የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የማይታጠፍ ጥላ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

                                                          ማክሰኞ ፣ ጥቅምት 04 /  2007 ዓ.ም
ዐፄ ዮሐንስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ሆነው በነገሡበት ዘመን ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የጎጃም፣ ንጉሥ ሚኒልክ የሸዋ ነገሥታት ነበሩ፡፡ ዐፄ ዮሐንስ ልባቸውም፣ ፍቅራቸውም፣ እምነታቸውም ከሚኒልክ ይልቅ እንደ ልጅ በሚያዩአቸው በንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ላይ ነበረ፡፡ ሚኒልክም ይህንን ስለሚያውቁ የሚጓዙት በጥንቃቄ ነበር፡፡ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የንጉሠ ነገሥቱን ልብ አግኝቻለሁ ብለው በትዕቢት ተኮፍሰዋል፡፡ ግዛት እያስፋፉም የሚኒልክን ግዛት ወደ ራሳቸው ለማስገባት እንቅስቃሴ ጀመሩ፡፡ ጉዳዩ ከሁለቱ ነገሥታት የጦር መሪዎች ወደ ነገሥታቱ እያለፈ ከሰላምም ወደ ጦርነት እየተቃረበ መጣ፡፡ ሚኒልክም ጉዳዩን ለመመርመር ወደ ዓባይ ዳርቻ ተቃረቡ፡፡ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትም እኔ ብዋጋ የንጉሠ ነገሥቱ የዐፄ ዮሐንስ ጦር ይደርስልኛል በሚል ስሜት ይሁን አሊያም በሚያነሡት ጦርነት ከዐፄ ዮሐንስ ያን ያህል ቊጣ አይደርስብኝም በሚል የመተማመን መንፈስ ይሁን ለጦርነት ልባቸው በጣም ተነሣሣ። መልእክተኛም ወደ ሚኒልክ ልከው የጦርነት ቦታ ይምረጡ ብለው የትዕቢት ቃል፣ ጦር ይውረድልኝ የሚል ምሕላ አሰሙ፡፡ ሚኒልክም የክርስቲያን ደም በከንቱ አይፍሰስ በሚል ነገሩ እንዲበርድ ቢፈልጉም ከንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ዘንድ ግን ነገሩ እንደ ፍርሃት ተቆጠረ፡፡ ጦርነቱም የማይቀር ሆኖ በእምባቦ ላይ ተካሄደ። ጦርነቱን የጀመረውና ለጥቂት ጊዜያት ያጠቃው የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ሠራዊት ነበር፡፡ በጀግንነታቸው የታወቁት ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ዳር ሆነው ትእዛዝ እንዲሰጡ ቢጠየቁም መሐል ገብተው ማዋጋት ቀጠሉ፡፡

        የንጉሥ ሚኒልክ ሠራዊት ግን በንጉሡ ታግዶ እኔ ትእዛዝ ሳልሰጥ አንድ ጥይት እንዳይተኰስ ስላሉ ሠራዊቱ ሁሉ ተኝቶ ትእዛዝ ይጠብቃል፡፡ ንጉሥ ሚኒልክም በጥይት እሩምታ መሐል በፈረሳቸው ተቀምጠው መዘዋወርና ነገሩን መከታተል ቀጠሉ፡፡ ፈረሳቸውም አንገቱን ተመትቶ ወደቀ፡፡ ሌላ ፈረስ ቀይረው ቢቀመጡም እርሱም ቆሰለ፡፡ የጎጃም ሠራዊት ዒላማ ውስጥ አስገብቷቸው ነበረ፡፡ ንጉሡ ዒላማ ውስጥ የገቡት በተዘረጋላቸው ጥላ መሆኑን የተገነዘበው አሽከር ጥላውን አጠፈው፡፡ በዚህ ጊዜ ምኒልክ፡- “የእኔ ጥላ አይታጠፍም ዘርጋ” ብለው ተቆጡ፡፡ ወዲያው የጎጃም ጦር እየፎከረ ቀረበ፡፡ በዚህ ጊዜ ምታ ብለው ሚኒልክ ትእዛዝ ሰጡ፡፡ መሬት ላይ የተኛው ሠራዊት በደረቱ እየተሳበ፣ እንደ ዔሊ አንገቱን ቀና እያደረገ የጎጃምን ሠራዊት መጣል ጀመረ፡፡ ከጥቂት ሰዓታት ውጊያ በኋላ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ተማርከውና ቆስለው እምኒልክ ዘንድ ቀረቡ፡፡ ማሩኝ ብለው ቢወድቁ ምኒልክ፡- “አይዞህ ምንም አላደርግህ ተነሣና ሳመኝ” ብለው እጃቸውን ዘረጉላቸው በመቁሰላቸውም አዝነው ቊስላቸውን አጠቡላቸው፡፡


