የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሚያደርሰው መንገድ

 አንድ መነኩሴ አባ ኢሳይያስን አንዳች ቃል እንዲነግረው ጠየቀው ሽማግሌውም እንዲህ ሲል መለሰለት ፡- ጌታችን ኢየሱስን መከተል ከፈለግህ ትእዛዛቱን ጠብቅ ። አሮጌው ሰውነትህ እኪሞት ድረስ ከእርሱ ጋር እንዲሰቀል ከፈለግህ ከመስቀል የሚያወርዱህን ነገሮች ረጣቸው ። ባዶነትን ለመታገ ፣ መጥፎ ነገር የሚያደርጉብህን ሰዎች ልብ ለማሳረፍ ፣ ካንተ የበላይ በሆኑት ፊት ራስህን ዝቅ ለማድረግ ፣ አንደበትህ ዝምታን ለመያዝና ማንም ሰው ላይ በልብህ ከመፍረድ ለመቆጠብ ራስህን አዘጋጅ ። (አባ ኢሳይያስ ፣ የምነና ንግግሮች ፣ 25)
ምክር በቢሮ በሚሸጥበት በዛሬው ዘመን ሰዎች ከመንፈሳውያን አባቶች በነጻ ለመማር አለመፍቀዳቸው ይገርማል መንፈሳዊ ምክር የማይሸጠው ዋጋ ስለማይተመንለትና “በነጻ የተቀበላችሁትን በነጻ ስጡ” የሚል አምላካዊ ትእዛዝ ስላለ ነው የቀደሙት አባቶች ዘወትር በተጠንቀቅ ላይ እንዳለ ወታደር በማመን የሚቀድሟቸውን አባቶች ለመጠየቅና ለመስማት ስንዱ ናቸው ያላቸውን ለማጽናት ፣ የጎደላቸውን ለመሙላት ይጠይቃሉ እንጂ ፀጥታን ለመሻር ፣ ጨዋታን ለማምጣት ብለው የሚጠይቁ አልነበሩም እስካለፉት ሃያና ሠላሳ ዓመታት ይህ ልማድ ነበረ አሁን ግን ሁሉም አባት ሁኖ ልጅ ጠፋ ሁሉም መምህር ሁኖ ተማሪ አለቀ የክርስትናን ሆሄ ያስጠናውን አባት ለመናቅ ብሎ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት የሚገባ ሆነ እድገትና እብደት ተዘበራረቀ የክርስትና ጉዳይ የእምነትና የልምድ መሆኑ ተዘንግቶ ወጣቶች በአእምሮ እብጠት ለመመካት ሞከሩ ውጤቱ ግን በአፉ እግዜር አለ የሚል ፣ በልቡ ግን የሚክድ ትውልድን አስገኘ
“እሳት ካልቆሰቆሱት አይነድም ” አዋቂም ካልጠየቁት ብዙ እውቀቱን አያወጣም ዝም ያሉ አባቶች እንዲናገሩ መጠየቅ ያስፈልጋል ዓለም ከምታሞግሰን መንፈሳውያን አባቶቻችን ቢገሥጹን ይሻላል እግዚአብሔር ልጅን ለወላጅ ፣ ደቀ መዝሙርን ለመምህር አደራ ሰጥቷል ራሴን አምጬ የወለድሁ ነኝ የሚል ካለ ሞኝ ልጅ ብቻ ነው እኛ እንድንወለድ ያማጡልን አሉ “ሁሉም ሆኖ ቃልቻ ፣ ማን ሊሸከም ነው ስልቻ” ይባላል ቀጥሎ ያለውን ስንኝ የገጠሙብን በእኔና በመሰሎቼ የተበሳጩ ይሆናሉ፡-
ከጥሬዎች ጋር አብረን የዋለን ፣
እነርሱ እስኪበስሉ እኛ ተቃጠልን ፤
