የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሚያደቅ ቃል

                                                      ቤተ ጳውሎስ፤ እሑድ ግንቦት 5 2004 ዓ.ም.
የእግዚአብሔር ሰው ኢዮብ በብዙ መከራና ፈተና ውስጥ አልፏል፡፡ መከራ አካላዊ ጉዳት፣  ፈተና ውስጣዊ ሙግት ነው፡፡ ኢዮብ ቀኑ ቀድሞለት ሌሊቱ ተከተለበት፡፡ ሰው ሁሉ የሚመኘው መከራው ከፊት፣  ደስታው ከኋላ እንዲሆን ነው፡፡ ነገር ግን ቀኑ አልፎ ሌሊቱ እንደመጣ፣ ሌሊቱም አልፎ ቀን ይመጣል፡፡ የተፈጥሮን ሌሊትና ቀን ብቻ ሳይሆን የሕይወትንም ሰልፍ እግዚአብሔር ያስተካክላል፡፡ ኢዮብ ያለውን ሁሉ ካጣ በኋላ ራሱንም የሚያሳጣ ትግል ገጠመው፡፡ የሰው ልጆች ሦስት ሀብታት አሉት፡፡ አንደኛ ያለው ነገር ሁለተኛ እኔ የሚለው ራሱ ሦስተኛ እምነቱ ነው፡፡ መከራና ፈተና ሲመጣ ከእነዚህ ሀብታት በየተራ ሊለይ ነው፡፡ ያለውን ሀብት ንብረት ሲያጣ ራሱንና እንደራሱ የሆነውን በማትረፉ ይጽናናል፡፡ ራሱንና የራሱ የሆነውን ነገር ሲከስር ደግሞ በእምነቱ ይጽናናል፡፡ እምነቱን ያጣ ግን መጽናኛ የለውም፡፡
ኢዮብ ሀብት፣ ልጅ፣ ትዳር፣ ጤና እነዚህ ሁሉ በዓመታት ውስጥ ተሰጡት፡፡ የፈረሱት ግን በአንድ ቀን ነው፡፡ ለዘመናት የገነባናቸው ነገሮች ለደቂቃ ውድመት የተዘጋጁ ናቸው፡፡ በሦስትና አራት መቶ ዓመታት የተሠሩ ከተሞች በ5 ደቂቃ የመሬት መንቀጥቀጥ እንዳልነበሩ ይሆናሉ፡፡ ዛሬ የምንኰራበት ሀብትና ንብረት፣ ጤናና ጉልበት ለደቂቃ የማይበቁ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር አይምጣ እንጂ በመዓቱ ፊት የሚቆም ጉልበተኛ፣ በቁጣው ፊት የሚፀና ኃይለኛ የለም፡፡

ጻድቁ ኢዮብ የአንዱን ሀዘን ሳይጨርስ የሚበልጥ ሌላ ሀዘን ይገጥመው ነበር፡፡ የሀብት መውደም በልጅ፣ የልጅ ሞት በትዳር፣ የየትዳር መፍረስ በጤና ይረሳሳ ይሆናል፡፡ ኢዮብ ግን የሚያየው እስኪያጣ ሁሉም ነገር ጥቁር ሆነበት፡፡ የዚህ ዓለም መጽናናት የአንዱን መታጣት በአንዱ መኖር መርሳት ነው፡፡ መርሻ ከሌለ ግን የዓለም መጽናናት ይቆማል፡፡ እውነተኛ መጽናናት ግን የሚመጣው እግዚአብሔርን በማየት ብቻ ነው፡፡
እጅግ የከበረው እጅግ ተዋርዷልና እጅግ የበለፀገው እጅግ ደህይቷልና ችግረኞችን ያበላው በአመድ ላይ ተቀምጧልና ባልንጀሮቹ ሊያዩት ወደ ኢዮብ መጡ፡፡ የድሮ መልኩ ዛሬ የለም፡፡ መከራ ቀዩን ጥቁር፣  ጥቁሩን ነጭ ያደርጋልና፡፡ በቁመናው በሐር ቀሚሱ ከሩቅ የሚታወቀው ኢዮብ በቅርብም ጠፋ፡፡ የማያውቁት ኢዮብ ሊሆን ይችላል ብለው የሚገምቱት ያ ሰው ባልንጀሮቹም ረሱት፡፡ ወደ መቃብር የወረደ እንኳ ያ መልኩ በዓይነ ኅሊና ላይ ተስሎ ይኖራል፡፡ የኑሮ ማዕበል የቀበረው ግን የዛሬው አቋሙ የፊቱን መልክ ያስረሳል፡፡ መልክ ምስክር ያሻዋል የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ቆንጆ ነበርኩ ቢሉ ማን ያምናል? መልክ ቅሬታ እንኳ ሳይተው፣ ነቊጥ እንኳ ሳያስቀር ኰብልሏልና፡፡ ይህች ዓለም የበረዶ ጭብጥ/ዝግን ናት፡፡ በረዶ የጨበጡ ከእጃቸው ቀልጦ አልቋል፡፡ ዓለም ኋላ ለማሳየት የማትሆን ተና ጠፊ፣ ቀልጣ አላቂ ናት፡፡ ለዚችው ዓለም እንዲህ መባላታችን በእውነት ያሳዝናል፡፡ አወይ ሰው መሆን ያሰኛል!
