የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የማላይህ ቦታ አጣሁ

 የልብን ጩኸት የምትሰማ ፣ የነፍስን መቃተት የምታደምጥ ፣ የፍጥረት መሸበር ግድ የሚልህ ፣ እረኛ ያጣው መንጋ የሚያሳዝንህ ፣ መጠለያ አጥቶ የሚሮጠው የሚያራራህ ፣ መሪው ተነቅሎ የሚከንፈውን ሠረገላ በዓይንህ ጥቅሻ የምትመራ ፣ የመጨረሻዬ መጣ ላለው መጀመሪያን አክሊል አድርገህ የምትሸልም ፣ ምን ይሉኛል ብሎ ራሱን ያሰረውን ከአሉተኛ ትውልድ የምታድን ፣ የት ልድረስ ለሚለው መሸሸጊያ የምትሆን ፣ ራሱ ላስጠላው ዋጋ የምትሆን አንተ እግዚአብሔር ነህ ። ፍጥረት ሁሉ ይስማ አንተ ያህዌ ነህ ።
ከዓለም ፊት ማጥቆር በላይ ያንተ ፈገግታ ለእኔ ግሩም ነው ። አናውቀውም ተብሎ ከመካድ በላይ ከዘላለም በፊት ባንተ መታሰቤ ለእኔ ልዩ ነው ። ጆሮ አትስጡት ተብሎ ከሚዘመተው በላይ ጸሎቴን መስማትህ ዕፁብ ነው ። እንዳይነሣ እርገጡት ከሚባለው በላይ የተዘረጋልኝ እጅህ ለእኔ ትንሣኤ ነው ። ሌት የማስበው ፣ ቀን የማመላልሰው መኖሬን ነው ። እንደ ኖርሁ አውቃለሁ እንዴት እንደ ኖርሁ ግን ምሥጢሩ አንተ ጋ ነው ። ሳላየው ያጎረሰኝ እጅህ ጥጋቤ ነው ። በማላይህ ዘመን ሁሉ ታየኝ ነበር ። እስካይህ ብትጠብቅ ኖሮ እስካሁን በጨለማ ነበርሁ ። የእልፍኙም የበረሃው አምላክ አንተ ነህ ። ጌታውም ሎሌውም ላንተ ያው ነው ። የሰው ፍቅር እንጂ የሰው ደረጃ የለህም ። ከቦታ ፣ ከጊዜ ፣ ከሁኔታ ባይ ትሠራለህ ። እንዳማረብህ ያለኸው ሆይ የሚረግፈው ዓለም እንዳያታክተኝ አቅሜ ነህ ። እንደ ጸናህ ያለኸው ሆይ እልፍ ፣ እልፍ የሚለው ይህ ጊዜ እንዳያናውጠኝ ዓለቴ ነህ ። እንዳፈቀርህ ያለኸው የሚሰናበቱ ወዳጆች ተስፋ እንዳያስቆርጡኝ ዋሴ ነህ ።ስያዝ የምታስለቅቀኝ የክፉ ቀን ስንቄ ነህ ።
ጌታ ሆይ የማላይህ ቦታ የለም ። እልፍ ሠራዊት ሳይ የዚህ ሁሉ መጋቢ ማነው እላለሁ ። እንደ አንድ ሰው የምመግበው እኔ ነኝ ትለኛለህ ። ብዙ በሽተኛ ሳይ የዚህ ሁሉ አልጋ አንጣፊው ማነው እላለሁ ። ሠርቼ የማስነሣው እኔ ነኝ ትለኛለህ ። አያሌ ስደተኛን ሳይ የዚህ ሁሉ ተቀባይ ማነው እላለሁ ። አንተን አገር ያላመድሁ ለዚህም አለሁ ትለኛለህ ። ሺህ ሕፃናት ሲወለዱ የዚህ ሁሉ አሳዳጊ ማነው እላለሁ ። አንተን ያሳደግሁ ዛሬም ያው ነኝ ትለኛለህ ። የዓመታት ርዝማኔ ጠባይህን አይለውጠውም ወይ ስልህ እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም ትለኛለህ ። የምከፍልበት መብራት ስንቴ ይሄዳል ፣ ያንተ ፀሐይ ግን በነጻ ይሰጠኛል ። የማልሰጋው ስጦታህ ቡሩክ ነው ።
መድኅኔ ሆይ አንተን የማልሰማበት  ቦታ የለም ። በነገሥታት አዋጅ ውስጥ እሰማሃለሁ ። አላርፍም ብሎ ምድርን ላጎሳቆለ የሰው ልጅ እግዚአብሔር ዓለም አቀፍ ሰንበት አወጀ እላለሁ ። ምድሩ ሲያርፍ ፣ ሰማይ ከሰው ብክለት ሲጸዳ ደስ ያለህ ይመስለኛል ። በጠቢባን ምክር ውስጥ እሰማሃለሁ ፣ የማላውቀውን የልቤን ትርታ ፣ የኩላሊቴን ሥራ ስሰማ አሁንም አንተን እሰማሃለሁ ። በጨዋታ መሐል እኔ ሰማይ ነኝ ። አንተ ደግሞ በምድር አለህ ፣ በወንድሜ ውስጥ አለህ ፣ በልቤ አለህ ። ከሰማይ ዝምታ ፣ ከምድር ዝርጋታ ውስጥ እንደገና ድምፅህን እሰማለሁ ። የድንበር መስመር የሌላቸው ሰማይና ምድር ሲያጫውቱኝ አሁንም እሰማሃለሁ ። በአበቦች ውበት ፣ በእንስሳት ገርነት ፣ በአራዊት አትንኩኝ ባይነት ውስጥ አንተን እሰማሃለሁ ። የፈጠርከውን አለመውደድ ትክክል አይደለህም ብሎ አንተን መስደብ ሆነብኝ ። የሌለህበት የለም ፣ እኔ የሌለሁበት አንተ አለህ ። ብዕር እያነባ ክብርህን ፣ ሰባኪ እየደከመ ገናንነትህን ፣ መላእክት እየታደሱ ልዕልናህን ፣ ድሆች እየተከዙ የምትመጣዋን ቀንህን ያወድሳሉ ። ይህችን ጽፌ እስክጨርስም ዕድሜዬን እሰጋለሁ ። ስለ ዕድሜ ምጽዋትህ ባለጠጋው ሆይ አመሰግንሃለሁ ።
ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ክብር ምስጋና ይገባሃል ። ከምታልቀዋ ከዛሬዋ ቀን እስከማይፈጸም ዘመን ፤ ከልባችን እስከ አርያም አሜን ። የሚሰማህ አሜን ይበል ።
የነግህ ምስጋና 18
መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