        ጦርነት በአጭር ታጥቀው፣ አንገትን ቀብረው፣ በርከክ ብለው የሚዋጉበት ነው፡፡ ሚኒልክ ግን በልዩ ኩራት በክብር ልብሳቸው፣ አንገታቸውን አቅንተው፣ በፈረስ ተቀምጠው ይንጎራደዱ ነበር፡፡ ጥይት ንጉሥ የሚያውቅ መስሏቸው ይሆን? ወይስ በኃይለ ኢየሱስ ክርስቶስ ተማምነው? ከዚህ ሁሉ በላይ በቤተ መንግሥት እንደነበረው ሥርዓት በጦርነትም ጥላ ተዘርግቶላቸው ይንጎማለሉ ነበር፡፡ በጦርነት ውስጥ በጥላ የሚንቀሳቀስ ንጉሥ ሚኒልክ መሆናቸውን ማንም ያውቅ ነበር፡፡ የጎጃም ሠራዊት ሚኒልክን ባያውቃቸው እንኳ በጥላቸው ግን ለይቷቸው ነበር፡፡ ንጉሥ በጥላው ይለያል፡፡ በጥንት ዘመን ጥላ የሚዘረጋለት ትልቅ ሰው ነበር፡፡ ስሙም ጃንጥላ ተብሏል፡፡ ጃን ማለት ትልቅ ክቡር ማለት ነው፡፡ የትልቅ ሰው ጥላ ማለት ነው፡፡

        ለሚኒልክ ጥላው መታጠፉ እንደ ሽንፈት ነበር፡፡ በጦርነት ውስጥም ቢሆን የእኔ ጥላ አይታጠፍም ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ጠላት ግን ከሩቅ ንጉሡን በጥላቸው ለያቸው፡፡ ንጉሡንም ገደልኩ እያለ ሁለት ፈረሶቻቸውን መታ፡፡ በሦስተኛው ግን ንጉሡ ድል ነሡት፡፡ አሽከሩ ያስጠቃቸው ያ የተዘረጋ ጥላ መሆኑን ዓይቶ ጥላውን አጠፈ፡፡ ንጉሥ ሚኒልክ ግን፡- “የእኔ ጥላ አይታጠይም ዘርጋ” አሉት፡፡ ጦርነት ያማረው፣ ጉልበቴን ልፈትሽ ያለው፣ የተዘጋጀው፣ ቀጠሮ የያዘው ሠራዊት ከነ መሪው ድል ሆነ፡፡ ንጉሥ ሚኒልክ ግን በሌላ መሣሪያ አሸነፉት፡፡ በይቅርታና በፍቅር! የሚኒልክ ጥላ ብቻ ሳይሆን በጦርነት ውስጥም ፍቅራቸውም አይታጠፍም ነበር።

        እገሌን አውቃለሁ፣ እገሌ ሹም ይወደኛል፣ እገሌ ባለሥልጣን ብነካ አያስችለውም ማለት በእውነት ሞኝነት ነው፡፡ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የንጉሠ ነገሥቱን ወዳጅነት ለጊዜው ችግር አልደረሰላቸውም፡፡ ከሩቅ ንጉሥ የቅርብ ጸሎት ይሻላል። ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ይረዱኛል የሚሏቸው ዐፄ ዮሐንስ ሰሜን ናቸው፡፡ ጦርነቱ ያለው መሐል አገር ነው፡፡ መቊሰልም፣ መማረክም የሆነው ንጉሠ ነገሥቱ ከሥልጣን ሳይወርዱ፣ ፍቅራቸውን ሳይለውጡ ነው፡፡ ሰው አያድንም፣ ፍጡር አያድንም፡፡ እግዚአብሔር ብቻ የዘላለም ትምክሕት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል፡- “ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችና በአለቆች አትታመኑ፡፡ ነፍሱ ትወጣለች ወደ መሬቱም ይመለሳል፤ ያን ጊዜ ምክሩ ሁሉ ይጠፋል፡፡ የያዕቆብ አምላክ ረዳቱ የሆነ ተስፋውም በአምላኩ በእግዚአብሔር የሆነ ሰው ምስጉን ነው፤ እርሱም ሰማይንና ምድርን ባሕርንም÷ በእነርሱ ያለውንም ሁሉ የፈጠረ፤ እውነትን ለዘላለም የሚጠብቅ፤ ለተበደሉት የሚፈርድ ለተራቡ ምግብን የሚሰጥ ነው” ይላል (መዝ. 145(146)÷ 3-7)፡፡