አባት ተብሎ ምክር መታጠቅ ግድ ነው በመንፈሳዊ ዓለም አባት የሚያሰኝ ምልክቱ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊነቱና እውቀቱ ነው ዝናብ የሌለው ደመና እንዳንሆን ፣ በሩቅ ያከበረን ሲቀርብ እንዳይንቀን ማንበብና መዘጋጀት ያስፈልጋል ከሁሉ በላይ የጸሎት ሠራዊት መሆን ይጠቅማል አባ ኢሳይያስም፡- “ጌታችን ኢየሱስን መከተል ከፈለግህ ትእዛዛቱን ጠብቅ ። አሮጌው ሰውነትህ እኪሞት ድረስ ከእርሱ ጋር እንዲሰቀል ከፈለግህ ከመስቀል የሚያወርዱህን ነገሮች ረጣቸው” ይላል
አይሁዳውያን በአንድ እግርህ ቆመህ የምትናገረው በማለት “ያህዌ አንድ ነው”   አሊያም “እግዚአብሔርንና ባልንጀራህን ውደድ” በማለት መላውን ቶራህ ወይም ሕጉን በአጭሩ ይናገራሉ የጌታችን ትእዛዝም በአንድ እግራችን ቆመን የምንናገረው ነው እርሱም “ፍቅር” ነው ፍቅር የሌላቸው መምህራን ተማሪዎቻቸውን በባርነት ይገዛሉ ፣ ፍቅር የሌላቸው ተማሪዎችም የወለዱአቸውን እንደ እፉኝት ልጅ ይገድላሉ ምንም ታላላቅ ተግባር ብንሠራ በፍቅር ካልተሠራ ትንሽ ነው ፍቅር የሌለበት ነገር ሁሉ አልጫና የእውነት ቅመም የተለየው ነው የጌታችን ትእዛዝ በጸጋ መወዳደር ፣ በስብከት መፋጀት አይደለም መፋቀር ብቻ ነው ስለ ጸጋ እንጂ ስለ ፍሬ ማውራት ያልቻለው ትውልድ ምስኪን ነው ጸጋ ፣ ጸጋ መሆኑን ረስተን ፤ጸጋ ስላልተለየን ፣ ጸጋን እንደ ፍሬ ቆጥረን መኖር አለማወቅ ነው
አሮጌው ሰውነት የተባለው ከአዳም የወረስነው ለኃጢአት የሚያደላው ማንነት ፣ በእኔነት የተቃኘው እሾህነት ነው ነገን ለመኖር ተስፋ አጥቶ በትላንት የሚዝናናው እርሱ አሮጌው ማንነት ነው አሮጌው ሰውነት በመስቀል ላይ ሊጠረቅ ይገባዋል እርሱ ካልሞተ ጠብና ክርክር አይሞትም ይህን አሮጌ ሰውነት ለመግደል መስቀል ላይ እንሰቅለውና መልሰን እናወርደዋለን ዓለምን መናቅ ፣ ክፉ ባልንጀርነትን መጠየፍ ፣ በጾምና በጸሎት መወሰን እርሱ አሮጌውን ሰውነት መስቀል ነው አጠገባችን ያለው ሰው ጥሎን ያደገ ሲመስለን ከመስቀል እንወርዳለን ብቻችንን የቀረን መስሎን አሮጌ ባልንጀሮችን ስንፈልግ ያን ጊዜ ከመስቀሉ እንወርዳለን መብልና ወሬን ብቻ ስንወድ ያን ጊዜ ከመስቀሉ እንወርዳለን ከመስቀሉ ሊያወርዱን የሚፈልጉ ቊጣና ንዴቶች ፣ ቅናትና ምቀኝነቶች ብዙ ናቸው መስቀል ሲያጌጡበት ቀላል ፣ ሲኖሩት ግን ከባድ ነው ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ” ያለውን እንዳትረሱ 1ቆሮ. 9 ፡ 27 ደግሞም፡- “ከኃጢአት ጋር እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም”ይላል ዕብ. 12 ፡ 4
አባ ኢሳይያስ በመቀጠል እንዲህ አለ፡- “ባዶነትን ለመታገ፣ መጥፎ ነገር የሚያደርጉብህን ሰዎች ልብ ለማሳረፍ ፣ ካንተ የበላይ በሆኑት ፊት ራስህን ዝቅ ለማድረግ ፣ አንደበትህ ዝምታን ለመያዝና ማንም ሰው በልብህ ከመፍረድ ለመቆጠብ ራስህን አዘጋጅ ።
