጠብ፣ ከሚወራው በሽታ ለመዳንና ጨዋ ለመሆን ነው፡፡ የክርስትና ዓላማው ግን ግብረ ገብነት ሳይሆን ሕይወት ነው፡፡ ሕይወትን እንቀበላለን እንንቀሳቀሳለን፡፡ «የባሕርይ ለውጥ እናምጣ» እየተባለ ይነገራል፡፡ ሰዎችም አሳቡን አምነውበታል፤ ሊያደርጉት ግን አልቻሉም፡፡ ሰው ራሱን ለመለወጥ አምላክነት ያስፈልገዋል፡፡ ታዲያ ለውጡ ካስፈለገ ለውጡ የሚመጣው በማን ነው? «. . . እውቀት አይለውጥም፣ ዕድሜም አይለውጥም ክርስቶስ ብቻ ይለውጣል፡፡» ክርስቶስን ካልፈለግን ዓለምና ጠላቶቻችን ከሚጐዱን ይልቅ ራሳችንን እንጐዳዋለን፡-
ሰው ራሱን መግዛት ባቃተው በዚህ ዘመን፣ ከኒውክለር ሥጋት ይልቅ የሞራል ውድቀት አስጊ በሆነበት በዚህ ቀን፣ ተስፋ የሚሰጡ ነገሮች በራቍበት በዚህ ዘመን ታላቅ መልስና የለውጥ ኃይል አለ፡፡ ይህ ኃይል ማን ይሆን? ይህ መጽሐፍ ወደለውጥ ወጋገን ለማድረስ መሪ ይሆናል ብለን እናምናለን፡፡ ክብር ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ አሜን፡፡
መግቢያ
በመጀመሪያው ምእት ዓመት የሰምርኔስ ቤተክርስቲያን ብዙ ስደትና ሰማዕትነት ደርሶባታል / ራእይ 2፡8-11/፡፡ አሥራ ሁለተኛውና በሰምርኔስ ቤተክርስቲያን የመጨረሻው ሰማዕት ታላቁ ሽማግሌ ፖሊካርፕ ነበር፡፡ እርሱም የሰምርኔስን ቤተክርስቲያን ለአርባ ዓመታት በትጋት ያገለገለና በሚሞትበትም ጊዜ ገና የሚያገለግል ነበር፡፡ የታሠረውም ሽማግሌ ሆኖ ነው፡፡ . . . አንድ ዓርብ ምሽት ገዥው ክርስቶስን እንዲክድ ጠየቀው፡፡ ፖሊካርፕም «ለ86 ዓመ ት አግልግዬዋለሁ፤ አንድም ጊዜ በድሎኝ አያውቅም፤ ታዲያ የሚያድነኝን ንጉሤን እንዴት ልካደው?» አለው፤ በዚህም ምክንያት በእሳት ተቃጥሎ ሞተ፡፡
የአንጾኪያው ሊቀጳጳስ ቅዱስ አግናጥዮስ «ስለክርስቶስ የማይናገሩ ወይም ለመናገር የሚያፍሩ ሰዎች ለእኔ የመቃብር ድንጋዮችና የሞቱ ጠጠሮች ናቸው» ብሏል፡፡ ክርስቲያኖች የምንናገርበትንና ዝም የምንልበትን ቦታ የምናውቅ ብንሆንም የክርስቶስ ነገር ከተነሣ ግን ይሉኝታ የለንም፡፡
ደቀ መዛሙርቱ « እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም» /የሐዋ. ሥራ. 4፣2ዐ/ በማለት ለገዢዎች ተናግረዋል፡፡ በርግጥም ሰው የክርስቶስ ነገር በትክክል ገብቶት ዝም ልበል ቢል እንኳ አይችልም፡፡