ኢዮብ ሊያዩት ያጓጓ እንዳልነበረ፣ አሁን አትዩት ጨፍኑ ያሰኛል፡፡ ያንን እንደቻሉ ይህንንም መቻል የሕይወት ሥነ ሥርዓት ነው፡፡ ምስጋናውን በደስታ እንደ ተቀበሉ ርግማኑንም፣ ካባውን እንደ ተሸለሙ ማቁንም በመጽናናት መሸከም ይገባል፡፡ የባለቤቱ ሥቃይ ይቀጥላል፣ የወዳጅ ልቅሶ ግን ይቆማል፡፡ የኢዮብ ወዳጆች ለጊዜው አልቃሾች ቀጥሎ አስለቃሾች ሆኑ፡፡ የሰው ግብዣ ከፊት ጣፋጩን ኋላ መራራውን ነው፡፡ የእግዚአብሔር ግብዣ ግን በተቃራኒው ከፊት መራራውን ከኋላ ጣፋጩን ነው፡፡ የሚያልቅ ልቅሶ አልቅሰው የማያልቅ ትችት በኢዮብ ላይ ማውረድ ጀመሩ፡፡ አዲስ በሽታ ሲያገኙ ሐኪሞቹ እንደሚመራመሩ በሽተኛው ግን እንደሚሰቃይ ኢዮብ ያለቅሳል፣ ወዳጆቹ ምርምር ያካሂዳሉ፡፡ በየልቅሶ ቤቱ አልቃሾቹ ልቅሶአቸውን ከጨረሱ በኋላ ወሬውን ማድቀቅ ይጀምራሉ፡፡ “ያ ልጁ ነው? ዲቃላ ሳይሆን አይቀርም፣ ወይ የዲቃላ ነገር ቊርጥ ራሱን ነው፡፡ ልጅ የሚታወቀው በጣቱ ነው አሉ፣ ራሱን ይመስላል፡፡ የዲቃላ ጠበቃ መልኩ ነው” እያሉ ሲያጠነጥኑ ከቀብር በኋላ ልጁ የሟች የወንድም ልጅ መሆኑን ይሰማሉ፡፡ በግምቱ የጠፋ ዓለም፣ በስህተት ወለድ የነጐደ ዓለም ነው፡፡ ብዙ ነገሮች ከግምታችን ውጭ ናቸው፡፡ እኛ እንደገመትናቸው በፍጹም አይደሉም፡፡ የኢዮብ ወዳጆች ልቅሶአቸው እውነተኛ፣ ግምታቸው ሐሰተኛ ነበር፡፡ ችግራችን የሚያልቅ ልቅሶ የማያልቅ ሐሜት አስከትሎብን ይሆን? እየሆነ ያለው ሲሆን የነበረ ነው፡፡
የኢዮብ ባልንጀሮች ዕድሜአቸው የሸመገለ፣ በሀብትም የተካከሉት፣ ንግግራቸውን በእግዚአብሔር ስም የሚያትሙ፣ ስለምድሩ ለማስረዳት ስለሰማዩ የሚጠቅሱ፣ ከመላእክት አንጻር የኢዮብን ቅድስና የሚገመግሙ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ሽምግልና ሁሉ አዋቂነት፣ በእግዚአብሔር ስም የተነገረ ሁሉ እውነት፣ ሰማያዊ ማስረጃ የቀረበበት ሁሉ ከነገሩ ጋር የሚሄድ አይደለም፡፡