        ዛሬም በትልልቆች ያለንን መታመን እግዚአብሔር ሊያስጥለን ይፈልጋል፡፡ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር የምንጥልበት ማንኛውም ነገር ጣኦት ነው፡፡ እግዚአብሔር ከእርሱ ውጭ ሌላ እንዲመለክ አይፈልግምና ጣኦት የሆነብንን ነገር ይሰብረዋል፡፡ የተማመንባቸው ሹሞች እያሉ እንጠቃለን፣ ፍርድ ይጓደልብናል፣ እንደውም የግፍ ግፍ ይደርስብናል፡፡ ከጥንት እስከ ዛሬ የተማመኑበት እንኳን ሊዋጋልን መልሶ ይወጋናል፡፡ ያላመነው እግዚአብሔር ግን በዓይነ ምሕረት ዓይቶናል፡፡ አንድ ኮሚኒስት ጭንቅ ደርሶበት ሲጸልይ፡- “የማላምንህ እግዚአብሔር እባክህ እርዳኝ” አለ ይባላል፡፡ ዛሬም የረዳን ያላመነው እግዚአብሔር ነው፡፡ ያመናቸውማ የጉም ስፍር ሆነውብናል፡፡

        የዓለም ጦርነት መሠረቱ ምንድነው? ስንል ኩራትና ስግብግብነት ነው፡፡ ጦር አምጣ፣ ወንድ ልጅ እየበላ መተኛት ሥራው ሆነ የሚሉ ትዕቢተኞች የጦርነት መነሻ ናቸው፡፡ የራሴ ይበቃኛል የማይሉ እነ ሁሉን ላፌም የዓለም ጦርነት መሠረት ናቸው፡፡ ውጤቱ ግን ትዕቢተኞች ይዋረዳሉ፣ ስግብግቦች የያዙትንም ይነጠቃሉ፡፡ ሰዎች በፍቅር የሰጡንን ስጦታ የምናስጠብቀው በፍቅር ብቻ ነው፡፡ በፍቅር የሰጡንን በጠብ ለማስከበር ከተነሣን የሰጡንን ይነሡናል፡፡ የፍቅር ስጦታ በፍቅር ብቻ ይኖራል፡፡ በበላይ ሹም መመካት የሁሉ የበላይ የሆነውን ጌታ መናቅ ነው፡፡ ጠቡም ከእግዚአብሔር ጋር ነው፡፡ እውነተኛ ቅድስናም እግዚአብሔርን በማየት የሆነ መታዘዝ እንጂ የበላይን በማየት የሆነ መታዘዝ አይደለም፡፡ ትዕቢት በመጀመሪያ ከሰው ቀጥሎ ከራስ ጋር ያጣላል። ለዘላለም ግን ከእግዚአብሔር ይለያል፡፡

        ትልቅ ሰው ከሩቅ የሚታወቀው በጥላው ወይም በጃንጥላው ነው፡፡ ዛሬ ጃንጥላ መያዝ ከፀሐይና ከዝናብ ጋር እንጂ ከክብር ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ ዛሬ ከሩቅ የምንለይበት የክብር ጥላችን ሊታጠፍ አይገባውም፡፡ ሰዎች ከሩቅ አገር ድረስ ወደ እኛ የሚገሰግሱበት፣ ተለይተን የምንታወቅበት የፍቅር፣ የደግነት ጥላ ሊኖረን ይችላል፡፡ ጠላት ግን ብጎዳቸው አይጎዱኝም፣ ብመታቸው አይከሱኝም ብሎ ያንን ጥላ ዒላማ አድርጎት ይሆናል፡፡ አጠገባችን ያሉትም ያስጠቃህ ይህ ጥላ ነውና ይታጠፍ እያሉን ይሆናል፡፡ በክፉ ቀንም ግን የእኔ ጥላ አይታጠፍም ብለን ልንቆጣ ይገባናል፡፡

        መልካምነት ዕድሜ የሚኖረው ሰዎችን ሳይሆን እግዚአብሔር ብቻ እያየን ስናደርገው ነው፡፡ የመልካም ነገር ደሞዝ ሰጪው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ መልካምነት ለጊዜው አስጠቂ ይመስላል፡፡ መልካምነት ግን ኅሊናን ማትረፊያ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ክብሩ ያለው በአገሩ ነው፡፡ የዕቃ አገር ሠሪው ነው፡፡ የሰውም አገሩ እግዚብሔር ነው፡፡ መልካምነትም አገሯ በሰማይ ነው፡፡ በእውነት ለነፍስ ብቻ ሳይሆን ለሥጋም ሰላም መልካምነት ወሳኝ ነው፡፡

