የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የማያልፍ ርስት

“ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ ” 1ጴጥ  .1:3- 5::

ሐዋርያው መልእክቱን የጻፈው ለተበተኑ የአይሁድ ክርስቲያኖች ነው። ሐዋርያው የኢየሩሳሌም ጳጳስ ነው። የሀገረ ስብከቱ ክርስቲያኖች ቢያንስ ስምንት ሺህ የሚያህሉት ከእስጢፋኖስ ሞት በኋላ በመጣው ስደት ተበትነዋል። እርሱ ቤተ ክርቲያንን ፣ ሀገረ ስብከቴን ለቅቄ አልሄድም ብሎ በኢየሩሳሌም ቀርቶአል። የምንስብካቸው ነገ ስደት፣ መከራ፣ ሞት ሊገጥማቸው ይችላል። እንደ ሰው ወግ ቢሆን ኖሮ ጴጥሮስ በሰበከ እስጢፋኖስ አይገደልም ነበር ። የምንወልዳቸው ልጆቻችን መስቀል እንዳለባቸው መንገር፣ እኛም ማሰብ  አለብን። መስቀል ጠብቀው ደስታ ቢሆን ችግር የለውም ፣ ደስታ ጠብቀው መስቀል ከሆነ ግን ከባድ ነው።

ቅዱስ ጴጥሮስ የኢየሩሳሌም ጳጳስ ተደርጎ ተመደበ። ይህም በሁለት ነገር ነው :- በዕድሜና በትዳር። የሰለጠነችውን ከተማ ሮምን የሄደባት ለጉበኝት ሳይሁን ለሰማዕትነት ነው። የአይሁድ ክርስቲያኖች ከአገር ተሰደዋል ፣ ዘመዶቻቸው የኛ ወገን  አይደላችሁም ብለው  ክደዋቸዋል። በሰው አገር ላይም ድርብ መከራ ይቀበሉ ነበር። ኦሪታዊ አይሁድ፣ ጣዖታዊ አሕዛብ፣ ራሳቸውን የሚያስመልኩ ቄሣሮች ፣ ዘመናውያን ትውልዶች ይሞግቷቸው ነበር ። ሐዋርያው በመከራ እንዲፀኑ በኀዘን እንዲጽናኑ ይህን መልእክት ላከላቸው።

ጌታችን ሞትን በሞቱ ማሸነፉ ለአማንያን ትልቅ ክብርና የመንፈስ ነጻነት ነው፡፡ “እሾህን በእሾህ” እንዲሉ ሞትን በሞቱ አሸነፈ። የእኛን ሞት ወስደ ፣ የእርሱን ሕይወት ሰጠን። መለኮትና ትስብእት በፍጹም ተዋሕዶ አንድ አካል ፣ አንድ ባሕርይ ሁነዋልና አንዱ የአንዱን ክብርና ዕዳ በግድ  ይወስዳል። ባልና ሚስት አንድ ናቸው ስንል በሁለት አካል፣ በአንድ ጠባይ ነው። መለኮትና ትስብእት ግን አንድ አካል ፣ አንድ ባሕርይ ናቸው።  የባልን ክብርም ዕዳም ሚስት ትወርሳለች። አንድ ናቸውና ። እንዲሁም መለኮት የሥጋን ሞት  ፣ ሥጋም የመለኮትን ክብር ይወርሳል። የጌታችን ትንሣኤ ሞትን ያሸነፈ፣ ትንሣኤያችንን ያረጋገጠ ነው።  እርሱ ከሞት በመነሣቱ ምክንያት ቤተ ክርስቲያን ተመሥርታለች። ዳግም ልደትም ወደ ቀደመ ርስታችን የምንገባበት ምሥጢር ሁኗል።

ይህም ዳግም ልደት በውስጡ የያዘው ሀብት ድንቅ ነው፦

1- ሕያው ተስፋ:-

ልጅነትን አግኝተናል። ልጅነት የሚያገኛቸውን ጸጋዎች በሙሉ አላገኘንም። 0ረቦን /መያዣ የሚሆኑ ጥቂት ጸጋዎችን ተቀብለናል። ሞት የማያሸንፈውን ሕያው ተስፋ፣ በጥምቀት አማካይነት ያገኘነው ዳግም ልደት ነው።

2 – የማይጠፋ፦

ስለ ቅድመ አያቱ በቂ ሥዕልና ስሜት ያለው ሰው ማግኘት ከባድ ነው :: የታላቁ እስክንድርን ቤተሰብ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ዘራቸው የጠፋ ብዙዎች ናቸው። እስክንድር “አባቴ ሕይወትን ሰጥቶኛል፣ አሪስቶትል ግን ዓለምን ስጠኝ” ያለ ሰው ነው። በግዛቱ ፀሐይ አትጠልቅም የተባለለት ፣ ምሥራቅና ምዕራብ ዓለም የሚባልን መስመር ያጠፋ ሰው፣ በ32 ዓመቱ ሞተ። ሥልጣኑን ለልጅ መስጠት አቅቶት አራት ጀነራሎቹ ተካፈሉት። የዚህ ዓለም ልደቱም ሥልጣኑም የሚጠፋ ነው ። እንደ ተወርዋሪ ኮከብ ታይቶ ጠፊ ነው። ዳግም ልደት ግን ሞት የማያሸንፈው በትንሣኤ ላይ የተመሠረተ ነው ።