ባልንጀሮቹ የኢዮብን ሕመም ተዉና ሕመሙ ያመጣውን ኃጢአት የሚያጣሩ የወንጀል መርማሪ ሆኑ፡፡ ኢዮብ በሽታውን ማስታመም ትቶ የእነርሱን አድቃቂ ቃል መሸከም ጀመረ። በቊስሉ ላይ ጥዝጣዜ ሆኑበት፡፡ ከሕመሙ ይልቅ በቃላቸው መሰቃየት፣ ከቃላቸውም የተነሣ መመረር ጀመረ፡፡ ባልንጀሮቹ በቃላት ብዛት እውነተኞች መሆን ፈለጉ፡፡ ማጽናናቱ ወደ ኲነኔ፣ ማልቀሱ ወደ ፍርድ ተለወጠ፡፡ ደጎች ናቸው ወይስ ክፉዎች? ሰው ለፍርድ አይመችም፡፡ አልብሶ የሚገፍ፣ አብልቶ የሚበላ፣ አመስግኖ የሚራገም ነው፡፡ ሲሻው እግዚአብሔር ባንተ ይህን እንዴት አመጣ? እርሱ ለወዳጆቹ አይሆንም እያለ እግዚአብሔርን ያማልናል፡፡ ቀጥሎ በስውር የሠራኸው አበሳ ይኖራል ተናዘዘው ይላል፡፡ በሽታ ሁሉ የኃጢአት ውጤት ቢሆን ማን ይኖር ነበር? በእውነት አልጋ ከያዘ በሽተኛ ቆሞ የሚሄደው፣ ሐኪም ፊት ከቀረበው ታማሚ አስተሳሰቡ የታመመው እርሱ ይብሳል፡፡ 
ኢዮብ ክፉ ተናግሮ አይሸኛቸው እርሱን ብለው መጥተዋል። ጠላቶቼ አይላቸው አመድ ላይ አብረውት ተቀምጠዋል፡፡ ለወሬ የማይመቹ ነበሩ። በርግጥ ላልማ ብለው የሚያጠፉትንና ላጥፋ ብለው የሚያጠፉትን መለየት ያስፈልጋል፡፡ የኢዮብ ወዳጆች ስለመናገራቸው እንጂ ቃላቸው እዚያ ጋር ስለሚያፈርሰው ነገር አላሰቡም፡፡ ቃላቸው ኢዮብን ወደ ሀዘንና ምሬት ውስጥ ከተተው፡፡ በእግዚአብሔር ላይ እንዲጠይቅ፣ ከሌሎች ይልቅ የበደልኩት ምንድነው? እንዲል አደረገው፡፡ ኢዮብ በመጨረሻ አደከሙት፤ መናገር ስለቻሉ ሐቀኞች፣ መግለጥ ስለቻሉ ዳኞች የሆኑ መሰላቸው፡፡ ብዙ በተናገርን ቁጥር ዕዳችን እንደሚበረክት ምነው ባወቅን! ለሰው የምንመክረውን እኛም በመከራችን ወቅት ለራሳችን መምከር ብንችል እንዴት መልካም ነበር!