ነቢዩ ዳዊት « አመንሁ ስለዚህም ተናገርሁ» /መዝ.115/116፣1/ ብሏል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም የእምነት መንፈስ የሚያናግር መንፈስ መሆኑን ተናግሯል / 2ቆሮ.4፣13/፡፡ ሰው ስለሚያምነው የሚናገረው ከሌለው የሚያምነው የለም ማለት ነው፡፡
ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት በጸሎት ቤቶቻቸው በሰቀሉት የመስቀል ምልክት ረክተው ከመቀመጥ ውጭ ለትውልዱ ወንጌል እንደሚያስፈልገው ዘንግተዋል፡፡ በተለያዩ አገራት ያሉ ተከ ዮቻቸውም ክርስትናቸውን ለመግለጥ በአካላቸው ላይ የተነቀሱትን የመስቀል ምልክት ከማሳየት ያለፈ ምስክርነት የላቸውም፡፡ የእምነት ነገር ግን እስኪጠይቁን የምንጠብቀው ሳይሆን ጠየቁንም አልጠየቁንም የምንናገረው ነው፡፡
በክርስቶስ ያመነ ሁሉ የክርስቶስ ምስክር ነው /የሐዋ.ሥራ.1፣8/፡፡ ሰው ስለክርስቶስ ለመመስከር ጸጋዬ አይደለም ቢል ይሳሳታል፡፡ ስለክርስቶስ ለመናገር ካረፈችው ነፍሳችን ይልቅ ማስረጃ አንፈልግም፡፡ ያረፍነው እውነት ስለሆነ ነውና፡፡
በዓለማችን ላይ የእውቀትን ብርሃን ያበሩና ለተጠቁትም ሕዝቦች ስለታገሉ ጥቂት ሰዎች ሰምተናል፡፡ ክርስቶስ ግን ዓለምን ሳይሆን ሰዎችን ራሳቸውን ሊለውጥ መጥቷል፡፡ ለሰው ትልቁ ጠላቱ የገዛ ኃጢአቱ ነው፡፡
በዓለማችን ላይ የተነሡ ታላላቅ ሰዎች ስለእውነት ሊመሰክሩ እንደመጡ ተናግረዋል፡፡ ክርስቶስ ግን ስለእውነት ሊመሰክር ብቻ ሳይሆን ራሱ የሕይወት እውነት ሆኖ መጥቷል፡፡ በዓለም ላይ ከእርሱ በቀር «እውነት ነኝ» ያለ ማንም የለም / ዮሐ.14፣6/፤ እውነትን ስናውቅ ብቻ ነጻ ሰው ነን፡፡ የተፈተነው እውነትም ክርስቶስ ነው፡፡
ሰባክያን ለሕዝቡ ስለክርስቶስ መናገር አለባቸው፡፡ የምእመናን እምነት የሚያድገው ስለክርስቶስ ይበልጥ ባወቍ ቍጥር ነውና፡፡ ይልቁንም ራስ ወዳድነት በነገሠበት በዚህ ዘመን ሰው የሥልጣኔው አዋቂና ተጠቃሚ ሆኖ ሳለ ስለ ሕይወት እውቀት ግን ትንሽ እንኳ ግንዛቤ ባጣበት በዚህ ዘመን ክርስቶስ ሊሰበክ ይገባዋል፡፡
ሰው ሲፈጠር የተዘጋጀለት የሞራል ደረጃ በክርስቶስ ትምህርት ተገልጧል፡፡ ለእኔ የማይለውና ፍቅር የተሞላው አኗኗር በእርሱ ተሰብኳል፡፡ እርሱን ወሰን አድርጐ ከሰው መለኪያ በላይ መኖርም በክርስቶስ ተነግሯል፡፡
እርሱ ሲነግሥ ብቻ ሕይወት አዲስ ትሆናለች፡፡ ክርስቶስ ግን ማን ነው?
የሚለውጥ ፍቅር –
በዲ/ን አሸናፊ መኰንን
የመጀመሪያ እትም 1997 ዓ/ም
አድራሻ፡ 0911 39 3521 / 0911 67 8251
ፖ.ሳ.ቁ. 1591 ኮድ 1110