        ያለንበት ዘመን ጦርነት ይመስላል፡፡ በጦርነት ውስጥ ውይይት የለም፡፡ በጦርነት ውስጥ ሁሉም የራሱን ገዳይ ነገር ይረጫል፡፡ ጦርነት ንብረትን ብቻ ሳይሆን ሕይወትን አውዳሚ ነው፡፡ በጦርነት ውስጥ ሕግ የለም፡፡ ጦርነቱ የራሱ ሕግ ቢኖረውም የሕጉ ግብ ግን መደምሰስ ነው፡፡ የጦርነት ሕግ፡- ሕግ አልባነትን የሚወልድ ነው፡፡ ሰው በሰው የሚጨክነው በጦርነት ዘመን ነው፡፡ ጦርነትም ሕጋዊ ጭካኔ ተብሎ ሊጠራ ይችላል። ዘመናችን ሁሉም አቅም አለኝ ሁሉም አውቃለሁ የሚልበት፣ በጎች እረኛን የማይከተሉበት፣ የመሪና የተመሪነት ቅርጽ የጠፋበት በእኩልነት ስም መደማመጥ ጠፍቶ የተደናቆርንበት ዘመን ነው፡፡ የለመድነው ተበላልጦ መደማመጥን ነው፣ ተካክሎ መደማመጥ ፍቅር መሆኑ አልገባንም፡፡ ያለንበት ዘመን ለነገ ሳይባል የወንድም አበሳ በአደባባይ የሚወጣበት፣ ከሰው ኅሊና እንዲወጣ የሚጣርበት ነው፡፡ ያለንበት ዘመን ስለ ንብረት የምናለቅስበት ስለ ሰው ሕይወት ግን ግዴለሽ የሆንበት ነው፡፡ ስለዚህ ዘመኑን ጦርነት ብንለው ይገልጠዋል፡፡ ወከባ እንጂ መረጋጋት የለም፣ የሚኖረውም ሬሣ ተራምዶ ነው፡፡ ከጭፍራ ቤት አጠገብ በረሀብ ለመሞት የሚያጣጥሩ አሉ፡፡ በውድ መኪኖች አጠገቡ ብርቱ ችግርን የሚጋፈጡ ይታያሉ፡፡

        ጥቂት መልካሞች፣ ከነጥላቸው ከነክብራቸው ያሉ የሚቆጠሩ ጥቂት ደጎች ቢኖሩም ቀስቱ በዝቶባቸዋል፡፡ የእነዚህ መልካሞች ቃላቸው ብቻ ሳይሆን ኑሮአቸውም ክፉዎችን ይወቅሳል። ደጋጎች የክፉዎችን ክፋት ስለሚያጎሉባቸው የክፉዎች የቀስት ዒላማ ይሆናሉ። መልካምነት ዋጋውን እያጣ ቢመስልም የመልካምነት ዋጋ ግን አይወድቅም። የበላይ ጠባቂው መለኮት ነውና። ብዙ ቀስት ቢበዛብንም የፍቅራችን ጥላ አይታጠፍም ብለን ልንቆጣ ይገባል። ብዙ ፍላጻ ቢበዛብንም የደግነታችን ጥላ አይታጠፍም ልንል ይገባናል። መልካምነትን ልንይዝ የሚገባን በራሱ ክብር ስለሆነ ደግሞም የሰብእናም መገለጫ ስለሆነ እንጂ ለመከበር ሊሆን አይገባውም። የገዛ ነፍሳችን በቃህ በጦርነት ውስጥ ጥላ አይያዝም። ይታጠፍ ትለናለች። የገዛ ወዳጆቻችንና ትዳራችን ያስጠቃችሁ ይህ ጥላ ነውና ይታጠፍ ይሉናል። እኛ ግን በእግዚአብሔር ቅንዓት በታላቅም የጽድቅ ቁጣ የእኔ ጥላ አይታጠፍም ልንል ይገባናል። ማሳመን መወያየት አይገባም። በታላቅ ቅንዓት የእኔ ጥላ አይታጠፍም በማለት የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን የማያስበውን ሰይጣንን ልንገሥጽ ይገባናል /ማቴ. 16፡23/።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