 
በዚህ ጊዜ ኢዮብ፡- “ነፍሴን የምትነዘንዙ÷ በቃልስ የምታደቅቁኝ እስከ መቼ ነው?” አለ (ኢዮብ 19÷2)፡፡ ኢዮብ አሁን የታመመው በሥጋው ነው። አካሉን በገል እስኪፍቅ ሕመሙ አላስተኛ ብሎታል ባልንጀሮቹ ደግሞ በነፍስ ይነዘንዙታል፡፡ እነዚህ ወዳጆቹ የነፍስ ብጉንጅ፣ የማይታይ ቁስል ሆነውበታል፡፡ የሥጋ መከራ ስብራት፣ ውልቃት፣ ግርፋት … ናቸው፡፡ የነፍስ መከራ ግን ስድብ፣ ነቀፋ፣ ውግዘት፣ የፍርድ መዛባት፣ ንቀት፣ … ናቸው፡፡ የመንፈስ መከራ ግን ከእግዚአብሔር መለየት ነው፡፡ ትልቁ መከራም የመንፈስ መከራ ነው፡፡ 
ሰዎችን በሥጋ ሕመማቸው ሊጠይቁ ሄደው በነፍሳቸው አሳምመው የሚመለሱ ብዙዎች ናቸው፡፡ በነፍስ ካሳመሟቸው በኋላ እነዚያ ታማሚዎች የመንፈስ በሽታ ይገጥማቸዋል፡፡ በምሬት ከእግዚአብሔር ይለያሉ፡፡ ብዙ በሽተኞች ከበሽታቸው ይልቅ የሰው አንደበት፣ ከመክሳታቸው ይልቅ የሰው ሽሙጥ ያሰቃያቸዋል፡፡ ከዚያ ሁሉ በላይ ሐኪሙ ካሳመመ፣ ወዳጅ አቊሳይ ከሆነ ብርቱ ስቃይ ነው፡፡ 
ኢዮብ በሥጋው ሕመም ላይ የነፍስ ሕመም እንዳደረሱበት ተናገረ፡- “ነፍሴን የምትነዘንዙ÷ በቃልስ የምታደቅቁኝ እስከ መቼ ነው?” አለ (ኢዮ. 19÷4-2)።  ንዝናዜ የማያስተኛ፣ የማያስቀምጥ፣ ፋታ የማይሰጥ፣ ሊታገሡት የማይቻል፣ እስከ ነፍስ ጠልቆ የሚሰማ፣ ልብን የሚሠውር ነው፡ የኢዮብ ባልንጀሮች ያወቁ መስሏቸው እየገደሉት፣ ያዘኑ መስሏቸው እየዘበቱበት ነበር፡፡ ልፋቱ አልቀረላቸውም፣ ዋጋ ግን አላገኙም፡፡ ትልቁ ኪሣራ ልፋቱ አለ፣ ዋጋ ግን አለማግኘት ነው፡፡ የኢዮብ ባልንጀሮች የሚያስቡትን ይናገሩ፣ የተናገሩትንም ያምኑ ነበር፡፡ እኛ ከተናገርን፣ ሦስታችን ከፈረድን በርግጥ ኃጢአት ሠርተሃል እያሉት ነው፡፡ ኢዮብ ግን “በቃልስ የምታደቅቁኝ እስከ መቼ ነው?” አለ። 
የሚያደቅ ነገር ከባድ የሆነ ክብደትና አቅም ያለው ነው፡፡ መዶሻ ያደቃል ቃል ከዚያ በላይ የማድቀቅ አቅም አለው፡፡ በመዶሻ የተሰበረ በወጌሻ ይጠገናል፣ በቃል የተሰበረ ግን በወጌሻ አይጠገንም፡፡ ምላስ አጥንት የላትም፣ ነገር ግን አጥንት ታደቅቃለች፡፡ ኢዮብ የጉዳቱን ልክ እየተናገረ ነው፡፡ ዛሬም በቃል የዳኑ እንዳሉ ሁሉ በቃል የደቀቁ፣ እህ እያሉ የሚያቃስቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ 