3- እድፈት የሌለበት፦

ነቢዩ ዳዊት፦ “እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ” በማለት ሥጋዊው ልደት እድፈት እንዳለው ይገልጻል። ዳግም ልደት ግን እድፈት የሌለበት ንጹሕ ነው ። እድፍ የነካውን ሁሉ ያሳድፋል። ሰውም ለልጁ  ቂሙን በቀሉን ያወርሳል። አብዛኛው ሰው የማኅበረሰቡ ውጤት ነው። ከአዳም ሞት እንደመጣ ከወላጆችም የሚወሰድ ጠባይ አለ። ሰው በክርስቶስ ካልተለወጠ አባቱን ሲያዝንበት ቢኖርም የአባቱን ጠባይ፣ በሚስቱ ላይ ይደግመዋል። ለእናቱ እያዘነ ኖሮ ሚስቱን ይበድላል። የአስተዳደጋችን ውጤት ነን። ክርስቶስ ግን ከዚህ ሁሉ በላይ ለመኖር፣ በዳግም ልደት ሰማያዊ ኑሮ አድሎናል።

4- የማያልፍ ርስት፦

ዓለም ትላንት በሌላ፣ ዛሬ በእኛ እጅ ናት። ቋሚ ነገር የላትም። መሬት ትዞራለች ከተባለ ብቻዋን ሳይሆነ እኛን ይዛ ትዞራለች። አለሁም፣ አለኝም ማለት ከንቱ ነው። የትላንት ሰጪዎች የዛሬ ለማኞች ሆነዋል። ከተማ እየቆረሱ መስጠት የሚችሉ መቀበሪያ ቦታ አጥተዋል። ዓለም ብላሽ ብትሆንም ዛሬም የምታታልለው ብዙ ሰው  አላት። የራስ፣ የደጃዝማች የሚኒስትር ልጅ መሆን  ርስቱ ያልፋል። ትርፉም ስደት ይሆናል። የትልቁ ጌታ ልጅ መሆን ግን ርስቱ አያልፍም።

ይህን የሚያህል ታላቅ ልጅነት ያገኘነው በትንሣኤው ኃይል ነው። መስፈርቱም የምሕረቱ ብዛት ነው ይለናል። “የጌታችን አምላክና አባት ይባረክ” ይላል። ለለበሰው ሥጋ ራሱ ወልድም አምላክ ነው ። አብም አምላክ ነው። ጌታችን ካረገ በኋላ እንዲህ መባሉ፦

1- የለበሰውን ሥጋ ጥሎ አለመሄዱን ፣
2- ተዋሕዶው መጠፋፋት የሌለበት መሆኑን ፣
3. የእኛ ሥጋ ዘላለማዊ ዙፋንን መጋራቱን ያሳየናል።

ሐዋርያው ዳግሞ ለወለደን አብ፣ ልጅ ተብሎ ልጅ ላሰኘን ወልድ ፣ ለሰማያዊ ልደት ላበቃን “ከማኅፀነ ዮርዳኖስ፣ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ተወልደናል” እንድንል ያበቃንን ጌታ መንፈስ ቅዱስን ያመሰግናል። ከማመስገን በቀር ምንም የምንከፍለው የለንም። ሥጋዊ ወላጆችም ተወላጆችም ይሞታሉ። ይህ አባትነትና ልጅነት ግን ዘላለማዊ ነው። አባት እናትን አጣሁ ብሎ ማዘን፣ ወገን የለኝም ብሎ መጨነቅ  እንግዲህ ቀረ ። ሁለተኛው ልደት የማያስረሳው የዓለም ቁስል የለም። አንዳንድ ሰዎች የጡት ልጅነት ጠይቀው አጥተዋል። እኛ ግን—

ተመስገን!
ከንጉሥ የሚወለድ ወንድ ልዑል፣ ሴትም ልዕልት ናቸው። ከሰማያዊ ንጉሥ ልዑላንና ልዕልቶች የሚያሰኝ  ሥልጣን ያለው ልጅነት የሰጠን አምላካችን ይባረክ።

ሞኙ  ሰው ልቅሶ ሲስማ የሞተው ተከራይ ነው ባለቤት ? ይላል ። ሁሉም ተከራይ መሆኑን አላወቀም። ዛሬ ቁጭ  ብለን ቡና የምንጠጣበት ሳሎን ነገ  መንገድ ይወጣበታል። ዛሬ “ከቤቴ ውጣ” ብለን ካባረርንበት ቤታችን በሸክም እንወጣለን። የደከምንለት ለማንም ፣ አንዳንዴም ለማንፈልገው ሰው ይሆናል። የማያልፍ ርስትን መያዝ ያሻናል። መያዣውም በክርስቶስ ማመን፣ ንስሐ መግባት፣ ምሥጢራትን መካፈል ነው።

ዲያቆን አሸናፊ  መኰንን
ተጻፈ ሚያዝያ 26 ቀን 2015 ዓ.ም

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