የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሚችለኝ ማነው ?

“እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ ሁኑ” ኤፌ. 5፡1
በራሴ ማስተዋል መደገፍ ፣ የገመትኩትን እያመንሁ መጓዝ ጌታ ሆይ ይብቃኝ ። የሙከራ ኑሮ እንዳያደክመኝ ፣ ያቆሰለኝ እንደ ገና እንዳያቆስለኝ ፣ ጥዋት የመታኝ ድንጋይ ማታ ላይ እንዳይደግመኝ ፣ ሁልጊዜ ዳዴ ሁልጊዜ ሀሁ የምል ፣ አይቼ የምረግጥ ሳይሆን ረግጬ የማይ እንዳልሆን እባክህ ጌታዬ ጠብቀኝ ። ልቤ እንዳይሸፍትብኝ ፣ ዘረኝነትን እንዳይተክልብኝ ፣ ጥላቻን እንዳያለማምደኝ ፣ ክፋትን እንዳያስተምረኝ እባክህ አድነኝ ። እንደ ሞገደኛ ልጆች ፣ በጥዋቱ ቀትር እንደሚሆኑ ሕፃናት ያልሁት ብቻ ይሁን እንዳልል ፣ በእውነቱ ሳይሆን በስሜቴ ነገርን እንዳለካ ፣ ቀድሜአለሁ ተከተለኝ እንዳልልህ እባክህን አድነኝ ። ሰው ከራሱ ከዳነ ሌላው ቀላል ነው ። እንደ ተወደዱ ልጆች አስፈቅዶ መውጣትን ፣ ምሪት ተቀብሎ መሰማራትን ፣ ምክርን ሰምቶ መዝመትን እባክህ አድለኝ ። አንተን ትቼ እምነቴን ከማመን ፣ ቃልን ትቼ ሕልምና ራእይ ከማሰስ እባክህ አድነኝ ። እንደ መስኖ ውኃ በየመንገዱ እንዳልቀየስ ፣ ብልጥ እንዳይመራኝ ፣ አፈ ቅቤ እንዳያቀልጠኝ ጌታዬ ሆይ አንተ ብቻ ምራኝ ። ወላጆቹን መካሪም መምህርም እንደሚያደርግ ተወዳጅ ልጅ አንተን አባትም መምህርም እንዳደርግህ እርዳኝ ። ክርስቶስ በዚህ አለ በዚያ እያልሁ ስባዝን ዘመኔ እንዳያልቅ ወልድ ሆይ ሰው ስለ መሆንህ አድነኝ ። ስሜትና እውነት ፣ ቅዱስና ርኩስ በተቀላቀለበት በዚህ ዘመን የሚያዋጣኝ አንተን ብቻ መከተል ነውና እባክህን በቀደምህበት አስከትለኝ ። ልቤን በዓለቱ ቃልህ ላይ መሥርትልኝ ። ማዕበል ወጀቡ ሲመጣ እንዳሳልፈው እንጂ እንዲያሳልፈኝ አትፍቀድለት ። አንተ ከረዳኸኝ የሚችለኝ ማነው ? ለዘላለሙ ክብር ምስጋና ላንተ ይሁን ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