ሴትዬዋ ሐኪም ዘንድ ሄደው በሽታቸውን ለሐኪሙ ሲያስረዱ፡- “ልክ እኩለ ሌሊት ሲሆን ጦሩን ይስልና ከእሳቱ ባሕር ያጠቅስና መሐል ደረቴ ላይ ይሰካዋል፡፡ ከዚያ ይነቅለውና በስለቱ ጀርባዬን እየሸቀሸቀ በእሳቱ እያነደደ ይደለድለዋል፡፡ ከዚያ ጎዳናውን ሠርቶ ሲጨርስ እንደ ሞተ ሰው እሆናለሁ፡፡ ሲነጋ አትሞችም በምን መብትሽ ብሎ ውሃውን ቸልሶ ያነቃኛል ከዚያ… ” ሲሉ ሐኪሙ አቋረጣቸውና እሜቴ እርሶን ላክም ወይስ አማርኛዎን ላክም አላቸው ይባላል፡፡ የሆነውን በግልጥ ሁኔታ መግለጥ እንጂ ሥዕላዊ ቃላት ለሐኪም አይጠቅምም፡፡ ሐኪምና ጠንቋይ ከእኛ እየጠየቀ ነውና መስመሩን በትክክል ልናስይዘው ይገባል፡፡ ዛሬም ቃላቸው ሊታከም የሚገባው ብዙዎች ናቸው፡፡ 
ይልቊንም ቀኑ አልፎ የሌሊቱ ጨለማ በመጣባቸው፣ ወድቀው በሚያቃስቱ ላይ አማርኛ የሚለማመዱ፣ ቃላት የሚያዋቅሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ምናልባት ይህ ችግር ከመምጣቱ በፊት መክርን መክርን አልሰማ ብለውን ቢሆን እንኳ ከወደቁ በኋላ መውቀስ አይገባም፡፡ ከእኛ ቃል በላይ መከራ እያዋራቸው ነውና፡፡ ማጽናናት ጸጋ ነው ማጽናናት የማይችሉ የአንደበታቸውን ቆሻሻ የታመመው ላይ ደፍተው የሚመለሱ ብዙዎች ናቸው፡፡ በእውነት ያምራል ብለው ከተናገሩት ይከፋል ብለው የተውት ይሻላል። በቃላቸው ሰውን ወደ ሕመም የሚያደርሱ፣ የታመመውን እንዳይነሣ የሚያደርጉ የሰይጣን መልእክተኞች ናቸው፡፡ የብዙዎቻችንም አንደበት ቢዘምርም፣ ቢቀድስም ቀጥሎ ለዲያብሎስ ይከራያል፡፡ በፈረንጅ አገር የሚቀደስባቸው ቤተ ክርስቲያኖች ቀጥሎ ጭፍራ ይካሄድባቸዋል፡፡ ኪራይ ናቸውና። የኪራይ አንደበትም ሲያመሰግንና ሲራገም ይኖራል፡፡ 
በጥይት ስለተገደሉ ሰዎች የወንጀል ሪፖርቶች ይወጣሉ፣ ብዙ ሀዘንም ይደረጋል፡፡ በአንደበት ስለተገደሉ ሰዎች፣ በሐሰተኛ ስም ማጥፋት በመንፈሳቸው ስለተረሸኑ ሰዎች ግን ሪፖርት የለንም፡፡ በጥይት የሚገድሉ ሰዎችን የምናወግዘው እኛ በመንፈስ የምንገድለው ነንና፡፡ በሥጋ የገደሉትን እያወገዝን በመንፈስ መግደል ይበልጥ ነፍሰ ገዳይነት ነው፡፡ 
ቃል ቢመክሩት መላሽ፣ ቢያጽናኑበት ፈዋሽ ነው፡፡ ቃል ቢተኩሱበት ገዳይ፣ ቢያወግዙበት አድቃቂ ነው፡፡ የክርስቲያን አንደበት ግን ሙት ቀስቃሽ፣ የሄደውን መላሽ፣ በፍቅር የታሸ፣ በጣዕም የበለፀገ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በአንደበታችን ያደቀቅናቸውን ዛሬ ይቅርታ እንጠይቅ፡፡ 
ዛሬም ሳይድኑ የሚያክሙ፣ ሳይኖሩ ሞቱ የሚሉ፣ ሳያምኑ መናፍቅ የሚሉ፣ ሳያውቁ እናስተምር የሚሉ… ነፍሳችንን ነዝንዘዋታል፡፡ በቃላቸውም ድጅኖ ስንቱን አድቅቀውታል፡፡ በሰው ቃል የተሰበራችሁ በእግዚአብሔር ቃል ተነሡ። ዘመኑ የትንሣኤ ነውና፡፡

ያጋሩ

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።