ዝግጅቱ የመጀመሪያው ባዶነትን ለመታገሥ ነው ጭው የሚልብን ሰዓት ብዙ ነው ተስፋችንን ማን እንደ ሰረቀው እስኪጠፋን ተስፋ ቢስ እንሆናለን ግን ይህ ስሜትም ያልፋልና መታገሥ ይገባናል ሁልጊዜ ልብ ሙሉ አይሆንም ሲጎድል በትዕግሥትና በምክር ልንደግፈው ይገባል ነቢዩ አታውኪኝ ነፍሴ ማለቱ ለዚህ ነው
“መጥፎ ነገር የሚያደርጉብህን ሰዎች ልብ ለማሳረፍ ተዘጋጅ” ይለናል የሚጠሉን ሰዎች ስለ እኛ ያላቸው ሥዕል ክፉና ትልቅ በመሆኑ ትልቅ መሳሪያ ሲተኩሱ ይጎዳናል ነገር ግን በመንገዳችን በመጽናት እነርሱንም ማሳረፍ ይገባናል ካልጮኸበት በቀር የሚጮኽ የለምና ስለ ስቃያቸው ልናዝንላቸው ይገባል
ካንተ የበላይ በሆኑት ፊት ራስህን ዝቅ ለማድረግ ተዘጋጅ” ይላል ከሚበልጡን ጋር ቁመት መለካካት መሬት ለመልቀቅና ለመውደቅ ነው በዕድሜም በማመንም የሚበልጡንን መስማት ይገባናል የሚበልጡንንም የሚያንሱንንም በትሕትና መቅረብ ግድ ይላል አሮጌውን ሰውነት መስቀል ማለት ይህ ነው
“በአንደበትህ ዝምታን ለመያዝ ተዘጋጅ” ይላል ትላንት ይቃወሙት የነበረውን ዛሬ ሲደግፉ ፣ ትላንት ይደግፉት የነበረውን ዛሬ ሲቃወሙ ብዙዎች ትዝብት ላይ ወድቀዋል “የፊት ምስጋና ለኋላ ሐሜት ያስቸግራል” እንዲሉ ከመለፍለፍ በኋላ ዱዳ የሆኑ አያሌ ናቸው ዝምታ ግን ዋጋዋ ከዘመን ዘመን ውድ ነው “ጊዜ የሰጠው ዘፈን እንቅርት ያፈርጣል” እንዲሉ ዛሬም በዘመነኛ ርእስ ሲጮኹ መዋል ቆይቶ ያጸጽታል ስሜት ያልፋል ፣ እውነት ይቀራል አባ አርሳንዮስ፡- “ብዙ ጊዜ እናገራለሁ ፣ በመናገሬ አዝናለሁ ፤ በዝምታዬ ግን ያዘንኩበት ጊዜ የለም” ብሏል
“በማንም ሰው ላይ በልብህ ከመፍረድ ለመቆጠብ ራስህን አዘጋጅ” ይላል ብዙዎቻችን የምናውቀው በአንደበት ስለ መፍረድ ነው  አባ ኢሳይያስ ግን በልብ ስለ መፍረድ እየተናገረ ነው በልብ መፍረድ መታዘብ ነው ፍርድ በቃል ብቻ ሳይሆን በልብም ነው በልብም የፈረዱት ይደርሳል የምንጓዘው የፈረድነውን ለመሆን ነውና ይቅር ይበለን
ወዳጆቼ ሆይ የሚያደርሰው መንገድ ይህ ነው
ጌታ ሆይ ዛሬም የደነዝሁትን ልጅህን ትወቅረኛለህ ከማላውቀው እውነትና አውቄው ከተዘናጋሁበት ነገር ታገናኘኛለህ በደጅ ተጥዬ እንዳልቀር ይህን ሁሉ እንክብካቤ ስለምታደርግልኝ አመሰግንሃለሁ አውቃለሁ ከሚል ስሜት አድነኝ ምክርህ በሕይወቴ አብቦ ፍሬው ለብዙዎች ጥጋብ እንዲሆን እርዳኝ በሚያነጋውና በሚያስመሸው ሥልጣንህ ለዘላለሙ አሜን
የበረሃ ጥላ 3
መስከረም 3 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